የመሎ ኮዛ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኤርሚያስ ወሴነ ለክቡር እንግዶች የእንኳን በደህና መጣችሁ መልእክት አስተላለፉ።
የመሎ ኮዛ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉ/ጽ/ቤት
ቀን 2022-02-05
የመሎ ኮዛ ወረዳ እና የላሃ ከተማ አስተዳደር በጋራ ለሚያስተናግዱት የ2014ዓ.ም የጎፋ ዞን ልዩ ልዩ የስፖርት ሻምፒዮን ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ወደ ወረዳችን እንግዶቻችን እየገቡ ሲሆን አስተዳዳሪውም እንኳን ወደ እናታችሁ ጓዳ በሠላም መጣችሁ ሲሉ በፍቅር ተቀብለዋል። እንግዶቻችን እንኳን በደህና መጣችሁ.......! ስለመጣችሁ በጣም ደስ ብሎናል.....! ዋና አስተዳዳሪው በመልዕክታቸው የመሎ ኮዛ ወረዳ እና የላሃ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት መሪዎች፣ ወንዶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ ተማሪዎች፣ ነጋዴዎች፣ ምግብ ቤቶች፣ ሱቆች፣ አልጋ ቤቶችና የመዝናኛ ቤቶች የሚመጡ እንግዶችን እንደ ከዚህ ቀደሙ በፍቅር እንድትቀበሉና እንድታስተናግዱ ጥሪውን አቅርቧል። አስተዳዳሪው አክለው ባስተላለፉት መልእክት የወረዳችን ነዋሪዎች ይህንን መልካም ዕድል በሚገባ በመጠቀም አካባቢያችንን ማስተዋወቅ ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል። ሁሉም ሰው ለጸጥታው ስራ ልዩ ትኩረት በመስጠት መስራት እንዳለበት የተናገሩ ሲሆን የሚካሄዱ ውድድሮች ላይ የምትሳተፉ እና የወረዳችን ነዋሪዎች ድጋፋችሁ በስፖርታዊ ጨዋነት የተሞላ እንዲሆን በአጽንኦት አስተዳዳሪው ተናግሯል። የበልጣ፣ የማይዘሎ እና የታታ ቀበሌ ነዋሪዎች እስከዛሬ ድረስ በእንግዳ አቀባበል እየከፈላችሁ ላላችሁት ከፍተኛ መስዋዕትነት አስተዳዳሪው ልባዊ ምስጋናውን ያቀረበ ሲሆን በቀጣይ ቀናትም የሚመጡ እንግዶችን በፍቅር ተቀብላችሁ እንድትሸኙ አስተዳዳሪው ጥሪውን አቅርቧል።
አፍርካ በብርቱ ፈተናዎች መካከል የፀናች፤ በተስፋ የተሞላች አህጉር ናት!!! ለአፍርካ ህዳሴ፤ ህብረትና አንድነት!! Proud to be African!!!!
አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በፌዴራል ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ
ቀን 2022-02-05
የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት እንደሚያረጋግጡት፣ እስከ 14ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ አፍሪካውያን በአመዛኙ የተረጋጋ ማህበራዊ ህይወት የሚመሩ፣ የራሳቸው ነባር የአስተዳደር ሥርዓት ያላቸው ፣በሁሉም መስክ በወቅቱ ከተቀረው ዓለም ጋር የሚያስተካክል ካልሆነም የተሻለ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገቶች ባለቤት ሆና የቆየች አህጉር ነበረች፡፡ አውሮፓውያን የአፍሪካን ምድር ከመርገጣቸው ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት አፍሪካውያን የገናና ሥልጣኔ ባለቤቶች እና የጠበቀ የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነትና ትሥሥር ያላቸው ህዝቦች