በጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው የተመራ ልዑክ ቡድን በገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ወይዛ ቀበሌ ላይ በኩታ ገጠም የተዘራን የስንዴ ማሳ ጎበኙ።
ዶ/ር ጌትነት በጋሻው
ቀን 2021-12-07
በዶ/ር ጌትነት በጋሻው የተመራው ልዑክ ቡድን የጎፋ ዞን ዋና አፈጉባኤ አቶ ጠንክር ጠንካን፣ የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አብረሃም ዞራ እና የዞኑ የመንግስት ረዳት ተጠሪን አቶ ፖውሎስ ፋይሌን ጨምሮ የዞንና ወረዳ አመራሮች ጋር በመሆን በገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ወይዛ ቀበሌ በ50 ሄክታር ላይ በኩታ ገጠም የተዘራ የስንዴ ማሳ ጎብኝተዋል። ከድህነት መውጣት የምንችለው ያለንን መሬት ተገቢውን ቴክኖሎጂ ተጠቅመን ለውጤታማነት መስራት ስንችል ነው ያሉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ለዚህም አመራሩ ተግባሩን አውቆ በቁርጠኝነት በመምራት ሙያተኛውን አቀናጅቶና አስተባብሮ አርሶ አደሩ ደግሞ በልማቱ ላይ በመሰማራት በቅንጅት በመስራት ሀገራችንን ከድህነት ማውጣት ይገባናል ብለዋል። ዋና አስተዳዳሪው አክለውም የሚያጋጥመውን የግብርና ምርት እጥረት ለመሸፈንም ሆነ ስንዴን በሀገር ውስጥ በማምረት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማዳን ለሌሎች ልማት ስራዎች በማዋል የሀገራችንን እድገት ለማፋጠን ትርጉም ባለው መልኩ እየተሰራ በመሆኑ አበረታች ነው ብለዋል፡፡ በምርምር ማዕከል ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ የግብርና ምርምር ውጤቶችን ለሁሉም አርሶ አደር ተደራሽ በማድረግ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንደሚገባ የገለጹ ሲሆን የኩታ ገጠም ስራው በስንዴ ብቻ ሳይገደብ በሌሎችም አዝዕርቶች በተመሳሳይ መስራት ይገባልም ብለዋል። የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ የሆኑት አቶ አብርሃም ዞራ በበኩላቸው የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ለምርታማነት የተሟላ የግብርና ቴክኖሎጂ መጠቀም ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል። ኃላፊው አክለውም ዛሬ በገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ወይዛ ቀበሌ የተጎበኛው በ50 ሄክታር ላይ የተዘራው የበጋ መስኖ የስንዴ ማሳ 3160 ኩ/ል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። የተሻለ ምርትን ለማግኘት የባለሙያን ምክረ ሃሳብ መስማትና ተግባራዊ ማደረግ የአርሶ አደሩ ድርሻ መሆኑን ኃላፊው ጠቅሰው የተጎበኘው የስንዴ ማሳ ማሳያ ነው ሲሉም ገልፀዋል። በኩታ ገጠም ቴክኖለጂ የተጀመረውን የስንዴ ማሳ እንደ ተሞክሮ በመውሰድ በዞኑ በሌሎች አዝዕርቶችም ቴክኖሎጂውን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል። በመጨረሻም የገዜ ጎፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳኒኤል ደግፌ ክልሉ የ50 ኩንታል የስንዴ ዘር እና የባለሙያ ድጋፍ በማድረጉና የዞኑ መንግስት ይህንን እድል አምሮ ለገዜ ጎፋ ወረዳ በመስጠቱና እስከዛሬ ድረስ ለተደረገልን ያልተቋረጠ ድጋፍና እገዛ በገዜ ጎፋ ወረዳ ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል። በክላስተር የማምረት ስራ ቀጣይነት እንዲኖረው በመስክ ጉብኝቱ ከተገኙ ባለድርሻ አካላት የተገኘው ግብረ መልስ የሚያበረታታ መሆኑን የገዜ ጎፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳኒኤል ደግፌ ተናግረዋል፡፡ #ታህሳስ 14/2014 ዓ.ም
ያልተነገረለት እና ያልተዘፈነለት ጠላቶችን ያቀጠቀጠ የአየር ኃይሉ የኛ ጀግና ኮሎኔል ክንፉ ሀብተወልድ ማን ናቸው????
