ባለ 5 በሯ የጎፋ ዞን መቀመጫ ውቧ የሣውላ ከተማ !
የሣውላ ከተማ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የስያሜ አመጣጥ ታሪክ
ቀን 2022-07-14
የጎፋ ዞን መቀመጫ የሆነችው ሣውላ ከተማ ከአዲስ አበባ በ526 ኪ.ሜ፣ ከሀዋሳ 300 ኪ.ሜ፣ ከወላይታ ሶዶ 135 ኪ.ሜ፣ ከአርባምንጭ 151 ኪ.ሜ፣ ከጂንካ 99 ኪ.ሜ ፣ ከላስካ 53 ኪ.ሜ እንዲሁም ከማጂ 220 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች። ከተማዋ በሰንሰለታማ ተራሮች የተከበበችና ተዳፋታማ የመሬት አቀማመጥ ያላት ስትሆን የአካባቢው አየር ፀባይ ቆላማ፣ ደጋማ እና ወይናደጋ አግሮ ኢኮሎጂካል ዞኖች ይከፈላል። የሣውላ ከተማ ስያሜ አመጣጥን በተመለከተ የተለያዩ ምንጮችና ታሪክ አዋቂዎች የሚከተለውን ትርጉም ይሰጣሉ። የመጀመሪያው "ሣውላ" የሚለው ቃል ከሁለት ጎፍኛ ቃላቶች ማለትም "ሳአ"/Sa'a/ እና "ውላ"/Wula/ የመጣ መሆኑን የዕድሜ ባለፀጎች ይናገራሉ። በአካባቢው ቋንቋ "ሳአ" ማለት ምድር ሲሆን "ውላ" ማለት በር እንደማለት ነው። አካባቢው "ሣውላ" የሚለውን የመጠሪያ ስያሜ ያገኘበት ምክንያት ሁለት መሆኑን የተፃፉ የታሪክ ምንጮችና አባቶች ይናገራሉ። ሣውላ ከተማን ከሌሎች አጎራባች አካባቢዎች ጋር የሚያስተሳስሩ መንገዶች እንዲሁም ከአራት በላይ የመውጫና መግቢያ በር ያላት ከተማ በመሆኗ ስያሜውን ማግኘት መቻሏን የታሪክ አባቶች ያብራራሉ። ሁለተኛው ትርጓሜ ሣውላ የሚለው ቃላት "ሳአ ጉልአ"/Sa'a Gul'a/ ወይም የምድር እምብርት ከሚለው የመጣ ሲሆን ከተማዋ በተራሮች የተከበበችና ለጎፋ እና አካባቢው ማዕከል ሆና የምታገለግል ስለሆነች የመሬት እምብርት የሚለውን የመጠሪያ ስያሜ ማግኘቷን ጥቅቶች ይናገራሉ። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የታሪክ አዋቂዎች ሣውላ የሚለው ስያሜ "ሳአ" እና "ውላ" ከሚባሉ ሁለት ጎፋ ቃላቶች የተገኘ መሆኑን ይናገራሉ። የሣውላ ከተማ ምስረታ ታሪክ በአጭሩ ➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖ ሣውላ ከተማ በአጼ ኃ/ስላሴ ዘመነ መንግሥት በወቅቱ የጎፋ አውራጃ ገዥ በነበሩት በአቶ ታዬ ጎላ በ1955 ዓ.ም እንደተቆረቆች የተፃፉ የመረጃ ምንጮች ያስረዳሉ። በ1950ዎቹ ሣውላ የጎፋ አውራጃ መቀመጫ ከመሆኗ በፊት ቡልቂ የአውራጃ ማዕከል እንደነበረችና በወቅቱ የነበሩ የክፍለሀገር እና አውራጃ ገዢዎች ማዕከሉን ወደ ዛሬዋ ሣውላ ከተማ እንዲዛወር ማድረጋቸውን የዕድሜ ባለፀጎች ይናገራሉ። የአካባቢው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና አየር ፀባይ ለነዋሪዎች ምቹ መሆኑ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ መዘጋጀቱ እንዲሁም ለጎፋ እና ለሌሎች አጎራባች አካባቢዎች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች አመቺ በመሆኗ ሣውላ ከተማ የጎፋ አውራጃ ማዕከል እንድትመሠረት ምክንያቶች መሆናቸውን አባቶች ያስረዳሉ። ከ1955 ዓ.ም ጀምሮ የጎፋ አውራጃ ማዕከል የነበረችው ሣውላ ከተማ ከ60 በላይ ዓመታት የደምባ ጎፋ ወረዳ እና የሣውላ ከተማ አስተዳደር የፖለቲካና አስተዳደር ማዕከል በመሆን አገልግላለች። ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የጎፋ ሕዝብ በዞን መዋቅር የመደራጀት ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎ ከተማዋ በአሁኑ ሰዓት የጎፋ ዞን፣ የደምባ ጎፋ ወረዳ እና ሣውላ ከተማ አስተዳደር የፖለቲካ መቀመጫ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች። ሣውላ ከተማ ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የተለያዩ የሐይማኖት ተከታዮች ተቻችለው፣ ተዋደውና ተፋቅረው ያለልዩነት የሚኖሩባት፣ ህብረብሔራዊ አንድነትና ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት ጎልቶ የሚታይባት ከተማ ናት። ከአራት በላይ የመግቢያና መውጫ በር ያላት ሣውላ ከተማ መንግሥት ከሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች በተጨማሪ የአካባቢ ባለሀብቶች ከመንግሥት ጎን በመቆም መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ የከተማዋን ገጽታ ለመቀየርና ከሌሎች ካደጉ ከተሞች ተርታ ለማሰለፍ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ። በአሁኑ ሰዓት የጎፋ ዞን አስተዳደር ከ 500 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የከተማዋን ገጽታ መቀየር የሚችሉ የተለያዩ የቢሮ ሕንፃ ግንባታዎችን እያከናወነ ይገኛል። የዞኑ አስተዳደር ሕንፃ ግንባታን ጨምሮ በከተማዋ የተጀመሩ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየርም ባለፈ አካባቢው የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን የጎላ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይታመናል። ይቀጥላል ...
