የጎፋ ብሔረሰብ ታሪክ አጠቃላይ ገጽታ

ቀን፡- 2021-08-01


አጠቃላይ ገጽታ የደቡብ ብሐር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 9 ክልሎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች አንዱ ሲሆን ክልሉ በ17 ዞኖችና በ7 ልዩ ወረዳዎች የተከፋፈለ ነው፡፡ የክልሉ አጠቃላይ ስፋትም 105,887.18 ስኳር ኪሎ ሜትር(40,883.27 ማይል) ሲሆን አጠቃላይ የህዝብ ብዛትም 19,170,007 ነው፡፡ የክልሉ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ 6.5157 ºN 36.9541 ºE ሲሆን ክልሉ በደቡብ ኬኒያ ቱርካና ሐይቅ፣ በደቡብ ምዕራብ ከኬኒያና ሱዳን፣በምዕራብ ከደቡብ ሱዳን በሰሜን ምዕራብ ከጋምቤላ ክልል፣በሰሜንና ምስራቅ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ይዋሰናል፡፡ በክልሉ ከ56 በላይ ብሔር ብሐረሰቦች ይገኛሉ፡፡ የጎፋ ዞን በክልሉ ካሉ 17 ዞኖች አንዱ ሲሆን አጠቃላይ ቆዳስፋቷም 4551 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ነው፡፡ የዞኑ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ 5054’N -- 6044’N ላቲትዩድ እና 36020’E-- 37020’E ሎንጊቱድ ነው፡፡ በሰሜን ከዳውሮ ዞንና ኮንታ ልዩ ወረዳ፣ በደቡብ ከደቡብ ኦሞ ዞንና ጋሞ ዞን፣ በምስራቅ ከዳውሮ ዞንና ጋሞ ዞን፣ በምዕራብ ከደቡብ ኦሞ ዞንና ባስኬቶ ልዩ ወረዳ ጋር ይዋሰናል፡፡ የዞኑ ዋና ከተማ ሣውላ ሲሆን ከአዲስ አበባ በ526 ኪሎ ሜትር፣ ከክልሉ ርዕሰ ከተማ አዋሣ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ አጠቃላይ የህዝብ ብዛትም 915,621 ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 732,715 ህዝብ በገጠር የሚኖርና 80 % የሚሆነው በእርሻ ሥራ የሚተዳደር ነው፡፡ ቀሪው የህብረተሰብ ክፍል በንግድ ሥራና በአነስተኛና ጥቃቅን የሥራ ዘርፎች ተደራጅቶ የሚሠራ ነው፡፡ በዞኑ ሁለት ብሔረሰቦች ያሉ ሲሆን ጎፋና ኦይዳ ናቸው፡፡ የዞኑ የአየር ንብረት በሶስት የተከፈለ ሲሆን ደጋ 20.92%፣ ወይና ደጋ 31.12%፣ ቆላ 47.96% ነው፡፡ የመሬት አቀማመጡም ሜዳማ፣ወጣ ገባና ሰንሰለታማ ተራሮችን ያቀፈ ነው፡፡ የዞኑ አየር ንብረትና የመሬት አቀማመጥ በጣም ማራኪና ለእርሻ ሥራ፣ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚና ለኑሮ ምቹ የሆነ ነው፡፡ የዞኑ የመሬት አቀማመጥ ከባህር ጠለል በላይ በአማካይ1976 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን በዞኑ በከፍታቸው የታወቁ በመሎ ኮዛ ወረዳ 3439 ሜትር ከፍታ ያለው የዳሞታ ተራራ እና የዑ/ደ/ፀሐይ ወረዳ 3421 ሜትር ከፍታ ያለው የአገርማሶ ዲዚ ተራራ ናቸው፡፡ የዞኑ አማካይ ዓመታዊ የዝናብ መጠን 170.5 ሚ.ሜትር ነው፡፡ የዞኑ ፓለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ገፅታን በተመለከተ የጎፋ ዞን ምቹና አሳታፊ የፖለቲካ አደረጃጀት ያለበት ዞን ሲሆን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ልዩ ትኩረት የተሰጠበትና ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በእኩል እየተስተናገዱ ያሉበት ዞን ነው፡፡ የጎፋ ዞን ለአስተዳደራዊ አመቺነት በ7 ወረዳዎችና በ2 ከተማ አስተዳደሮች በ196 የገጠርና ከተማ ቀበሌዎች የተከፋፈለ ነው፡፡ በዞኑ ያልተማከለ አስተዳደር ሥርዓት ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን ህዝቡም ከቀበሌ እስከ ፌደራል ባሉ መንግስታዊ የአስተዳደር እርከኖች በተወካዮቹና በቀጥታ በውሳኔ ሰጪነት እየተሳተፉ ይገኛል፡፡በዞኑ በመንግስት ሥራ ላይ የተሠማራ የሰው ኃይልብዛት ወንድ 7171 ሴት 3487 ድምር 10658 ነው፡፡ የዞኑ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን በተመለከተ የዞኑ አጠቃላይ ማክሮ ኢኮኖሚ በእርሻ ሥራ፣ጥቃቅንና አነስተኛ የማምረቻ ዘርፍና በንግድ ሥራ ገቢ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ከአጠቃላይ የመሬት መጠን በእርሻ ሥራ የለማ መሬት 245,000 ሄክታር 53.83 %፣ የሚለማ መሬት 26,893.5 ሄክታር 5.91 %፣ለግጦሽ የዋለ መሬት 35,844 ሄክታር 7.88%፣በውሃ የተሸፈነ መሬት 1,536 ሄክታር 3.38%፣በደን የተሸፈነ መሬት 104,071 ሄክታር 22.87%፣ በሌሎች የተሸፈነ መሬት መጠን 23,218.5 ሄክታር 5.10% ነው፡፡ በዞኑ የአርሶ አደሩን የመሬት ባለቤትነት መብት ለማረጋገጥ በተካሄደ የመሬት ልኬት መሠረት104,862 አርሶ አደሮች የመሬት ማረጋገጫ ደብተር ተሰጥቷቸዋል፡፡ ዞኑ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚ ምቹ የአየር ንብረትና መሬት ያለው ሲሆን በዞኑ 6210 ሄክታር መሬት ለኢንቨስትመንት ሥራ ተዘጋጅቶ ይገኛል፡፡ የቱሪስት መስዕብን በተመለከተ የዞኑ ህዝብ ቱባ ባህላዊ ቅርሳቅርሶችና ድንቅ ዋሻዎችና ብርቅዬ አራዊት ያሉበት የማዜ ብሔራዊ ፓርክ በከፊል እና ሌሎች ተፈጥሮአዊ የመስዕብ ቦታዎች የሚገኙበት ዞን ነው፡፡ የእርሻ ሥራ በዋነኛነት የሚካሄደው በዝናብና በአነስተኛ የመስኖ ሥራ ሲሆን በዞኑ አጠቃላይ 36 ዘመናዊ የመስኖ አውታሮች ያሉ ሲሆን በአነስተኛ መስኖ የለማ መሬት 1,093.63 ሄክታር ነው፡፡ ይህም በእርሻ ሥራ ከለማው መሬት 0.45%ነው፡፡ የዞኑ ዋና ዋና ምርት የሰብል፣ ቅመማቅመም ፣ፍራፍሬና ከብት እርባታ ነው፡፡ የሰብል ምርቶችን በተመለከተ ቦቆሎ፣ጤፍ፣ስንዴ፣ገብስ ባቄላ፣አተር ቦሎቄ ሲሆኑ፤ የቡናና የቅመማቅመም ምርቶች ቡና፣ ኮረሪማና ዝንጅብል ናቸው፡፡ የቅባት እህሎች ሰሊጥና ኦቾሎኒ ሲሆኑ ፍራፍሬን በተመለከተ ሙዝ፣ማንጎ አቮካዶ፣ብርቱካን ሎሚ ይመረታል፤ ከሥራ ስር ምርቶች ነጭና ቀይ ሽንኩርት፣ ካሳቫ ይመረታል፡፡ ቡናና ሰሊጥ ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ሲሆኑ ቦቆሎ፣ጤፍ፣ገብስ ስንዴ፣ሙዝ ማንጎ፣ ካሳቫ በከፍተኛ ደረጃ ተመርቶ በበቂ ደረጃ ለአገር ውስጥ ገበያዎች ፍጆታ የሚቀርቡ ምርቶች ናቸው፡፡ በጎፋ ዞን የእንስሳት እርባታና ልማት በከፍተኛ ደረጃ የሚካሄድ ሲሆን የቀንድ ከብቶች ላም፣በሬ፣በግ፣ፍየል በአርሶ አደር ደረጃና በተደራጁ ማህበራት አማካይነት እርባታና የማድለብ ሥራ የሚካሄድ ሲሆን፤ የደለቡ ከብቶች በሬ፣በግ፣ፍየል በከፍተኛ ደረጃ ለአገር ውስጥና ለውጪ ገበያም ጭምር በጥራትና በብዛት በመቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሠረት መንግስት የአቅርቦት አቅምን ለማሳደግ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ የቀንድ ከብት ፍየሎችና በጎች፣ የጋማ ከብት መገበያያ ማዕከል በሳውላ ከተማ በ10,794 ካሬ ሜትር ላይ ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ የማህበራዊ አገልግሎትን በተመለከተ በዞኑ የጤና ሽፋንን ለማሳደግ 2 ሆስፒታሎች፣ 24 ጤና ጣቢያዎች እና 169 ጤና ኬላዎች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፤ የትምህርት ሽፋንን በተመለከተ 348 ቅድመ መደበኛ ት/ቤቶች፣ 290 ሙሉ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ 29 ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ 3 የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣አንድ የግል ኮሌጅና 15 የግል የርቀት ማስተባበሪያና የአርባምንጭ ዩንቨርስቲ ሳውላ ካምፓስ በዞኑ የትምህርትና ስልጠና ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የመንገድ ልማትና አገልግሎትን በተመለከተ በቀበሌ ተደራሽ መንገድ ሥራ ፕሮግራምና በህዝብ ተሳትፎ ቀበሌ ከቀበሌ እና ቀበሌን ከወረዳ ጋር የሚያገናኙ የጠጠር መንገዶች ግንባታና ሽፋንን በተመለከተ 394.74 ኪሎ ሜትር የበጋ የጠጠር መንገድ የተገነባ ሲሆን ይህም ከዞኑ የቀበሌያት ብዛትና አቀማመጥ አንፃር ሲታይ በጣም አነስተኛ ሽፋን ነው፡፡ የዞኑን ዋና ከተማ ከአርባምንጭ ጋር የሚያገናኝ 151 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ተገንብቶ አገልግሎት በመሥጠት ላይ ይገኛል፡፡ ከሶዶ ሣውላ በፌደራል መንግስት 136 ኪሎ ሜትር ደረጃውን የጠበቀ የአስፓልት መንገድ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ከሣውላ እስከ መሎ ኮዛ 96 ኪ.ሜትር አስፓልት መንገድ ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይይገኛል፡፡ ከሣውላ ሸፊቴ 9 ኪሎ ሜትር መንገድ በፌደራል መንግስት በመገንባት ላይ ያለ ሲሆን ሣውላን ከደቡብ ኦሞ ዞን ርዕሰ ከተማ ጂንካ ጋር የሚያገናኝ የጠጠር መንገድ ያለ ሲሆን በዞኑ ርዕሰ ከተማ ሣውላ 2.7 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድና በሳውላና በቡልቂ ከተሞች 8.63 ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ኮብል ስቶንና 26ኪሎሜትር የጎርፍ ማስወገጃ ቦይ ተገንብቶ አገልግሎት በመሥጠት ላይ ይገኛል፡፡ የዞኑ አጠቃላይ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ከአጠቃላይ የዞኑ ህዝብ ተጠቃሚነት አንፃር ሲሰላ 26% ነው፡፡ በዞኑ የዘመናዊ ስልክ አገልግሎትና የዲጂታል ፋይቨር ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚነትን በተመለከተ በሣውላ ና በቡልቂ ከተማ አሰ/ር ቢቻ የሚገኝ ሲሆን በገጠር በውስን ቀበሌያት ገመድ አልባ ሽቦ የስልክ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል በዞኑ 6 ወረዳዎችና 2 ከተማ አስተዳደር ዋና ከተሞች የ24 ሰዓት ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች ሲሆኑ በዞኑ ውስጥ ካሉ196 የከተማና የገጠር ቀበሊያት ውስጥ43 ቀበሌያት የመብራት አግልግሎት ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ይህም ሽፋን 21.94% ነው፡፡ በዞኑ ዋና ከተማ ሣውላ ዘመናዊ የመንገድ ላይ መብራት በመዘርጋት ላይ ይገኛል፡፡




jsCalendar


Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved
Gofa,Ethiopia