ዶ/ር ጌትነት በጋሻው
ቀን 2021-12-05
ከጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ በና ሐሙስ ገበያ እስከ አሜሪካን ሳን ፍራንሲስኮ በወፍ በረር የጀግናውን ኮሎኔል ክንፉ ሀብተወልድ ታሪክ እናስቃኛቹህ። ታህሳስ 11/2014 ዓ.ም ሣውላ: በጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው የሚመራው አጠቃላይ የዞኑ አመራር ለቀድሞው የአየር ኃይላችን ጀግና ኮሎኔል ከንፉ ሀብተወልድ እንኳን ደህና መጣህ ደማቅ የጀግና አቀባበል አደረጉ። ኮሎኔል ክንፉ ሀብተወልድ የተወለዱት በ1948 ዓ.ም በአሁኑ የጎፋ ዞን በዛላ ወረዳ በና ሐሙስ ገበያ በሚባል አካባቢ ሲሆን ከ1ኛ-3ኛ ትምርታቸውን እዛው በተወለዱበት ቀያቸው ተከታትለዋል። በኋላም ከ4ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በተወለዱበት አካባቢ በወቅቱ ትምርት ቤት ስላልነበረ ወደ ቀድሞው ፈለገ ነዋይ ልዕልት ሮማንወርቅ ትምርት ቤት (የአሁኑ ሣውላ ቦትሬ ትምርት ቤት) በመዛወር ትምርታቸውን ተከታትለዋል። ኮሎኔል ክንፉ ሀብተወልድ በትምህርታቸው እጅግ በጣም ጎበዝ ትጉህና ታታሪ ስለነበሩ 8ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ከአውራጃው ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገባቸው የተደሰቱት አጎታቸው ፊታውራሪ አባይነህ ፊኖ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በወቅቱ አጎታቸው የፓራላማ አባል ስለነበሩ ወደ ሚኖሩበት አዲስ አበባ ከልጆቻቸው ጋር እንዲማሩ ሁኔታውን አመቻቹላቸው። በዚህን ጊዜ ነበር ለኮሎኔል ክንፉ ሀብተወልድ የስኬት መውጫ በር በአጎታቸው አማካኝነት የተከፈተላቸው። ኮሎኔል ክንፉ ሀብተወልድ የ2ኛ ደረጃ ትምርታቸውን በጥሩ ውጤት አጠናቀው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በMechanical Engineering ተከታትለው ተመርቀዋል። በመቀጠልም በቀድሞው የኢትዮጵያ የአየር ኃይል የአይሮፕላን በረራ ትምህርት ቤት ገብተው በተዋጊ አብራሪነት በመሰልጠን በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቀዋል። ኮሎኔል ክንፉ ሀብተወልድ ከ19 ዓመታቸው ጀምሮ የወጣትነት አፍላ ዕድሜያቸው በሙሉ የሀገራችንን የአየር ክልል እዳይጣስ፣ በህዝቡና በተቋማት ላይ ጉዳት እንዳይደር ከባድ ኃላፊነት ተቀብለው ሀገራቸውን በአራቱም ማዕዘናት ተዘዋውረው ለሕይወታቸው ሣይሳሱ በአውሮፕላን አብራሪነት፣ በአሰልጣኝነት እና ተዋጊነት እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን እንዲሁም የሚችሉትን ሁሉ ለሀገራቸው አበርክተዋል። ምስጋና ጀግና ለሚወልዱ ለጎፋ እናቶች ይሁንና የጎፋ አባቶች በአደዋና በማይጮ ጦርነት ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰው የሀገር አንድነትን አጽንተው አኑረውናል። ለዚህም ምስክር የሚሆን ለታሪክ ማስታወሻነት በመሀል አዲስ አበባ ጎፋ ሰፈር ስያሜ ተሰጥቶታል። በተመሳሳይ የአየር ኃይሉ ጀግና ኮሎኔል ክንፉ ሀብተወልድ ከ1960ዎቹ እስከ 1983 ዓ.ም ሀገራችን በሰሜን በኩል ከሻቢያ እና ከወያኔ ጋር ያጋጠማትን መጠነሰፋ ወረራ በመመከት እንዲሁም በምስራቅ በኩል ከሱማሊያ ሰርጎ ገብ የተቃጣባትን ወረራ በብቃት በመመከት አኩሪና ደማቅ ታሪክ የሰራ ያልተነገረለት እና ያልተዘመረለት የሀገር ባለውለታ የቁርጥ ልጅ ነው። ይህንን የሀገር ባለውለታ የአየር ኃይሉን ጀግና ጨምሮ ሌሎችንም የቀድሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላትን ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ እና ውለታ በመካድ በ1983 ዓ.ም ህወሓት ሀገሪቱን ስልጣን በአሜሪካን እርዳታ ሲቆጣጠር እዚህን የቀድሞ ባለውለታ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ያለጡረታ እና ያለደመዝ በትኖ ገሚሱን ገድሎ፣ ገሚሱን አስሮ የተቀሩትን በባዕድ ሀገር እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል። በባእድ ሀገር ከሚከራተቱ እጅግ ብዙ የሀገር ባለውለታ ጀግኖች ውስጥ ታሪኩና ዝናው ያልተነገረለት የአየር ኃይሉ ጀግና ኮሎኔል ክንፉ ሀብተወልድ አንዱ ነው። ኮሎኔሉ ምንም እንኳን ኑሮውን በስደት ከተቤተሰቡ በአሜሪካን ሳን ፍራንሲስኮ ቢያደርግም ሀገራችን በጭንቅ ጦር በተወጠረችበት በአሁኑ ወቅት የገጠማትን ውስብስ ችግር ከሚወደው ወገኑ ጋር ለመጋፈጥ በመላው አለም የሚኖሩትን ፍቃደኛ የሆኑ በቁጥር 25 የቀድሞ የሀገሪቱ ሰራዊት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በማስተባበር ባላቸው ዕውቀት (በአየር ኃይል፣ በምድር ኃይል እና በባህር ኃይል) ለመገዝና ለመደገፍ ቡድኑን መርቶ ወደ አገር ውስጥ የገባ ሲሆን ይዘውት የመጡትን $40,000 (አርባ ሺህ የአሜሪካን ዶላር) እና በአንድ አይሮፕላን ሙሉ የተጫኑ ግምታቸው በሚልዮን የሚቆጠር ብር የሚያወጣ የተለያዩ መዳኒቶችን በማምጣት ለሀገር መከላከያ ሚኒስተር አስረክበዋል። ህውሓት ውለታቸውን እና ድካማቸውን ዘንግቶ በክፉ ጊዜ ከሀገር እንዲሰደዱ ቢያደርጋቸውም እነሱ ቂም ሳይዙ እውነተኛ የሀገር ፍቅር ወኔ ስላስገደዳቸው ሀገራችን የገጠማትን ውስብስብ ችግር በመገንዘብ አቅማቸው የፈቀደውን ለማድረግ በስደት የሚኖሩበትን ቅንጡ ህይወት እና ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ሀገራቸውን ለማገዝና ለመደገፍ መተዋልና ምስጋና ይገባቸዋል። በመሆኑም ይህንን የሀገር ባለውለታ ለማመስገን በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው የሚመራው አጠቃላይ የዞኑ አመራሮች እና የኮሎኔል ከንፉ ሀብተወልድ ወዳጅ ዘመድ በተገኙበት የስጦታ፣ የዕውቅና እና የምስጋና ሥነስርዓት ተካሄዳል። #ታህሳስ 11/2014 ዓ.ም
