በዞኑ የሚገኙ እምቅ ሀብቶች
የጥራጥሬ ሰብሎች
ቀን 2021-08-13
የጥራጥሬ ሰብሎች ቦሎቄ፣ ሽምብራ፣ ባቀላ፣ አተር፣ ማሾ (ግዥንዳ)ና ምስር በዞናችን አብዘኛው ወረዳ ቀበሌያት የሚመረቱ የምግብና የሽያጭ ሰብሎች ናቸው፡፡ ከጥናት ዘመኑ ዓመታዊ የሰብል ልማት ሽፋን አኳያ የጥራጥሬ ሰብል ጠቅላላ ሽፋን 13,021 ሄ/ር ሲሆን ከአጠቃላይ ዓመታዊ ሰብል ሽፋን 7 በመቶ ይይዛል፡፡ ቦሎቄ ከሁሉም የጥራጥሬ ሰብሎች በስፋት የሚመረት ሰብል ሆኖ በጥናት ዘመኑ 3,961 ሄ/ር መሬትን ሲይዝ ከአጠቃላይ ጥራጥሬ ልማት 30.42 % ይሻፍናል፡፡ ያለቴክኖሎጅ በ13 ኩ/ል ምርታማነት 101,725 ኩ/ል ዓመታዊ ምርት ያስገኛል፡፡ ምርታማነት ዝቅተኛ በመሆኑ ለቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይፈልጋል፡፡ ከምርት አጠቃቀም አንፃር 65% ለፍጆታ ሲውል 35% ደግሞ ተሸጦ ገቢ የሚያስገኝ በመሆኑ ከ37,603.7 ኩ/ል በ2700 ብር ሽያጭ 96129990 ብር የሽያጭ ገቢ ያስገኛል፡፡ ባቄላ ከቦሎቄ ቀጥሎ በስፋት የሚመረት የደጋ የጥራጥሬ ሰብል ነው፡፡ 3,369 ሄ/ር ሽፋን ሲይዘ በ13 ኩ/ል ምርታማነት 43,797 ኩ/ል ምርት በአመት ይገኛል፡፡ ለቤት ፍጆታ 40% ሲውል 60% ደግሞ የሚሸጥ ሲሆን በዚሁ መሠረት 26,278.2 ኩ/ል በ2,200 ብር ነጠላ ዋጋ 57,812,040 ብር ገቢ ያስገኛል፡፡ ማሾ(ግዥንዳ) ሙሉ በሙሉ ለሺያጭ የሚውልና ከ10 ዓመት ወደህ በዞናችን የሚመርት ጥራጥሬ ሰብል ነው፡፡ በሁሉም የዞናችን ወረዳ ቀበሌያት መብቀል ይችላል፡፡ በጥናት ግኝት መሰረት በዞኑ 1,830 ሄ/ር የለማ ሲሆን በ9 ኩ/ል ምርታማነት 16470 ኩ/ል ተመርቶ አንድ ኩ/ል 3000 ብር ሲሸጥ በድምሩ 49,410,000 ብር ገቢ ያስገኛል፡፡ ይህ ሰብል በውጪ ገበያ እጅግ በጣም ተፈላጊ ስለሆነ ለገቢ ምንጭ ትኩረት በመስጠት በሰፋትና በብዛት ሊመረት ይገባል፡፡ ሽምብራ በዞኑ 74 ሄ/ር መሬት የሸፈነ ሲሆን በ5 ኩ/ል ምርታማነት 370 ኩ/ል ምርት ይገኛል፡፡ አጠቃቀሙም ልክ እንደማሾ በአብዛኘው ለሽያጭ ሲሆን ለአፈር ለምነነትም ትልቅ ድርሻ ስላለው የብዕር ሰብሎችንም ምርት ያሻሽላልና ተስማሚ አየርና አፈር ባለባቸዉ አከባቢዎች ልማቱ ቢስፋፋ ጠቀሜታው ሊሰፋ ይገባል፡፡ አተር በዞኑ 2,702 ሄ/ር የመሬት ሽፋን የያዘ የደጋና ወይነደጋ ጥራጥሬ ሰብል ነው፡፡ ከ10 ኩ/ል ምርታማነት 27,020 ኩ/ል ምርት በአመት ይገኛል፡፡ ለሽያጭ 65% በማዋል 17,563 ኩ/ል በ2,500 ብር ነጣላ ዋጋ 43,907,500 ብር አመታዊ ገቢ ያስገኛል፡፡ ሰብሉ ከዛላና ሣውላ ከተማ በስተቀር በሁሉም ወረዳ ይመረታል፡፡ ምስር በጥናቱ መሠረት 110 ሄ/ር ብቻ የለማ የደጋ ተፈላጊ የምግብ እህል ሲሆን ከጥራጥሬ ሰብል በጣም ዝቅተኛ ሽፋን ያለው ነው፡፡ በተለይም በተለምዷዊ አመራረት ሥርዓት 4 ኩ/ል ምርታማነት በድምሩ 440 ኩ/ል አመታዊ ምርት ያስገኛል፡፡ ሙሉ በሙሉ ለሽያጭ የሚውል ሲሆን በ3,500 ብር ነጠላ ዋጋ 1,540,000 አመታዊ ገቢ የሚያስገኝ ነው፡፡ በአገር ውስጥ ገበያ ተፈላጊ ምርት በመሆኑ በሙሉ ፓኬጅ በቴክኖሎጅ ትግበራ ታግዞ ቢመረት የላቀ ገቢ ያስገኛል፡፡ የጥራጥሬ ሰብል በኩታ ገጠም (ክላስተር) ተለይቶ ማልማት ከቦለቄ በስተቀር የተለመደ ባይሆንም በተለይ አተርና ባቄላ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲለማ ሊደረግ ይገባል፡፡ ባጠቃላይ የጥራጥሬ ሰብሎች የመሬት ለምነት ለማሻሻል አኳያ ያለው ሚና ቀላል የሚባል ስላይደለ ማሳን አቀያይሮ በመዝራት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ያለው ፋይዳ የላቀ በመሆኑ በወይነ ደጋውና ደጋው የተሻለ ማሳ ሽፋን ያላቸው ወረዳዎች ትኩረት ሰጥተው መሥራት የሚያስፈልግ ይሆናል፡፡
እምቅ የሰብል ሀብት
የሰብል ሀብት
ቀን 2021-08-03
ሰብል የዞናችን ህብረተሰብ የምግብና የገቢ ምንጭ መሆኑና ከ85% በላይ የዞናችን ሕዝብ መተዳደሪያና ከአጠቃላይ እርሻዉ ዘርፍ ገቢ 47.5 በመቶ የያዘ ነው፡፡ የዞናችን ወረዳዎችና ቀበሌያት ቆላ፤ ወይና ደጋና ደጋ የአየር ንብረት የያዘ ሲሆን ማንኛውም ጉልበቱ ለሥራ የደረሰ ሰው በልምድ ቅብብሎሽ እና በኤክሰቴንሽን አገልግሎት ድጋፍ እየተመረተ ያለ ሀብት ነው፡፡ ከምግብ የተረፈው ምርትም ለአመራቹ ተሸጦ ገቢ ከማስገኘት ባለፈ ለሀገራችንና ለውጭ ፋብርካዎች በጥሬ ዕቃነት ያገለግላል፡፡ የሰብል ቅርትና ተረፈ ምርት ለቤት እንስሳት ለመኖ፤ ለማገዶ እና ለቤት ግንባታ አገልግሎት የጎላ ድርሻ አለው፡፡ በዳሰሳ ጥናቱ በተረጋገጠው መሠረት ከጠቅላላ የዞኑ ቆዳ ስፋት 242,495ሄ/ር በተለያዩ የሰብል ዕፅዋት የተሸፈነ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው መልካአም ምድራዊ አቀማመጥና አየር ንብረቱ ለልማቱ ሚቹ መሆኑን ነው፡፡ ቋሚ ሰብሎች ከምግብነት አልፎ የዕፅዋት ሽፋናችን በማደግና ለአየር ንብረት (ኢኮሎጂ) መስተካከል ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ የሰብል ሀብታችን የምግብና የገቢ ዋስትናችን መሠረት ቢሆንም ዘመናዊ ቴክኖሎጂንና የተሻሻለ የአሠራር ሥርዓት አሟጠን ባለመጠቀማችን የተፈለገውን ያክል ተጠቃሚ እንዳንሆን አድርጎናል፡፡ ለኢንዱስትሪዎች የማይተካ ጥሬ ዕቃ የሆነውን ሀብታችንን ዘመኑ ያፈራውን ዕውቀትና ክህሎት እንዲሁም ጊዜና ጉልበት ተጠቅመን የላቀ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በዋናነት በዘርፉ የሚተዳደረውን ህብረተሰብ እና መላው ህብረተሰብ በአጠቃላይ ከምግብ እጥረትና ከድህነት ሊናሻገረው ይገባል፡፡ አገዳ ሰብል በቆሎና ማሽላ በዞናችን ሁሉም ወረዳዎችና ቀበሌያት የሚመረቱ ሲሆን በተለይ በቆሎ ዋና የምግብ ሰብል በመሆኑ በበልግና በመኸር የአዝመራ ወቅት 98,290 ሄ/ር መሬት ሽፋን በመያዝ ከሁሉም ሰብሎች ጋር ሲነፃፀር የመጀመያውን ቦታ ይይዛል፡፡ ይህ ማለት ከአገዳ ሰብል ሽፋን 97.7 በመቶ ከዓመታዊ ሰብሎች ሽፋን 40 በመቶ በመያዝ በቆሎ በሁሉም ወረዳ ቢመረትም ዛላ ወረዳ 21,469 ሄ/ር፣ ዑ/ደ/ፀ/ 20,192 ሄ/ር፣ ደምባ ጎፋ 17,485 ሄ/ር በመሸፈን ትልቁን ድርሽ ይይዛሉ፡፡ በቆሎ በዞናችን እየተገኘ ያለው ምርታማነት በቴክኖሎጅ 45ኩ/ል ያለቴክኖሎጅ 25.5ኩ/ል ስለሆነ ግብዓት ያለመጠቀማችን ምን ያክል እየጎዳን እንዳለ መረዳት ይቻላል፡፡ ጥናቱ በተሰራበት የምርት ዘመን የበቆሎ ምርታማነት 25.5 ኩ/ል ሲሆን ከአገራዊና ክልላዊ ምርታማነት ስነፃፀር በጣም በመቀነስ ጠቅላላ ምርት 2,498,082ኩ/ል ተገኝቷል፡፡ ከመጠይቅ መላሾች በተገኘው መረጃ መሠረት ከጠቅላላ ምርት 15% ለሽያጭ ይውላል እናም 374,712 ኩ/ል በወቅቱ ገበያ 800 ብር ቢሸጥ ከሰብሉ በዓመት 299,769,840 ማግኘት ይቻላል፡፡ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ለበቆሎ ምርት ዕድገት ወሣኝ ግብዓት በመሆኑ ይህንን ቴክኖሎጂ ቢቻል ሙሉ በሙሉ አለበለዚያ ከ75 በመቶ በላይ የመሬት ሽፋናችንን ብንጠቀም ከዞናችን ተርፎ ሌላ አከባቢ መመገብ እንችላለንና የማልማት አቅምንና ፍላጎታችንን ከመፈፀም አቅማችን ጋር አቀናጅተን በትርፍ አምራችነት ተርታ ሊንሰለፍ ይገባል፡፡ ለዚህም የበቆሎ በኩታ ገጠም (ክላስተር) ተለይቶ በልዩ ትኩረት መሥራት የሚያስፈልግ ሲሆን ለበቆሎ ክላስተር የተለየ አከባቢ በዛላ፤ ኡባ/ደ/ፀሐይ፤ ደምባ ጎፋ፣ ገዜ ጎፋና መሎ ኮዛ ቆላው ሰፋፊ ሜዳማ ቦታዎችን በዘመናዊ እርሻ መሣሪያ ታግዞ ማረስና ማልማት ያስፈልጋል፡፡
የግብርና እምቅ ሀብት በጎፋ ዞን
የጎፋ ዞን ግብርና እምቅ ሀብት
ቀን 2021-08-11
ግብርና ለዞናችን ከ85% በላይ የህብረተሰብ ክፍል የሚተዳደርበት፣ የምግብና የገቢ ምንጭ የሆነ፣ ለሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ (ግብይት) የሚያቀርብ፣ ለማንኛውም ዜጋ ምቹ የሥራ ዕድል ማግኛ የሥራ መስክና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ የኢኮኖሚ ዘርፍ ቢሆንም ዘመኑ በሚጠይቀው ቴክኖሎጂ ባለመታገዙ፣ ፈጣን ቀልጣፋና ተደራሽ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ለአርሶ አደሩ ባለመሰጠቱ፣ ችግር ፈቺና ተከታታይ የድጋፍና ክትትል ሥርዓት በአግባቡ አለመዘረጋት፣ በቴክኖሎጂ ግብይት አቅርቦት እጥረትና በመሣሰሉት ማነቆዎች ምክንያት ከዘርፉ ማግኘት ያለብንን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም ማግኘት አልተቻለም፡፡ የግብርና ዕምቅ ሀብታችንን (potentials) ዓይነት፤ መጠንና ሥርጭት፣ የግብርና ልማታችን ያለበትን ደረጃና መሠረታዊ የልማት ማነቆዎችን አንጥሮ በማውጣት የመፍትሄ ሀሣቦችን ለማቅረብ ይቻል ዘንድ ሁሉንም የዞኑን አካባቢዎች ያካተተ፣ የግብርና ልማት ተሣታፊ አካላትን በናሙናነት ያሣተፈ የቃልና የጹህፍ መጠይቅ በማዘጋጀት፣ መሠረታዊ የሶሺዮ-ኢኮኖሚ መረጃ ማጠናቀሪያ ቼክ-ሊስት በማዘጋጀት በአሃዛዊና ገለጻ ዘዴ መረጃዎችን በመሰብሰብ በማደራጀትና በመተንተን የፖቴንሻልና ተግዳሮች ዳሰሳ ጥናቱን ማካሄድ ተችሏል፡፡ በዚሁ መሠረት ዞናችን 455,092 ሄ/ር የመሬት ቆዳ ስፋት ያለው ሆኖ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ደን