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው የ 2014 ዓ.ም የክረምት ወራት ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሣውላ ከተማ የአቅመ ደካማ ቤት ግንባታ በመጀ
የጎፋ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ
ቀን 2022-07-07
የክረምት ወራት ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃግብር የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ጌትነት በተገኙበት በሣውላ ከተማ በይፋ ተጀምሯል። በጎፋ ዞን የሣውላ ከተማ "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ቃል ዞናዊ የ 2014 የክረምት ወራት ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መረሃ ግብር በዛሬው ዕለት ተካሂዷል። በሣውላ ከተማ ቦትሬ ቀጠና 3 ነዋሪ የሆነችው ወ/ሮ ጉቲቺ ጉራደ የ 5 ልጆች እናት እና ባለቤቷን በሞት ያጣች ስትሆን በዛሬው ዕለት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው በተገኙበት በክረምት ወራት በጎፍቃድ አገልግሎት የቤት ግንባታ በመጀመር እና ከአመራሩ የተሰበሰበ 5580 ብር ድጋፍ ተደርጎላታል። ወ/ሮ ጉቲቺ ጉራደ በተጀመረላቸው የቤት ግንባታ የተሰማቸውን ደስታ በእንባ ሲቃ በተሞላው ንግግራቸው በመግለፅ አመስግነዋል። የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ጌትነት እንደገለፁት የቤቱን ግንባታን እንዳስጀመሩ ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለማስረከብ እንደሚመጡ ገልፀዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳደሪ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው የዲንኬ-ሣውላ-ሸፊቴ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ያለበትን ደረጃ ገምግመዋል
የጎፋ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ
ቀን 2022-05-30
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳደሪ ዶ/ር ጌትነት በጋሻውን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የዲንኬ-ሣውላ-ሸፊቴ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አፈፃፀም ተገምግሟል። በውይይቱ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ጌትነት በጋሻው ፣ የፕሮጀክቱ ኮንትራክተር እና አማካሪዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። አስተዳዳሪው በዓለም አቀፉ የስራ ተቋራጭ በቤጂንግ አርባን ኮንስትራክሽን ግሩፕ ካምፓኒ እየተሠራ የሚገኘው የዲንኬ-ሣውላ-ሸፊቴ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ያለበትን ደረጃ ከተቋራጩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ተወያይተዋል። ፕሮጀክቱ የሶዶ-ዲንኬ-ሳውላ-ሸፊቴ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ አካል ቢሆንም ከዲንኬ - ሣውላ-ሸፊቴ ያለው የመንገድ ግንባታ አፈፃፀም ከህዝቡ የመልማት ፍላጎት አንፃር ዝቅተኛ መሆኑ ተገምግሟል። 76 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው ሲሆን የዲንኬ -ሣውላ - ሸፊቴ መንገድ የመንገዱ እና የዲልድይ ዲዛይን ማሻሻያዎች እና ከፍተኛ የሆነ የሲምንቶ እጥረት ለፕሮጀክቱ መጓተት እንደምክንያትነት የተጠቀሱ ናቸው። ከሞርካ እስከ ሸፊቴ ካለው 76 ኪ.ም 32.77 ኪ.ሜ የተሠራ ሲሆን 26.954 ኪ.ሜ ከካሳ ክፊያ እና የወሰን ማስከበር ጉዳይ ጋር በተያያዘ እንዳልተሠራ ተገልጿል። ከሜላ ካምፕ ወደ ሌላ አከባቢ የተወሰዱ የግንባታ ቁሳቁሶች በአጭር ጊዜ ወደ ካምፑ እንደሚመለሱም በውይይቱ ተገልጿል። የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው በውይይቱ እንደገለጹት መንገዱ የህዝቡ የዘመናት ጥያቄ በመሆኑና ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጥቅም አንፃር አንገቢጋቢ ጉዳይ በመሆኑ የወሰን ችግር ያጋጠሙ አከባቢዎች ላይ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት በማድረግ የመንገዱን ግንባታ በፍጥነት ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል። ዋና አስተዳዳሪው አያይዘውም የሚያጋጥማቸውን የትኛውም ችግር የዞኑ መንግሥት ከጎናቸው በመቆም እንደሚፈታ በመግለፅ ጥራቱን ጠብቆ ፕሮጀክቱ እንዲጠናቀቅ አሳስበዋል። በመጨረሻም ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የመንገዱን ሥራ ማፋጠን እና የአከባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካል ሊረባረብ እንደሚገባ በውይይቱ ተገልጿል። ለበለጠ መረጃ የተሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
ያግኙን
☏046-777-1536
ተዛማጅ ሊንኮች
Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved
Gofa,Ethiopia