በጎፋ ዞን በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ለዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት ሚናቸው የጎላ እንደሆነ ተገለፀ
የጎፋ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ
ቀን 2022-10-05
በጎፋ ዞን ኡባ ደብረፀሃይ ወረዳ በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ለዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት ሚናቸው የጎላ መሆኑን የወረዳው አስተዳደሪ ገለፀ። በወረዳው በ 230 ሄክታር መሬት ላይ ማምረት የጀመረው የመሳይ በዛብህ አግሮ ቢዝነስ ስራ በከፍተኛ ሁኔታ ለውጥ እያስመዘገበ እንደሚገኝ ተገልጿል። በወረዳው ኬንቾ ቀበሌ በ370 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎችን ለማልማት ማሳ የተረከበው መሳይ በዛብህ አግሮ ቢዝነስ በአሁኑ ወቅት በ230 ሄክታር መሬት ላይ ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ እና ለአከባቢ ገበያ ሊውሉ የሚችሉ የተለያዩ ምርቶችን በስፋት በማምረት ላይ እንደሚገኝ የሚናገሩት የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኮማንደር ፊሊቨር ቁጮ ናቸው። ኮማንደር ፊሊቨር አክለውም ከ124 በላይ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ገልፀው የምርት ሽያጭ በሚከናወንበት ወቅት እስከ 180 ሺህ ብር ለመንግስት ገቢ እንደሚያስገቡም አስረድተዋል። በጎፋ ዞን የኡባ ደብረፀሃይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኤልቶ እፀና በበኩላቸው አከባቢው ለኢንቨስትመንት ስራዎች ምቹ በመሆኑ የተለያዩ ባለሀብቶች በዘርፉ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ አስረድተዋል። የአከባቢው አርሶአደሮችም ምርጥ ተሞክሮዎችን ወደ ስራ በመቀየር ምርታማነትን ለማሳደግ መጣር እንዳለባቸው አሳስበዋል። የአከባቢው ወጣቶች የተፈጠረላቸውን የስራ ዕድል ተጠቅመው በመስራታቸው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከመርዳት ባለፈ ከሚያገኙት ገቢ እየቆጠቡ እንደሚገኙም አንስተዋል።
የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ የመስኖ ስንዴን ውጤታማ ለማድረግ ለአምራች አርሶ አደሮች የውሃ መሳቢያ ፓምፕ መቅረቡን ገለፀ
የጎፋ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ
ቀን 2022-10-04
የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ በ2015 ዓ.ም በዞኑ ያሉትን የውሃ አለኝታና የቴክኖሎጂ አማራጮችን አሟጦ በመጠቀምና አብዛኛዉን አርሶ አደር ተደራሽና በልማቱ ተሳታፊ በአጠቃላይ (በአንደኛ ዙር 11,739 ሄ/ር እና በሁለተኛ ዙር 1,401 ሄ/ር) በምርት ወቅቱ በአጠላይ 13,140 ሄ/ር መሬት በመስኖ ለማልማት ግብ ጥሎ የቅድሜ ዝግጅት ስራ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ ለበጋ መስኖ ስራ በ10 ወረዳዎች 24 የመስኖ አማራጮች የተለዩ ሲሆን 18ቱ ዘመናዊ መስኖ አውታር እና 6 ባህላዊ መስኖ አማራጮች ናቸው፡፡ በተጨማሪ ለበጋ መስኖ የሚረዱ 132 ነባር እና 74 አዲስ በድምሩ 206 የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ተዘጋጅተዋል፡፡ ከዓምናው የመስኖ ስንዴ አፈፃፀም ልምድ በመውሰድ በ2015 ምርት ዘመን በዞኑ በተለዩ ወረዳዎች ዘመናዊ የመስኖ ተቋም ባለባቸዉ አካባቢዎችና የወንዝ ጠለፋን መሠረት በማድረግ 969 ሄ/ር የበጋ መስኖ ስንዴን ለማምረት በማቀድ የቅድሜ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ እንደምገኝም መመሪያው አስታውቋል፡፡ የመስኖ ስንዴ ስራን ውጤታማ ለማድረግ የዘመናዊ መስኖ አማራጭ ለሌላቸው የመስኖ ስንዴን ለማምረት ለተለዩ አርሶ አደሮች የሚሠራጭ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ መቀረቡን በመጥቅስ የውሃ መሳቢያ ፓምፑ የሚሰራጨው ኩታ ገጠም ማሣ ያላቸው በቡድን ለተደራጁ አርሶ አደሮች መሆኑን ገልጿል።
ኦሞ ባንክ 6ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን እካሄደ
የጎፋ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ
ቀን 2022-08-26
ቀደም ሲል ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ በሚል ስያሜ የሚታወቀው እና በቅርቡ ስያሜውን "ኦሞ ባንክ" በሚል ወደ ባንክ ያደገው ተቋም 6ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን በሀዋሳ ከተማ አካሄደ። ጠቅላላ ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የኦሞ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን ከበደ የመንግስት የፋይናንስ ተቋም የነበረው የኦሞ ማይክሮፋይናንስ ተቋም ከ25 ዓመታት በኋላ ወደ ባንክ ማደጉን ገልጸዋል። ተቋሙ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች በተለይም የአርሶአደሮች፣ አርብቶአደሮችና የከተማ ነዋሪዎችን ህይወት መቀየር የቻለ መሆኑንም ተናግረዋል። ወደ ባንክ ያደገው ተቋሙ በቀጣይም የህዝቡ ኑሮ እንዲሻሻል ይሠራል ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢ ባንኩ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት ቀልጣፋ፣ ተመራጭ፣ ተዓማኒ፣ ዘመናዊና ተወዳዳሪ እንዲሆን ባለ አክሲዮኖች ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ባንኩ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ባንክ እንደመሆኑ መጠን በብድር አቅርቦት፣ በቁጠባና በመሠረታዊ የባንክ አገልግሎት ወቅቱ የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልቶ እንዲገኝ ባለሀብቶችም ሚናቸውን እንዲወጡ ነው ያሳሰቡት። የኦሞ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ኃ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው ተቋሙ ቀደም ሲል የሚሰጠውን አገልግሎት በማሻሻል እና አቀራረቡን በማዘመን በዘርፉ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ተዘጋጅቷል ብለዋል። ባንኩ እያካሄደ ባለው 6ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው የጉባኤውን ጸሐፊ የመረጠ ሲሆን የባንኩን ገንዘብም በሙሉ ድምፅ በማጽደቅ አሳድጓል። የኦሞ ባንክ በ712 ሚሊየን 20 ሺ በተከፈለ ገንዘብ ሥራ መጀመሩም ተገልጿል።
ያግኙን
☏046-777-1536
ተዛማጅ ሊንኮች
Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved
Gofa,Ethiopia