ቀን፡- 2021-01-05
የኦይዳ ብሔረሰብ የብሔሩ ታጋይ እራሻ አልቶ ባሎ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት በጎፋ ዞን ከሚገኙ ሁለት ነባር ፣ብሔረሰቦች መካከል አንዱ ነው፤፤ ብሔረሰቡ አዋሳኞች በሰሜን ፡- ገዜ ጐፋ ወረዳ፣በደቡብ፣ ኡባ ደብረ-ፀሐይ ወረዳ በምስራቅ ደንባ ጐፋ ወረዳ፣ በምዕራብ ሰሜን አሪ ወረዳ ያዋስኗታል፡፡ ብሔረሰቡ የሚገኝበት የወረዳው ቆዳ ስፋት 20,000 ሄክታሪ የወረዳው ስነ-ምህዳር ሦስት ዓይነት ስሆን እነሱም፡-ደጋ፡- 15% ወይናደጋ፡-75% እና ቆላ፡- 10%የያዘ ከመሆኑ ባሻገር የወረዳዋ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፡-ተራራማ 80% ሜዳማ 15% ወጣገባ 5% እንደሆነ ይታወቃል፡፡የወረዳ የአፍር ዓይነት አምስት ስሆን እነሱም፡- ለም አፈር፣ አስዳማ አፈር፣ ሸክላማ አፍር፣ ጨዋማ አፈር እና አሸዋማ አፈር ናቸው፡፡ ዓመታዊ የወረዳው ሙቀት መጠን በአማካይ ከፍተኛ 270c ፣ ዝቅተኛ 13.20c እና አማካይ 12.20c እና የዝናብ መጠን ከፍተኛ 1700ml ፣ ዝቅተኛ 1300ml እና አማካይ 1300 እስከ 1700ml ነው፡፡ የብሔረሰቡ አመጣጥ ዞንጋር ተብሎ ከሚጠራው ወንድና ጉዳሮ ተብላ ከሚትጠራው ሴት መነሻ እንደሆነ የሀገር ሽማግሌዎች ትውፊት ይነገራል፡፡ እነዚህ ሰዎች በባልጣ ቀበሌ ከላይኛው ባልጣ እንዳአክ ምንጭ አከባቢ ተነስተው ወደ ታችኛው ባልጣ ቀበሌ በመውረድ መኖረያቸውን ዞባ በሚባል ንዑስ ያደረጉና ከአብራካቸው የተወለደው ታላቅ ልጃቸው ማዳር እና ሌሎች ልጆች እየተዋለዱና እየተባዙ ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱ በጎሳ ለመከፋፈል ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል፡፡ ከየወገናቸው የተለያየ ስያሜና መጠሪያ ተሰጥቶ እስከ አሁን በብሔረሰቡ የሚገኙ አርባ ሁለቱ ጎሳዎች ዣዥንቴ፣ ሻራ፣ ጋኮና፣ አጋር፣ አንታል፣ ወርቃ፣ ካታ፣ ዙል፣ ዞባ፣ አማን፣ አይግር፣ ሸፋል፣ አዢ፣ ጋናዝ፣ ጐሀ፣ አሳ፣ አይካ፣ ሳርካ፣ ዛግርሳ፣ ሞያ፣ ዝና፣ ጉዳርቲ፣ ሳውራር፣ ጋርፃ፣ ኦቅ፣ ማንግ፣ ጋንጅሬ፣ ዛካ፣ ጐንት፣ ሶዙም፣ ሃይቦማል፣ ጎሎማል፣ ወርዝ፣ ጋድር፣ ጋውህና፣ ማሽን፣ ጋንሳ፣ አምፋርሲ፣ ዛግን፣ ዛል፣ ማርንት፣ እና አርጋማ ስሆኑ ደቢ እና ኦይድ ካፋሼ ከሚትባል ሴት የተወለዱ መንታ ልጆች እየተባዙ ስመጡ ደቢና እና ኦይዲና የሚል የጎሳ ስያሜ ተሰጥቶአቸው የኦይዳ ብሔረሰብ ቁጥር ወደ አርባ አራት ክፍ ብሏል፡፡ የጐሳዎች ማህበራዊ አደረጃጀት ማሊ፣ ፆማ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በሌላ በኩል በሕዝቦች