መዝናኛ በኦይዳ ብሔረሰብ
ቀን 2021-12-15
የ”ሶፋ” /Soofa/ ይህ ሥርዓት በኦይዳ ብሔረሰብ ከጋብቻ በኋላ ተጋቢዎች ከጫጉላ ቤት ሲወጡ ከቤተሰቦቻቸዉ እና ከሕብረተሰቡ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ለመቀላቀል እና የማሕበራዊ ዕውቅናን ለማግኘት ሲባል፤ ሁለቱም ተጋቢዎች ከጓደኞቻቸው ጋር በገበያ ስፍራ የሚፈፅሙት ባሕላዊ የመዝናኛ ሥርዓት ሲሆን፤ ከጫጉላ ቤት ቆይታቸዉ በኋላ ለሕብረተሰቡ በይፋ የሚታዩበት እና የሙሹራው ቤተሰቦችን የሀብት መጠን በሙሹሮች ተክለ-ሰውነት እና የደም ግባት የሚለካበት ስለሆነ የልጁ ቤተሰብም በተቻለ መጠን ከሕብረተሰቡ እና ከልጅቱ ቤተሰቦች ሊደርስባቸዉ ከሚችለዉ ከትችት እና ከወቀሳ ለመዳን ሲሉ ሙሹሮቹን በጫጉላ ቤት የቆይታ ጊዜያቸዉ በደንብ ይንከባከቡዋቸዋል ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሥርዓቱ የሚከበረው በገበያ ሥፍራ ሲሆን በጓደኞቻቸው ታጅበው በባሕላዊ ዘፈን በእልልታ እና በጭብጨባ ገበያውን ከዞሩ በኋላ ሥርዓቱ ወደ ሚፈፀምበት ገበያ ዳር ከሚገኝ ጥላ ሥር በመሄድ እየበሉ እና እየጠጡ ሥርዓቱን ያከብራሉ፡፡ ከዚህ ሥርዓት በኋላ ሙሹሮች እና ታዳሚዎች እርስ በእርሳቸዉ እየተመራረቁ ታጅበው እንደመጡ ታጅበው በዘፈን እና በጭፈራ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ ፡፡ በአጠቃላይ ከዚህ ሥርዓት በኋላ ሙሹሮች በማንኛውን ማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ የሚጀምሩ በመሆኑ የሶፋ /Soofa/ ሥርዓቱ በብሔረሰቡ ዘንድ ለዘመናት ሲከበር መቆየቱን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ አያ “Aya” በብሔረሰቡ አንድ ወንድ ሚስት ካገባ መጀመሪያ ሴቷ በአባቷ ጐሳ ስትጠራ እና ስትታወቅ የነበረችውን ሴት ከባሏ ጐሳ ተቀላቅላ በብሔረሰቡ ባሕል የእርሱ ናት እንድትባል የሚያደርግ የስጦታ ዓይነት ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ካልተፈፀመ ባሏ በእርሷ ቤተሰብ ዘንድ ሁሌም እንደ ባለዕዳ ስለሚቆጠር እና በሕዝቡ ዘንድ ሙሉ ሰው ስለመሆኑ ማረጋገጫ ስለማይሰጠው የአያ ሥርዓት በባል እና በሚስት ቤተሰቦች ዉስጥ ለዝምድና ማጠናከሪያነት እንደ ዓምድ ይወሰዳል፡፡ ሌላው የአያ ሥርዓት /ሥጦታ/ የሰጠ በሚሰቱ ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም ጥቃትና ጉዳት ሙሉ ኃላፊ ወይም ባለቤት በመሆን ስለእርሷ የመከራከር እና መብቷን ለማስከበር ሥልጣን የሚያስገኝለት ሲሆን በሌላ በኩል ባለቤቱም ከሞተች በራሱ የጐሳ መቃብር ላይ የመቅበር ሥልጣንም የኖረዋል፡፡ ይህ ሥርዓት ካልተፈፀመ ለሚደርስባት ጉዳት ጥብቅና የመቆም መብት የለውም፤ ብትሞትም በራሱ የጐሳ መቃብር የመቅበር ዕድል ስለማይኖረውና በሕዝብ መቃብር /ħayle Booza/ ስለምትቀበር የሞራል ኪሳራ ጭምር ስለሚያጋጥመዉ የአያ ሥርዓት ስጦታ በመስጠት የሁለቱም ጎሳ አካላት የማስተሳሰር ሥርዓት መፈፀም ለባል ግዴታ ግዴታ ነው፡፡ ላአሣ/ዣጋና/ “Laa7asa/Zhagana/” የአያ ሥነ-ሥርዓትን ከጨረሱ በኋላ በልጅቱ ቤተሰብ የሚፈፅም ሥርዓት ሲሆን በዘመናዊዉ አጠራር መልስ ወይም ሠርግ እንደሚባለው የልጅቱ ቤተሰብ የአያ ሥርዓትን የተከተለ ድግስ አዘጋጅተው ልጁ እና ልጂቱን የመመረቅ እና መልሰው የፍቅር ስጦታ የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡ በተጨማሪም የሁለቱ ተጋቢ ቤተሰቦች የሚቀላቀሉበት ፕሮግራም ነው ፡፡
የኦይዳ ብሔረሰብ የአመጋገብ ሥርዓት
ቀን 2021-12-15
የኦይዳ ብሔረሰብ የአመጋገብ ወግ በሁለት የተከፈለ ሲሆን አንደኛው በማንኛውም ሰዓት የሚመገቡት የአመጋግብ ሥርዓት ሲሆን ሁለተኛው ለበዓላት እና ለእንግዳ የሚዘጋጅ ተብሎ ይታወቃል፡፡ በማንኛውም ሰዓት ማሕበረሰቡ የሚያዘውትረው የምግብ ዓይነቶች የእንሰት ዉጤቶች እንደ አምቾ፣ ቆጮ እና ቡላ ከእህል ዘር ከጤፍ፣ ማሽላ፣ ከበቆሎ ዱቄት በቆጮ ተለውሶ የሚዘጋጁ /Dhufe/ ምግቦች ዋና ዋና ሲሆኑ በተለየ መልኩ ለመስቀል በዓል እና ልዩ ለሆኑ ለክብር እንግዶች የሚዘጋጁ ምግቦች የጤፍ ቂጣ፣ ገንፎ /Dhoqqe/ እና ከሥጋ ጋር የሚበላ የቆጮ ቂጣ ማሕበረሰቡ ትልቅ ቦታ የሚሰጥ የምግብ ዓይነቶች ናቸው ፡፡ በተጨማሪ የቅቤ ቡና ፣ ማር እና የእርጎ ወተት ለእንግዳ ይቀርባሉ፡፡ በኦይዳ የመጠጥ ዓይነቶች /Songee Daana/ የቦርዴ ጠላ ከገብስ፣ ከጤፍ፣ ከእንሰት፣ ከበቆሎና ማሽላ የሚዘጋጅ መጠጥ ሲሆን ከጤፍ ብቻ የሚዘጋጅ “ባሽንቻ ዳና” የሚባሉ ባሕላዊ መጠጦች በማሕበረሰቡ በዋናነት ይዘወተራሉ፡፡ እጅግ በጣም ልዩ ተደርጎ የሚወሰድዉ የመጠጥ ዓይነት “ማጋፃ” የሚባል ሲሆን ይህ የሚዘጋጀው የበግ ወይም የፍየል ጠቦት ደም ተጣርቶ ከቀይ ጤፍ ወይም ከአጃ ዱቄት ጋር በመለወስ ተዘጋጅቶ በነጭ ሽንኩርት፣ ዝንጅብል እና ሌሎች ቅመማቅመሞች ተቀምሞ ይቀርባል፡፡ ጥቅሙ ለስብራት መጠገኛ ፣ ለደም ለመተካት እና ሌሎች አካል ጉዳቶች ማገገሚያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ያግኙን
☏046-777-1536
ተዛማጅ ሊንኮች
Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved
Gofa,Ethiopia