የኦይዳ ብሔረሰብ አለባበስ
ቀን 2021-09-03
የአንድ ማሕበረሰብ አለባበስና አጋጌጥ ከዕድሜ ፣ ከፆታና ማሕበራዊ ኑሮ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው ፡፡ የአለባበሳቸውን ሁኔታ ማጤን ስለ ግሰቦቹ ዕድሜ እና በማሕበረሰቡ ዉስጥ ስላላቸው ተቀባይነት ለማወቅ ያስችላል ፡፡ በወንዶች እና በሴቶች መካከል ጎላ ያሉ የአለባበስና የአጋጌጥ ልዩነቶች ያሉት ሲሆን በተመሳሳይ መልክ በፆታዎች መካከል እና በዕድሜ ደረጃቸው የአለባበስ እና የአጋጌጥ ሁኔታቸው ልዩነቶች ይኖራሉ ፡፡ ከዚህ ባሻገር የጀግንነት ተግባር የፈፀሙ ግለሰቦች እና በማሕበረሰቡ ዉስጥ የተለያየ ኃላፊነት እና ማዕረግ ያላቸው ግለሰቦች የተለየ የአለባበስ እና የአጋጌጥ ሥርዓት አላቸው ፡፡ አለባበስና አጋጌጥ የሀብትና የድሎት ደረጃ ማሳያም ተደርጎ ይታያል፡፡ በመሠረቱ ታሪክ እንደሚዘክረው ሰዎች በመጀመሪያዎች ዘመናት ራቁታቸውን እንደሚንቀሳቀሱ እና በሂደት ቀስ በቀስ ቅጠል፣ የዛፍ ልጣጭ፣ ቆዳ እና በባሕላዊ መንገድ በሽመና የተሰሩ ልብሶችን እየተጠቀሙ አሁን ወደ ደረስንበት የአለባበስ ሁኔታ ላይ ተደርሷል ፡፡ በአለባበስ ረገድ የጥጥ ድርሻ ከመጀመሩ በፊት የኦይዳ ማሕበረሰብ ከቤት እንስሳት እና ከአደን የተገኙ ቆዳ እና የቆዳ ዉጤት አልባሳት ለገበናቸው መሸፈኛ እና ለመኝታ አገልግሎት በማዋል ይጠቀሙ ነበረ፡፡ ስለሆነም በአካባቢው የሚሰራ ልብስ ከእንሰት ቅጠል፣ ከጥጥ ፈትል እና ከእንስሳት ቆዳ ልብሳቸውን አዘጋጅተው እንደሚለብሱ ቀደምት አባቶች ያስረዳሉ ፡፡ ልብሶቹ ጶኔ (dhoone) እና ሞኦ (moo7o) ከጥጃና ከፍየል ቆዳ የሚዘጋጁ ሲሆን የሴቶች አልባሳት ከቆዳ እና ጨሌ የሚዘጋጅ ማንቾ (manchcho) ፣ ከእንሰት ቅጠል (dasa) ከላይ የሚለብሱት ሾዳ /Shoda/ የሚያጠቡ እናቶች እንደ ጡት መያዥያነት የሚጠቀሙበትን ይሠራሉ፡፡ በሂደት ከጥጥ የሚዘጋጅ ወንዶች ከወገብ በታች የሚያገለድሙት ፋታላ ፣ አሸርጠው የሚለብሱት ፣ ጹቡቆ /xubbuqo/ በብዛት ከዝናብ ለመከላከል የበግ እና የፍየል ለምድ መልበስ የተለመደ ነው፡፡ ዳባላ ዳንጮ ረጅም መታጠቂያ መቀነት ጀግኖች እና ትላልቅ ሰዎች በልቅሶ ቦታ የሚለብሱት የነብር ቆዳ (Worba moo7o) ወንዶች በጀርባቸው ላይ የሚለብሱት ሆኖ ጉቼ (Guchche) ወንዶች በጭንቅላታቸው ላይ አስረው የሚቀስሩት እና በእጅ የሚይዙት ጋሻ (gonddale) እና ጦር /toora/ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በጦርነት ጊዜም ዳባላ ዳንጮ (ረጅም መታጠቂያ መቀነት)፣ ጋሻ (gonddale) እና ጦር /toora ይጠቀማሉ፡፡
ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት በኦይዳ ብሔረሰብ
ቀን 2021-09-03
ግጭት በሰዎች መካከል የሚከሰት ዘርፈ ብዙ የእምነትና የሕይወት ኡደት የሚፈጥራቸው ልዩነቶች በፖለትካ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ዘርፍ በተዘረጉ ጉዳዮችና ግቦች ላይ ለመድረስ የሚፈጠር ልዩነት ነው፡፡ በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ማህበራዊ እንቅስቃሴ ዉስጥ በግለሰቦችና በቡድኖች መካከል የሚነሱ ሃሳብም ሆነ የአስተሳሰብ ልዩነት የተነሳ ግጭቶች የሚፈጠር መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ ሰዎች በአንዳንድ አከባቢ አብረው በሚኖሩበት ጊዜ በተለያዩ አጋጣሚዎች ማህበራዊ ግንኙነቶችን ይፈጠራሉ፡፡ ለምሳሌ በንግድ ልዉዉጥ ፣ በጋብቻ መተሳሰር በለቅሶ፣ በሠርግ … ወዘተ ስሆን ሆኖም ግን አልፎ አልፎ በእነዚህ ማህበራዊ ግንኙነቶች ዉስጥ አለመግባባቶችና ግጭቶች ሊከሰቱ ይቻላሉ፡፡ የብሔረሰቡ ህዝቦች እርስ በርሳቸዉም ሆነ ከሌሎች አጉራባች ብሔረሰቦች ጋር ማህበራዊ ግንኙነት ያላቸው ብሆንም አንዳንደ በመካከላቸው ግጭቶች ይከሰታሉ፡፡ ይሁን እንጂ ባህላዊ አስተዳደርና ዳኝነት ሥርዓት የማህበረሰቡን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለትካዊ እንዲሁም የማህበረሰቡ አባላት የዕለት ኑሮ የተረጋጋ እና ሠላማዊ እንዲሆን የተለያዩ ኃላፊነቶች አሉት፡፡ ከእነዚህ ኃላፊነቶች አንዱ በማህበረሰቡ አባላት መካከል የሚፈጠሩ በግልና በቡድን የሚነሱ ግጭቶችን በዘለቄታ መፍታት ነው፡፡ በኦይዳ ብሔረሰብ የግጭት መንስኤዎች ተብለው በዋናነት የሚጠቀሱት ድንበር መተላለፍ ፣ የሴት ልጅ ጠለፋ፣ በግጦሽ መሬት ፣ ነፍስ መግደል፣ እና በሌሎችም ወጣቶች መካከል የሚፈጠሩ የሃሳብ አለመግባባት የግጭት መንስኤ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ መሠረት ኦይዳ ብሔረሰብ ከጥንት ጀምሮ ባህላዊ አስተዳደር ሥርዓቱ እስከ አሁን የዘለቀ ነዉ ፡፡ በማህበረሰቡ ግጭቶች እንደ ግጭት በዓይነት ተለይተው በየደረጃው ባሉ ባህላዊ አስተዳደር መሪዎች አማካኝነት በተለያዩ ደረጃ ባላሉ /Buca/ ወይም ባህላዊ የመሰብሰቢያ አደባባይ ግጭቱ ይፈታል፡፡ አለመግባባቶች በበታችኛው እርኬን ባሉ ባህላዊ በመንደር ሽማግሌዎች አማካኝነት ቡጫ /Buca/ የመሰብሰቢያ ቦታ ታይቶ እልባት የሚሰጠውና እልባት ካላገኘ በጮማች /Comachi/ እንዲዳኝ የሚደረግበት የመጀመሪያ ደረጃ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ነው፡፤ ጮማች /Comachi/ የግጭት መንስኤዉን በጥልቀት መርምረውና በማስረጃ አስደግፎ የሚሰጠው ዉሳኔ ስሆን በዚህ ያልተጠናቀቄ ጉዳይ በቢታን /Bitan/ የሚታይ ይሆናል ፡፡ የግጭቱን መነሻ እና በየደረጃው የተደረጉ ጥረቶች በዝርዝር ከፈተሸ በኋላ እልባት ይሰጣል፡፡ በሶስቱ እርከኖች በሚሰጠዉ ደሰኝነት ያልረካ ለካቲ ጉዳዩ እንድቀርብ ይደረጋል፡፡ በባልጣ ቡጫ /Buca/ ካቲ የመጨረሻው ዉሳኔ ይሰጣል ፡፡ የተሰጠውን አልቀብልም የሚል ወገን ካለ ከማኛውም ማህበራዊ ተሳትፎ ማለትም ከብት ከከብት ጋር ወይም ልጅ ከልጅ ጋር እንዳይገናኝ፣ እንድሁም እሳትና ውሃ ከጎሮበት እንዳይወስድ የሚገለል ከመሆኑ በላይ በንጉሱ ትዕዛዝ ከአካባቢው እንዲሰደድ ይደረጋል፡፡ በኦይዳ ብሔረሰብ ሰው ነፍስ ያጠፋ ግለሰብ መፀፀቱን ገልፆ ስቀርብ ካቲ ጉዳዩን መርምረው ሁለቱንም የሟችና የገዳይን ወገኖች በአንድ ላይ መሰብሰብ ገዳዩን የጦር ጫፍ አስነክሰው ባህላዊ የአምልኮና ቃሌ-መሀላ ሥርዓት በማስፈፀም በቡጫ ላይ ይቅር ተባብለው፣ ተግባብተውና ሠላም አውርደው እንዲኖሩ የሚያደርግበት ሥርዓት ነው፡፡ የባህላዊ እርቀ-ሠላም አውራረድ ሂደት በተመለከተ የሟች ቤተሰብ እና የገዳይ ቤተሰብ አንዳንድ በግ እንዲያቀርቡ ከተደረገ በኋላ ተጫማሪ አንድ በሬ ቀርበው ታርደው እና ሁለቱንም በጎች አንድ ላይ በማረድ ደማቸውን እንዲቀላቀል ይደረጋል፡፡ የሁለቱ በጎች ደማቸውን የመቀላቀል ምሳሌ በደም ተለያይተን በደም አንድ ሆነናል የሚል ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የበሬ ቆዳ ተገፎ ክብ ነገር በእንጨት ተሰርተው የሟች እና ገዳይ ቤተሰብ ተወካዮች እንዲያልፉ የሚደረግ ስሆን ይህም በኦይደኛ ቋንቋ ቡእንቴ /Bu7intte/ አደባለቀ ማለት ነው፡፡ እንደዚህ የሚያደርጉም በፊት በግጭት ምክንያት ተለያይተው የነበሩ አሁን ታርቀው አንድ ሆነዋል፣ ሠላም ተፈጥሮአል የሚለውን ለመግለጽ ነው፡፡ ከሌሎች አጎራባች ህዝቦች ጋር የሚከሰቱ አለመግባባቶች በሚፈቱበት ወቅት መጀመሪያ በኦጋዴዎችና በሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት ጉዳዩ እንዲፈታ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ በኋላ እርቀ-ሠላም የሚፈፀመው ደግሞ ሁለቱም ባህላዊ መሪዎች በጋራ በመሆን በህዝቦች መካከል በግጭት ምክንያት ተቋርጠው የነበረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ለማጠናከር ሁለቱም ወገኖች ወደሚያዋስናቸዉ ወንዝ ጋ በመገናኘት በመካከላቸው ቅም እንዳይዙ ቃሌ-መሃላ ይፈፅማሉ፡፡ በባህላዊ ሥርዓት መሠረት እርቅ ወንዝ ዳር የሚፈፀመዉ ግድያ ከሆነ በወንዙ ግራና ቀኝ በኩል ሁለቱን ወገኞች የሚወክል ትንንሽ ቤት /ዉልቼ/wulichche/ በመሥራት ለአንደኛው ወገን ወደ አከባቢው በኩል ለሌላኛው በዚያ ልክ ሆኖ ሥርዓቱ ከተፈፀመ በኃላ ቤቱን /ዉልቼ/wulichche/ ያቃጥሉታል /yijjo michchida/ እያሉ ለእስሙላ እየጮኹ ከላይ በተባለው ልክ ታርቀው ይጨርሳሉ፡፡ ከእርቅ በኋላ በመካከላቸው የተፈጠረው ቅም በዚያ ወንዝ ይሄዳል የሚል እምነት ስለነበራቸው ነው፡፡ ብሔረሰቡ ከለሌሎች አጎራባች ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ቡጫ የሚባል ባህላዊ የመሰብሰቢያ ሥፍራ ላይ በሠላማዊ መንገድ በሽማግሌ አማካኝነት እንዲፈታ የሚደረግበት ባህላዊ ሆነ የግጭት አፈታት ሥርዓት አለው፡፡ በአጠቃላይ የባህላዊ አስተዳደር መዋቅር ዉስጥ በየደረጃው የተቀመጡት ባህላዊ ተሿሚዎች ተግባርን መሠረት ያደረገውን ባህላዊ አምልኮ ሥርዓትን ነው፡፡ በብሔረሰቡ ዘንድ ባህላዊ እምነቶች ከፍተኛ ተቀባይነት ስላላቸው በግጭት አፈታቱ ላይ የጎላ ድርሻ አላቸው፡፡ በኦይዳ ብሔረሰብ እርስ በርስ ግጭቶች ሆነ ከሌሎች አጎራባች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶች ካቲ ከሌሎች ባህላዊ መሪዎች ጋር በመሆን እንደሚፈታ ያመለክታሉ፡፡ የባህላዊ እርቅ ሥርዓት የሚመራው በካቲ ስሆን በካቲ አደባባይ (ቡጫ) አብረው እርቅ የሚፈጽሙ ጮማች ፣ ብታን ፣ ጎድ እና ቡጫ ጭማ (የሀገር ሽማግሌ) ናቸው፡፡
የኦይዳ ብሔረሰብ ባሕላዊ ልብስ /Gade Ma7o/
ቀን 2021-12-01
የብሔረሰቡ ባሕላዊ አልባሳት፤ ቀለማት እና ትርጉማቸው የኦይዳ ብሔረሰብ በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ፣ በጎፋ ዞን ከሚገኙት ሁለቱ ነባር ብሔረሰቦች አንዱ ነው፡፡ ብሔረሰቡ ካላቸው እሴቶች አንዱ የአለባበስ ዘይቤ ሲሆን፤ የአልባሳቱ አዘገጃጀት በቀለማት ረገድም ሲገለፅ ጥቁር፣ ቀይ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴና ነጭ አምስት ቀለማት ካላቸው ክር የሚዘጋጅ ሆኖ እያንዳንዱ ቀለምም የራሱ የሆነ ገላጭ ትርጉም አለው • ጥቁር፡- የድንብር /ወሰን/ ምልክት ነው፡፡ • ቀይ፡- የደም /ትግል/ ምልክት ነው፡፡ • ቢጫ፡- የተስፋ ምልክት ነው፡፡ • አረንጓዴ፡- የልምላሜ /ልማት/ ምልክት ነው፡፡ • ነጭ፡- የሠላም /የጽድቅ/ ምልክት ናቸው፡፡
ያግኙን
☏046-777-1536
ተዛማጅ ሊንኮች
Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved
Gofa,Ethiopia