እንቅስቃሴ ዘመን ወደ አካባቢው የመጡ ከዕደ-ጥበብ ሥራ ዘርፍ በሸክላ ሥራና በብረት ቅጥቄጣ ሥራ የተሰማሩ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡ በጊዜው ለዕደ-ጥበብ ሙያ ለሕዝቡ ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ ለእነዚህ ማኒ (ፉጋ) በማለት ስያሜ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ማህበራዊ አደረጃጀት ማሊ፣ ፆማ እና ማኒ በመባል በሦስት ተመድቧል፡፡ የብሔረሰቡ አሰፋፈር የኦይዳ ብሔረሰብ በዋናነት የሚገኘው በብሔረሰቡ ስም በሚጠራው በኦይዳ ወረዳ ቀበሊያት ባልጣ ፣ ባጋራ ፣ ሻላባሪንዴ ፣ ዳይሻላ ፣ ማርካላ ፣ ላሜ ፣ ጋራ-ዲዳ ፣ ጐይቢ ፣ ሱቢ ፣ ዳልሻ ፣ ገምቲ-ጎቾ፣ ጋርዳ ፣ ቃሞኦ ሾምባ ፣ ካላ-ማሎ፣ ሸፊቴ ቁጥር-1 ፣ ሸፊቴ ቁጥር-2 እና ሐርብር ሲሆን አልፎ አልፎ በሁሉም በሀገሪቱ ክፍሎች ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር ተቀላቅለው ይኖራሉ፡፡ በአካባቢው የሚነገረው አፌ-ታሪክ ከሕዝቦች እንቅስቃሴ ዘመን ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ለም የእርሻ መሬትና ግጦሽ ፍለጋ እና ከነፍጠኛው መሬት ከበርቴዎች አስተዳደር ጫና ለማምለጥ ሸሽተው ከሌላ አካባቢ የመጡ ሕዝቦች በዛሬው ኦይዳ ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅለው በአንድነት ይኖራሉ፡፡ የኦይዳ ብሔረሰብ የሰፈረባቸው አካባቢ መልክዓ ምድር አቀማመጥ በቆላ ፣ በወይነ-ደጋና ደጋ የአየር ንብረት የተከፋፈለና እና ለኑሮ ምቹ በመሆኑ አከባቢው ለም ነው ፣ እርጥብ ነው ፣ ምቹ ነው ፣ በማለት በኦይደኛው ቃል “oya”ለምለም ከሚባለው ቃል መነሻ በመውስድ ኦይዳ /oyda/ የሚል ሲያሜ ሰጥተዋል፡፡ ባህላዊ አስተዳደር የኦይዳ ብሔረሰብ በአከባቢው ዘመናዊ የመንግስት መዋቅር ከመዝረጋቱ በፊት ራሱን በራሱ የሚመራበት እና የሚያስተዳደርበት ባህላዊ የአስተዳደር መዋቅር ነበረው፡፡ የባህላዊ አስተዳደር መዋቅር አደረጃጀቱ ካቲ ፣ ቢታን ጮማች ፣ ጎድ እና ቡጫ በተሰኘ ተዋረዳዊ አስተዳደር እርኬኖች የተዋቀረ ስሆን ሁሉም የየራሳቸው የሥራ ኃላፊነትና ድርሻ አላቸው፡፡ ካቲ ፡- ንጉስ /Kaati/ በበላይነት ሥልጣን እርኬን ባለሙሉ ሥልጣን ባለቤት ሲሆን ሥልጣን የመያዝ ዕውቅና ለዣዥንቴ ጐሳ ተሰጥቶ ከጐሳው አባል፡- 1ኛ ካቲ ዣዦ ለኦይዳ ብሔረሰብ የመጀመሪያ ካቲ ሆኖ ተመርጠዋል፡፡ 2ኛ ካቲ ዣልሽ ሲሆኑ በዣልሽ አስተዳደር ዘመን ሕዝቡ እርካታ በማጣቱ ከዣዥንቴ ጐሳ የካቲነት ሥልጣን ወደ ሻራ ጐሳ እንዲሸጋግር ሕዝበ ዉሳኔ በመስጠት ከሻራ ጐሳ ካቲ ጉሳ ሆኖ እንደተመረጠ ይነገራል፡፡ ከሻራ ጎሳ የተሾመው ንጉስ /Kaati/ ጉሳ አስተዳደሪነታቸው ለሕዝቡ ሳይመች ሲቀር ሕዝቡ እንደባህላቸው በመመካከር ከሻራ ጎሳ ወደ ደቢና ጎሳ ሥልጣን ለማሸጋገር ሲፈልጉ ለንግስና ሥርዓቱ የሚያስፈልገውን ባህላዊ ዝግጅት ጠላ ሙሉ እና ብረት ነክ ቁሳቁሶችን በሚያስቀምጡት ቦታ ያስቀመጠውን ለማየት አንጋሾች በንጋታው ማሌዳ ሄደው ጠላው ተደፍተው እና ብረት ነክ ቁሳቁሶችን ተበታትነው ስላገኙ አዉሬ ገብቶ እንዳበላሸ በማሰብ ይህ ዕድሌብስ ነው በማለት ካቲ እንዳይሆን ከልክለዋል፡፡ ምክንያቱም ለካቲነት (ንግስና) የታጨ ዕጩ ለንግስናው ሥርዓት ለሹሜቱ ያዘጋጀው መስዋዕት በማናቸውም ሁኔታ መነካካት ወይም መነካካት ወይም መበላሸት በፍጹም የማይፈቀድ ስለሆነ ነው፡፡ ፡፡ በሌላ አማራጭ ኦይዲን ለማንገስ ያጩታል፡፡ ዕጮኛው ኦይዲ ለንግስና ሥርዓቱ ያዘጋጀውን ባህላዊ ዝግጅት በአንዳች ምክንያት እንዳይበላሽ በከፍተኛ ጥንቃቄ ጠብቆ በማሳደሩ በህዝቡ ዘንድ ይሁንታ አግኝቶ ካቲ ሆኖ ተሹሟል፡፡ ደቢ ከካቲ ቀጥሎ ባለው እርኬን ብታን ሆኖ እንዲሰራ ህዝቡ ሹሟል፡፡ የኦይዲ ጎሳ ሀረግ ኢትዮጵያ በዘመናዊ መንግስት መዋቅር እስከምዘረጋ ድረስ የራሱን ወሴን በማስጠበቅ በበላይነት ስመራ እንደቆየ እና አፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት እስከ ንጉሱ ዘመን ማብቂያ ድረስም ባህላዊ አስተዳደር መዋቅሩ በየእርኬኑ የሐይማኖት ሥርዓት ማስፈፀሚያ ኃላፊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በመንግስት እንደ አማካሪ ሆኖ ሲያገለግል እንደቆየ ይነገራል፡፡ የኦይዳ ብሔረሰብ ባህላዊ አስተዳደር መዋቅር እርኬን ንጉስ /Kaati/ የኦይዳ ብሔረሰብ ንጉስ /Kaati/ ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤት ሲሆን ራሱን ግዛትና ሕዝብ በበላይነት ይመራል፣ ያስተዳድራል፡፡ ከእርሱ በታች ባሉ እርኬኖች ያልተፈቱ አለመግባበቶች ሲቀርቡ በመመርመር የመጨረሻ ዉሳኔ ይሰጣል፡፡ ከአጉራባች አከባቢዎች ጋር ግጭት ስፈጠረ ወታደራዊ ኃይሉ ይመራል፡፡ ግጭቱ አልፎ ወደ ፀብ የሚቀየር ከሆነ ጦሪነት ያውጃል፡፡ ከባህላዊ ሐይማኖታዊ ሥርዓቶች በአካባቢ ድርቅ ወረርሽን ስከሰት ከታችኛው ተዋረድ እርኬን ኃላፊዎች ጋር በመሆን የተለያዩ ውርሶ /የማንፃት/ ሥራ በመሥራት የመጨረሻ መፍትሔ ፈጣሪ እንደሆነ በብሔረሰቡ ባህል ስለሚታመን ፈጣሪን /Xoozi/ ለህዝቡ ይማፅናል፡፡ የእርስ በእርስ ግጭቶችን ያስታርቃል፡፡ ከነፍስ ግዲያ ጋር የተገናኙ ግጭቶችን የሟችና ገዳይ ወገን በማግባባት ገዳዩን ለሟች ወገን የደም ካሣ በማስከፈልና ለእርቀ-ሠላሙ ማረጋገጫ ሁለቱም ወገን