የጎፋ እድገትና ብልጽግና ማህበር ሞዴል ማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ ግንባታ 150 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ
የጎፋ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ
ቀን 2022-05-30
የጎፋ እድገትና ብልጽግና ማህበር በሣውላ አጠቃላይ ሆስፒታል ለሚገነባው ሞዴል ማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ 150 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ። በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የሆስፒታሉ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ጌትነት በጋሻው ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር የዞኑ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። የጎፋ እድገትና ብልጽግና ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ደግፌ ኃ/ማሪያም በበኩላቸው ለሕዝቡ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት በፍትሐዊነት ተደራሽ እንዲሆን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በቀጣይም ልማት ማህበሩ ለጤና ተቋማት የሚያደረገውን የቁሳቁስና ገንዘብ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል። የሣውላ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ግዛቸው ቦሎ በበኩላቸው ግንባታው ሲጠናቀቅ በመንግሥት ጤና ተቋማት በሚሸጠው በተመሳሳይ ዋጋ ለህብረተሰቡ መድኃኒት ማቅረብ የሚያስችል አማራጭ የመድኃኒት ቤት ነው ሲሉ ገልጸዋል። ከ 1.6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚገነባው ሞዴል ማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ ግንባታ በጎፋ ዞን አስተዳደር ፤ በጎፋ ዕድገትና ብልጽግና ማህበር ድጋፍና በሆስፒታሉ የውስጥ ገቢ በጀት የሚሸፈን መሆኑን ዶክተር ግዛቸው ተናግረዋል። ግንባታው በሦስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለማህበረሰቡ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኑሮ ውድነትና የገበያ ችግሮችን ለመፍታት በምደረገው ጥረት ህብረት ስራ ማህበራት የድርሻቸውን እንድወጡ ተጠየቀ።
ቀን 2022-05-15
ህብረት ስራ ማህበራት በገበያ ላይ ያለውን ዋጋ ጭማሪና ኑሮ ውድነት ለማሻሻል የድርሻቸውን እንዲወጡ የክልሉ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ገለጸ። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዜሮ አሚሪያ ሲራጅ በሆሳዕና እየተካሄደ ባለው ንቅናቄ መድረክ ላይ እንደተናገሩት ህብረት ስራ ማህበራት ተዛብቶ ያለውን የገበያ ሥርዓት ሚዛን በማስጠበቅ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች ሊጠናከሩ ይገባል። አርሶ አደሩ ላመረተው ምርት ተገቢ ጥቅም እንዲያገኝና የከተማው ሸማች ኅብረተሰብም ጥራት ያለውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ በማድረግ የኑሮ ውድነቱን ጫና ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ እና አማካሪ አቶ ስንታየሁ ሀሰን በበኩላቸው፣ ህብረት ሥራ ማህበራት በግሉ ዘርፍ በምርት በማቀነባበር ተግባር የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን በማገናኘት የእርስ በእርስና ቀጣይነት ያለው የአምራች ሸማች ቀጥተኛ የገበያ ትስስርንና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ዘርፍ ነው ሲሉ ገልጸዋል። አቶ ስንታየሁ አክለውም ህብረት ሥራ ማህበራት የአባሎቻቸውን ገቢ ከማሳደጋቸውም በላይ የሀገሪቱን ቀጣይና ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት ተገቢውን ድጋፍ እንድያደርጉም አሳስበዋል።
የጎፋ ዞን ሁለተኛ ዙር መደበኛ የስፖርት ምክር ቤት ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል
የጎፋ ዞን ሁለተኛ ዙር መደበኛ የስፖርት ምክር ቤት ጉባኤ በዛሬው ዕለት እየተካሄደ ይገኛል። በጉባኤው የዞኑ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የወረዳና ከተማ አስተዳደር ሥራ አስፈፃሚ አካላት፣ የወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና የሥራ ሂደት አስተባባሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተሳትፈውበታል። የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዞኑ ስፖርት ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ጌትነት በጋሻው የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ስፖርት ለሰው ልጆች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። ዋና አስተዳዳሪው አክለውም በሁሉም መዋቅሮች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በማዘጋጀት ለስፖርታዊ ውድድሮች ማመቻቸት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አወቀ አለሙ በበኩላቸው ስፖርት ለጤንነት ብቻም ሳይሆን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ከማጠናከር አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል። የመምሪያው ኃላፊ አያይዘውም የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ባዘጋጀው ዞናዊ ልዩ ልዩ የበጋ ስፖርት ሻምፒዮና ለተሳተፉ አካላት የምስጋናና የእውቅና ምስክር ሰርተፍኬት በጉባኤው እንደሚበረከትላቸው ተናግረዋል። በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ የተለያዩ አጀንዳዎች የፀደቁ ሲሆን የም/ቤቱ መተዳደሪያና መቋቋሚያ ደንብ ፣ የሀብት አሰባሰብ ፣ የሙያ አበል እና የላብ መተኪያ ክፊያዎች መመሪያ እንዲሁም የጎፋ ዞን ልዩ ልዩ ስፖርት ሻምፒዮና እና የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ሪፖርት ሰነድ በመምሪያው ኃላፊ አቶ አወቀ እና ስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጠንክር ግዛቸው ቀርቧል። በቀረቡ ሰነዶች ላይ ውይይት ተደርጎ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ለበለጠ መረጃ የተሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
ያግኙን
☏046-777-1536
አስተያይት ይስጡን
ተዛማጅ ሊንኮች
የደቡብ ኢትዮጳያ ክልል መንግስት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ
አዳዲስ የስራ ማስታወቂያዎች
የቆዩ የስራ ማስታወቂያዎች
የስፖርት ዜናዎች
ቱሪዝም
የጎፋ ማህበረሰብ ባህል
የኦይዳ ማህበረሰብ ባህል
Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved Gofa,Ethiopia
By logging in you agree to our Terms and Conditions and Privacy Policy