የተያዘ 12.8%፣ በቋሚ ሰብል የለማ 12%፣ በዓመታዊ ሰብል የለማ 41%፣ በግጦሽ መሬት የተያዘ 8%፣ ወደፊት ሊለማ የሚችል 14% እና ሊለማ የማይችል 3.2% ነው፡፡ ለሰውና እንስሳት መጠጥ እንዲሁም ለመስኖ አገልግሎት የሚውል 56 ወንዞች፣ 655 ምንጮችና ሰፊ የከርሰ ምድር የውሃ አካላት ባለቤት ነው፡፡ ከእንስሳት ሀብት አንጸር ዳልጋ ከብት 1,241,148፣ በግና ፍየል 832,647፣ ጋማ ከብት 94,094፣ ዶሮ 1,378,159 እና በተለያዩ ቀፎች ያለ የንብ ቤተሰብ 57,281 ክምችት ይገኛል፡፡ ከዞናችን የመሬት ቆዳ ሽፋን ውስጥ ለተፋሰስ ልማት የተለዩት ንዑስ ተፋሰሶች በቁጥር 315 እና በመሬት ሽፋን 304,493.4 ሄ/ር ሲሆን ዞኑ በአዲስ መልክ በሚደራጅበት ወቅት ማለትም እስከ 2011 በጀት አመት ድረስ በተቀናጀ ተፋሰስ የለማ መሬት ሽፋን 185,592.2 ነው፡፡ የሰብል ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያን በስፋት መጠቀም ቁልፍ ተግባር ቢሆንም በዋና ዋና ሰብሎች ከሚለማው ማሳ ቴክኖሎጂ ቀመስ የሆነው ከ2012/13 በልግ አፈፃፀም አንፃር 2 መቶና መኸር አፈጻፀም አንፃር ደግሞ 9 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህም ዞናችን ከዚህ ቀደም ወደ ነበረው የምርታማነት ደረጃ ለመመለስ ጠንክሮ መስራት በሚጠይቅ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን ያሳያል፡፡ የወተት ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል የደልጋ ከብት ዝሪያን ማሻሻል ወሣኝ በመሆኑ እስከ 2012/13 በተሰሩ ሥራዎች ከ1,241,148 ጠቅላላ ደልጋ ከብት ውስጥ 22,150 (1.8%) ዲቃላ ናቸው፡፡ ከዝሪያ ማሻሻል ሥራ ባሻገር የመኖ አቅርቦት ማሣደግ ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑ ለሁሉም የቤት እንስሳት ከሚያስፈልገው 2,287,413 ቶን ድርቆሽ መኖ 1,791,799 ቶን (78.3%) ማቅረብ ተችሏል፡፡ ከግብርና ዕምቅ ሀብታችን የላቀ ተጠቃሚ ለመሆን የዘርፉን መሠረታዊ ማነቆዎች ማለትም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ የግብርና ምርት ሥርዓት፣ ዝቅተኛ የቴክኖሎጂ ግብዓት አቅርቦትና አጠቃቀም ላይ ሥርነቀል ለውጥ በማምጣት ጊዜው የሚጠይቀውን ዘመናዊ የግብርና ልማት ለማምጣት ፈጣን ቀልጣፋና ተደራሽ የኤክስቴንሽን አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ለተፈፃሚነቱም መንግስት፣ ግብረሰናይ ድርጅቶች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና ተዋንያን የላቀ ተሣትፎና ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል፡፡
ያግኙን
☏046-777-1536
ተዛማጅ ሊንኮች
Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved
Gofa,Ethiopia