የበግ ግልገል የምግብና የመጠጥ /Kuntsts/ ካቀረቡ በግዛቱ ዳርቻ ወስደው ገዳዩ ወገንን ከግዛቱ ወሴን ማዶ እና ሟች ወገንን በግዛቱ ክልል ዉስጥ በማቆም ንጉስ /Kaati/ እና ከእርሳቸው ጋር ያሉት እርቅ አስፈፃሚዎች በመካከላቸው በመሆን የበጎችን ደም በመቀባት ከሁለቱን ወገን የቀረበውን ምግብና መጠጥ በማቅመስ ያስታርቃል እርቁን በመሀላ ያፀናል፡፡ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩ ተግባራት ካቲ በዋናነት የሚፈጽመቸው ተግባራት ናቸው፡፡ በኦይዳ ብሔረሰብ ባህላዊ አስተዳደር ካቲ ሆኖ የነገሱ ግለበሶች፡- 1ኛ. ካቲ ዣዦ 2ኛ.ካቲ ዣልሽ 3ኛ.ካቲ ጉሳ 4ኛ.ካቲ ኦይዲ 5ኛ.ካቲ ድጋ 6ኛ.ካቲ ቡዴ 7ኛ.ካቲ አይሎ 8ኛ.ካቲ ካቺ 9ኛ.ካቲ ወጋ 10ኛ.ካቲ ጎድ 11ኛ.ካቲ ሳዴ 12ኛ.ካቲ ካማ 13ኛ.ካቲ አፋ 14ኛ. ካቲ ግጋ ናቸው፡፡ ቢታን /Bitan/ ቢታን ከካቲ ቀጥሎ የሚገኝ ባህላዊ የሥልጣን አርኬን ሲሆን ከሁለት እስከ አምስት ቀበሊያት የሚመራ ሆኖ በኦይዳ ብሔረሰብ ቢታን በዋናነት በባህላዊ እምነት ሥርዓት ላይ ያተኩራል፡፡ በራሱ ከሚመራው አካባቢ ያሉትን ሕዝች በማስተዳደር ድርቅና ወረረሽን ስከሰት ዉርሶ ሥርዓት ይፈፅማል፡፡ አለመግባባቶችን ያስታርቃል፡፡ ከካቲው የሚተላለፈውን ትዕዛዝ በተዋረድ ወደ ታችኛውን እርኬን ያወርዳል፡፡ ከታችኛውን እርኬን የሚቀርቡ ጥያቄዎችንና ሃሳቦችን ተቀብሎ ይፈፅማል፡፡ከአቅም በላይ ስሆን ወደ ካቲ ያደርሳል፡፡ ጮማች /Comachch/ በካቲ አስተዳደር እርኬን ከቢታን ቀጥሎ የሚገኝ ባህላዊ አስተዳደር እርኬን ሲሆን በዘመኑ አደረጃጀት የቀበሌ መዋቅር ነው፡፡ ጮማች የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት በድንብር ጉዳይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ያስተዳድራል፡፡ የስድብና መዋረድ አቤቱታዎችን ይመረምራል፣ ዉሳኔ ይሰጣል፡፡ የተለያዩ ባህላዊ ሃይማታዊ ሥርዓቶችን ያስፈፅማል፡፡ ለካቲ እና ቢታን ማሣ በወቅቱ እንዲታረስ ያስተባብራል፡፡ ግጭቶችን ያስታርቃል፡ ከአቅሙ በላይ በሆኑ ጉዳዮች ቢታንን በመጋበዝ የማውጣጣት ተግባር ያከናውናል፡፡ በጦሪነትና አደን ታዋቂ የሆኑ ግለሰቦችን ከሕብዝ ጋር በማዋሄድ ሥራ ይሰራል፡፡ ምክንያቱን በጦርነት ወይም በአደን በወቅት የተላበሰውን ጭካነ እና አደን ከሆነ ለዓይን የገደላቸውን የአውሬ መንፈስ ያልፍበታል ተብሎ ስለሚታመን የቁጣ /ጭካኔ/ ማብረጃ ተብሎ የሚፈፅም “ብርሴ” /birse/ ያከናውናል፡፡ የግለሰቡን ጀግነትን ያረጋግጣል፡፡ የለቅሶ ሥነ-ሥርዓት ከቀብር በኋላ በለቀስተኛው ቤት ደግሞ ለቅሶ እንዳይመጣ (የለቅሶ ማንሻ “ዳሜ /dame wodhe/” ሥርዓት