በጎፋ ዞን ደምባ ጎፋ ወረዳ ወይዴ ዳርግንሳ ቀበሌ ከ120 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተገነባ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ።
አቶ አብራሃም ዞራ
ቀን 2021-12-12
በጎፋ ዞን ደምባ ጎፋ ወረዳ ወይዴ ዳርግንሳ ቀበሌ ከ120 ሺህ ብር በላይ ወጪ በክርስቲያናዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም CVM ፕሮጀክት የተገነባ የንጹህ መጠጥ ውሃ የዞን እና የወረዳ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተመርቋል። የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አብራሃም ዞራ በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ በአካባቢያችን የሚስተዋሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራ ላለው ድጋፍ በራሳቸውና በዞኑ መንግሥት ስም ምስጋና አቅርበዋል። ምክትል አስተዳዳሪው አክለውም የዞኑ መንግሥት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሁሉም አካባቢዎች የሚስተዋሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግሮችን ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የደምባ ጎፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አንዳርጌ አራታ በወረዳችን ሕዝቡ ከሚያነሷቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር መሆኑን ገልጸዋል። ዋና አስተዳዳሪው አክለውም ድርጅቱ ከመንግሥት ጎን በመቆም የሕብረተሰባችን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት እያከናወነ ላለው ድጋፍ በራሳቸውና በወረዳው ሕዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል። የደምባ ጎፋ ወረዳ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አሰፋ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም በዑባ ባርኤ፣ ካርጮ ሜላ፣ ሎጤ፣ ዶጫ እና ዛንጋ ቀበሌያት ህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። የፕሮጀክቱ የህብረተሰብ ተሳትፎ አስተባባሪ አቶ ትንሳኤ አለማየሁ በበኩላቸው በደምባ ጎፋ ወረዳ በወይዴ ዳርግንሳ ቀበሌ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ከ120 ሺህ ብር በላይ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል። የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አክለውም ሕብረተሰቡ በገንዘብና በጉልበት በአጠቃላይ ከ35 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም የጠቆሙ ሲሆን ከ135 አባዎራዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። ድርጅቱ በደምባ ጎፋ፣ ገዜ ጎፋ፣ ባስከቶ ልዩ ወረዳ እና በሰሜን አሪ ወረዳ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል። አስተያየታቸውን የሰጡ የአካባቢ ነዋሪዎች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር መኖሩን በመግለጽ፣ አሁን የተሰራው የንጹህ መጠጥ ውሃ በቀበሌ የሚታየውን የአቅርቦት ችግር እንደሚቀርፍም ተናግረዋል። በአካባቢያቸው የሚታየውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ድርጅቱ እያከናወነ ላለው ተግባር ነዋሪዎቹ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በመጨረሻም የቀበሌው ነዋሪዎች በአካባቢው የሚስተዋሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በማቅረብ ውይይት ተካሂዶ በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል። ለፕሮጀክቱ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎችና ባለድርሻ አካላት የእውቅና ሰርቲፍኬት ተሰጥቷቸዋል። #ታህሳስ 12/2014 ዓ.ም
ያግኙን
☏046-777-1536
ተዛማጅ ሊንኮች
Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved
Gofa,Ethiopia