ያስፈፅማል፡፡ ጐድ /god/ ይህ ባህላዊ አስተዳደር እርኬን ከጮማች ቀጥሎ የሚገኝ ሲሆን እንደሌሎች ባህላዊ መሪዎች በግልና በቡድን የሚያከናውናቸው ተግባራት አሉት፡፡ ጐዲ በሚገኝበት አከባቢ ካሉት ባህላዊ መሪዎችና ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት በአካባቢው የሚከሰቱ በዋናነት ባህላዊ ሃይማኖት ነክ ጉዳዮች ላይ ያቶክራል፡፡ ከሚተግባራቸው ጉዳዮች ዋና ዋናዎቹ በሚቀርብበት አካባቢ ከጐሣ ወይም ቤተሰብ አባላት አቅም በላይ የሆኑ ከአከባቢ ሕዝብና ከብሔረሰቡ ባህል ዉግዝ የሆኑ ጉዳዮች ሲከሰቱ የወግና ባህል መተላለፍ ኃጥአት ወይም ጐሜ /Gome/ የማንፃት ሥርዓት ያስፈፅማል፡፡ ከላይኛው አርኬን በተዋረድ የሚተላለፉ ትዕዛዛትን ያስፈፅማል፡፡ የካቲ ፣ ቢታንና ጮማች እርሻ /Maddo/ ያሳርሳል፡፡ ከሕዝብ የሚቀረቡ ጥያቄዎችን ወደ ላይኛው እርኬን ያደርሳል፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ሕዝቡን ያማክራል፡፡ መዋጮ ያሰባሰባል:: ለካቲ፣ ለቢታንና ለጮማች የሚሰጥ እህል አሰባስቦ ለሚመለከታቸው ያቀርባል፡፡ በፌሾ /Feesho/ በዋና ለቅሶ ቀን ፣ በደቦ ዝናብ እንዳይዘንብ ለላኛው አካል ለዕለቱ ወደ አምላክ እንዲማፀን መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ ቡጫ /Buca/ ቡጫ /Buca/ የመጨረሻ የመዋቅር እርኬን ሲሆን አወቃቀሩ ከሕዝቡ የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ስብስብ ነው፡፡ ይህ መዋቅር እጅግ የሚከብር የሚፈራና ተሰሚነት ያላቸው የሀገር ሽማግሌዎች ዳኝነት የሚሰጥበት መዋቅር ነው፡፡ የሚያከናወኑበት ተግባር ከላይ የተገለፀው የአስተዳደር እርኬኖችን የመሾምና የመሻር ሥልጣን አላቸው፡፡ በሚገኙበት አከባቢ በሚፈጠሩ ማናቸውም ግጭት አለመግባባት ችግሮች የመጀመሪያ ደረጃ አጣሪና ዉሳኔ ሰጪ አካል ሆኖ ከታች ወደላይኛው እርኬን የሚተላለፍ ጉዳዮችን ከላይኛው እርኬን ጋር እየተመካከሩ ዉሳኔ የመስጠትና በሚሰጡት ዉሳኔ በማይስማማው ላይ የመጨረሻ እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን አላቸው፡፡ የእርምጃ ዓይነቶች ከጎሮበት እሳት እንዳይጭሩ መከልከል ከብቶቻቸው ከሕዝቡ ከብት በግጦሽ እንዳይሰማሩ መከልከል ልጆች ከሕዝቡ ልጆች ጋር በሜዳ እንዳይጫወቱ መከልከል እና በማናቸውም ማህበራዊ ጉዳዮች ማግሌለ ወዘተ…. ናቸው፡፡ የኦይዳ ብሔረሰብ የማንነት መገለጫ በዓለም የሚገኙ ሰባዓዊ ፍጡራን ሁሉ ቦታና ጊዜ ሳይገድባቸው ዘርና ቀለም ሳይለያቸው እያንዳንዳቸው የየራሳቸው መገለጫ ሲኖራቸው በጋራ ደግሞ የሚጋሯቸው ባህላዊ ሂደቶች እንዳሏቸው የዘርፉ ሙሁራን ያስረዳሉ፡፡ የአንድ ማህበረሰብ የማንነት መገለጫዎች እሴቶች የራሳቸውንም ሆነ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ አስተዳዳራዊ ፣ ሃይማኖታዊ ሥነ-ልቦናዊ ፣ የማምረቻ መሣሪያዎችን ፣ አመጋገብንና አለባበስ ፣ ቋንቋ ፣ ባህል ፣ አዕምሮአዊና ቁሳዊ እሴት የሚወክልና በአንድ በተወሰነ ወቅት ብቻ ሣይሆን ለረጅም ዘመን በአብሮነት ተቀብለውና አምነው የጋራ መገለጫቸው አድርገው የሚተገብሩበት ነው፡፡ በዚህ መሠረት የኦይዳ ብሔረሰብም የራስ የማንነት መገለጫዎች የሆኑ የዘመን አቆጣጠር ፣ የቋንቋ ፣ የአምልኮ ፣ ባህላዊ የጋብቻ ሥርዓት ፣ የአለባበስ ፣ የአመጋገብ ፣ የለቅሶ ሥነ-ሥርዓት ያለው ሲሆን እነዚህን የማንነት መገለጫ የሆኑትን ታሪካዊ እሴቶች በዝርዝር ቀጥለን እንመለከታለን፡፡ ቋንቋ ቋንቋ የአንድ ብሔረሰብ ማንነት መገለጫ ከሆኑት እሴቶች ዉስጥ ዋንኛው እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑ አንድ ማህበረሰብ የራሱን ባህል ፣ ወግ እና መንፈሳዊ ሥርዓቱን ለመሰሎቹ በተለያዩ መንገዶች የሚገልጽበት ዋንኛ መሣሪያ ቋንቋ ነው፡፡ በቋንቋ ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉት የመስኩ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት ቋንቋ ሰፊ ባህሪያት ያሉት ሲሆኑ ከባህሪያቶቹ አንደኛው መመሳሰል እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ የኦይዳ ብሔረሰብ ቋንቋ ኦይደኛ /oyditstsa/ በመባል የሚታወቅ ስሆን ከኦማዊ ቋንቋዎች ቤተሰብ ይመደባል፡፡ ቋንቋው ከሁሉም ኦሞትክ ብሔረሰቦች ጋር እንዲሚመሳሰል በመስኩ ጥናትና ምርምር ያደረጉት ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ አንድ ቋንቋ ከሌላኛው ቋንቋ ጋር ተመሳሰለ ወይም ተወራረሰ ስንል አንድ ቃል ሙሉ በሙሉ በመውሰድ በጋራ መግባባት መዋል መቻሉን የሚገልጽ ሲሆን ለዚህ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት ዉስጥ ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ አካባቢ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴና በሕዝቦች የሚፈጠሩ ግንኙነቶች ፣ ታሪካዊና ማህበራዊ ቁርኝት የተነሳ መሆኑን ለመገዘንብ ተችሏል፡፡ በመሆኑ የኦይዳ ብሔረሰብ በዞኑ ዉስጥ ካለው ጐፋ ብሔረሰብ ጋር የባህል መመሳሰል ፣ የንግድ ልውውጥና የህዝቦች እንቅስቃሴ መኖር ይበልጥ አንዱ የሌላኛውን ቋንቋ የመናገርና መስማት እንደሚችል ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ባህል ከሚገልጽባቸው መንገዶች አንዱ ቋንቋ ስሆን የእነዚህ ቋንቋዎች መመሳሰል መግባቢያ መሆን ብቻ ሳይሆን ካላቸው የባህልና ቋንቋ መመሳሰል የቆየ አብሮነት ፣ አንድነትና ተግባቦትን የሚያመለክት ቋሚ ቅርስ ነው፡፡ በአጠቃላይ የኦይደኛ ቋንቋ ከኦሞትክ ቋንቋ ተናጋሪ ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋ ጋር የመመሳሰል እና የመወራረስ ባህሪያት እንዳሉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ እምነት ጥንታዊ ማህበረሰቦች የአኗኗር ግንኙነት ሥርዓት ዉስጥ ከሚከሰቱ ማህበራዊ ለውጦች ሳቢያ የሚገጥማቸውን ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎችን ለመከላከል ይረዳናል ብለው ስለሚያምኑ ባህላዊ የአምልኮ ሥርዓት ይፈፀማሉ፡፡ ይህ ባህላዊ አምልኮ ሥርዓት በግለሰቦች መካከል እንዲሁም ግለሰቦች ከማህበረሰቡ ጋር ጤናማና ሠላማዊ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ከጥንት ጀምሮ ከሰው ልጅ ባህላዊ የአምልኮ ሥርዓት የሚፈፀመው በሽታ ፣ ረሀብ ፣ ጦሪነት እንዳይከሰት ከመሆኑም በተጨማሪ ረጅም ዕድሜ እንዲሰጣቸው ፣ ልጆችን ለመወለድ ፣ ወደ እርሻ ተግባር ለመግባት ፣ ምርት ለመሰብሰብ ፣ ከብቶች እንዲራቡና ከድርቅና ከተምች ወረርሽን ለመከላከል የተለያዩ ባህላዊ ሥርዓቶችን በመፈፀም እምነታቸውን ይጠቀማሉ፡፡ በኦይዳ አካባቢ የክርስቲናና እስልምና ሐይማኖት ከመግባታቸው አስቀድሞ ጥንት ሰዎች እምነት ስጀምሩ የአባት ፣ የአያትና የቅድመ-አያቶቻቸው አማልክት በማምለክ እንደጀመሩት መረጃ ሰጪዎች ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ የተፈጥሮ ክስተቶች መብረቅ ንፋስና ዝናብ የእንስሳት በሽታ እና በአገር ላይ ድርቅ እንዳይከሰት ….. ወዘተ የመሳሰሉትን ለመከላከል የአባትና እናታቸው አምላክ /Xoozi/ መልካም ነገር እንዲያመጣላቸው በተመረጡ በባህላዊ አምልኮ ሥፍራ ባህላዊ መሪ በቢታን በህዝብ ላይ ጉዳት እንዲያደርስ የእንስሳት እርድ መስዋዕት ይፈፀማል፡፡ እነዚህ ከላይ የተመከልናቸው ባህላዊ እምነቶች በኦይዳ በአብዛኛው የህብተረሰብ ክፍል ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ዉስጥ በመግባት ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ባህላዊ ተቋሞች ናቸው፡፡ የኦርቶዶክስ ክርስቲና ኃይማኖት ወደ አካባቢ የገባው በ1890ዎች የወራሪው የሚኒልክ ሠራዊትን ተከትሎ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ኃይማኖቱ ወደ አካባቢው ከገባ ረጅም ጊዜ ብሆንም የቆይታ ያህል በአካባቢው በሰፊው እንዳልተስፋፋ መረጃ ሰጪዎች ያስረዳሉ፡፡ እንደ ኦርቶዶክስ ሁሉ የፕሮቴስታንት ኃይማኖት ወደ አካባቢው የገባው በ1920ዎች በሱዳን ኢንተሪየር SIM/sudan interior mission/ አማካኝነት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ምንም እንኳን ከላይ ከተመለክትናቸውን የክርስቲና ኃይማኖት ቁጥራቸው ከፍተኛ ብሆንም አሁን ላይ ባህላዊ የአምልኮ ሥርዓቶች በአንዳንድ አከባቢዎች እንደሚስተዋሉ ለመገንዘብ ችለናል፡፡ በአጠቃላይ የእነዚህ የእምነት ተቋማት ማህበረሰቡን አንድ ላይ በማሰባሰብ የሰዎችን እርስ በርስ ግንኙነት በማሻሻል የህብረተሰቡን አንድነት በማስጠበቅ እንድሁም ግጭቶችን በማስወገድ እና የአገርን ደህነትና ሠላም በመስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳበረከቱ በአከባቢው ነዋሪዎች ይነገራል፡፡ የቤተሰብ ጽንሰ ሃሳብ በኦይዳ ብሔረሰብ በኦይዳ ብሔረሰብ የቤተሰብ መሠረት በአንድ ቤት ዉስጥ የሚኖር አባት ፣ እናትና ልጆች ናቸው፡፡ በዝምድና ያልተሳሰሩ ግን የቤተሰብ መሠረት ከሆኑ ጋር በአንድ ቤት የሚኖሩና በቅርብ ርቀት ሆነው የጋራ ሀብት ተጠቃሚ የሆኑ በአንድ አባዎራ ስር የሚተዳደሩ እንደ ቤተሰብ አባል ብቆጠሩም ከማህበራዊ አንድነታቸው የዘለለ መብት የላቸውም፡፡ በደም ጋብቻ ትስስር በጐሣ አጎትና አክስት ፣ የእናት አባት ፣ እናት ወንድሞች ፣ እህትና አያት ቤተ-ዘመድ /Igina/ ተብሎ የሚጠሩ ስሆን በእናት በኩል /በጋብቻ/ ተሳስረው ዝምድና ተቀላቅለው እስከ ሰባተኛ ትውልድ ድረስ ስሆን በዘር ሀረግ ግንድ የመጣ ቤተሰባዊ ዝምድና በማናቸውም ሁኔታ መቆሚያ የለውም፡፡ አይዳ ብሔረሰብ የቤተዘመድ ቁጥር መብዛት የክብር መግለጫ በመሆን አንድ አባዎራ የማስተዳደር አቅም ሀብትና ንብረት ካለው ሁለትና ከዚያ በላይ ሚስቶችን በማግባት በርካታ ልጆችን በመውለድ ሀብቱንና ንብረቱን እንዲወርስ ይደረግል፡፡ እንደነበረ የሀገር ሽማግሌዎች መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይሁን እንጂ የመጀመሪያዋ ሚስት (Kara Inddo) በመባል የሚትጠራው ትልቅ አክብሮት ሲኖራት ሌሎች ደግሞ (Laggi Inddo) በመባል የሚጠሩ ሲሆን ሁሉንም በአንድ አጥር ግቢ ዉስጥ ብቀመጡ ጥልና ዛቻ ሊፈጠር ይችላል ተብሎ ስለሚታሰብ በተለያየ ቦታ ቤት ተሰርቶላቸው እንዲቀመጡ እንደሚደረግ የመረጃ ምጮች ያስረዳሉ፡፡
ያግኙን
☏046-777-1536
ተዛማጅ ሊንኮች
Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved
Gofa,Ethiopia