እንደሆኑ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ የአክሱም /ኢትዮጵያ/፣ ኑቢያ፣ ካርቴጅ፣ ግብፅ፣ ሥልጣኔዎችን ያስተናገደች አህጉር ናት፡፡ የቅድመ ታሪኳን የፑንት ምድርን ጨምሮ የተደራጀ የአስተዳደር ሥርዓት /የኮንጐ፣ ዙምባቡዌ፣ ቤኒን ሥርወ-መንግስት፣ የጋና ኢምፓየር፣ የኢትዮጵያ ኢምፓየር፣ አሻንቲ ኢምፓየር፣ ሾንግሃይ ኢምፓየርን/ የመሳሰሉት ግዛቶችን የመሰረቱ ህዝቦች መገኛ አህጉር ናት፡፡ አፍሪካ በተፈጥሮ ሀብትም የታደለች አህጉር ናት፡፡ በዓለም ላይ እጅግ ውድ ናቸው ተብሎ የሚታመኑ ማዕድናት ሁሉ ቅርጫት ናት፡፡ አፍሪካውያን ዛሬ በሚገኙበት ደረጃ ላይ እንደሆኑ ብዙ ምክንያቶች /ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች/ ቢኖሩም ለዛሬው ግን ውጫዊ ምክንያቶች ላይ አተኩራልለው። የውጭ ጣልቃ ገብነት ለአፍሪካ መቆርቆዝ ትልቅ ድርሻ አለውና። የአፍረካውያን መከራ ዘመን አሃዱ ብሎ የሚጀመረው ከሞላ ጐደል ከባሪያ ፍንገላ ዘመን አንስቶ ነው፡፡ ከ15ኛው እስከ 19ኛው ክ/ዘመን ድረስ ከ400 ዓመታት ላላነሰ ጊዜ የቆየው የባሪያ ንግድ የአፍረካ ውድቀት መጀመሪያ ነበር፡፡ በወቅቱ /Trans – Atlantic slave trade Root/ ተብሎ በሚታወቀው የባርያ ንግድ መሥመር ከ30 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን ወደ ደቡብ አሜሪካ፣ ሰሜን አሜሪካና ምዕራብ አውሮፓ እንደተጓጓዙ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ ዛሬ ላይ ምዕራባውያን ለደረሱበት ብልፅግና አንዱ መሠረት የጥቁር ህዝቦች ደም፣ ላብና ጉልበት እንደሆነ ብዙ ምሁራን ይስማሙበታል፡፡ በተቀራኒው ግን የባሪያ ፍንገላን ተከትሎ አፍሪካ አምራች ዜጐችን አጥታለች፣ የፀጥታ /Security/ መዋቅሯ ተንኮታኩቷል፣ ከሁሉ በላይ ከሰው በታች ሆነዋል፣ የሞራል ውድቀትም ደርሶባቸዋል፡፡ ሌላው አፍሪካን ከጥቅም ውጭ ያደረገው ታሪካዊ ክስተት የቅኝ አገዛዝ ዘመን ነው፡፡ ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ ምዕራባውያን የባሪያ ንግድ እንዲቆም ወሰኑ፡፡ በጣም የሚገርመው ግን የባሪያ ንግድ ሰብዓዊ መብትን የሚነካ ስለመሆኑ “በሰብዓዊነት ወይም /Human Right/ ስም መሆኑ ላይ ነው፡፡ ሀቁ ግን በብዙ ሰው ጉልበት የሚከናወነው የጉልበት ሥራ ማሽን ስለተካው ነው፡፡ /በነገራችን ላይ ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የአፍሪካዊያን ባህልና የአኗኗር ዘይቤ ከአውሮፓውያን ይልቅ ለሰባዊነት የቀረበ ነው(እመለስበታለሁ)። ዛሬ ላይ ግን ስለ ሠብዓዊነት ምዕራባውያን አፍሪካውያንን ማስተማር /Leacture/ ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ነገሩ ጉልበት ያለው ሁለም ልክ ነኝ ይል የለ፡፡ በአፍሪካ እሰከ ዛሬ ድረስም የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ እጆች አፍሪካን ማተራመስ አላቆሙም፡፡ በሰብዓዊ መብት ሥም፣ በብድርና ዕርዳታ ሰበብ፣ በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ሥም በአፍሪካውያን ውስጠ ጉዳይ ጣልቃ ይገባሉ፡፡ ምዕራባውያን ከባሪያ ፍንገላ ዘመን ጀምሮ በተደጋጋሚ ወደ አፍሪካ የሚዘምቱበትን ምክንያቶችን ለማብራራት ይሞክራሉ፡፡ ሊያሰለጥኑን፣ ስለዴሞክራሲ ሊያስተምሩን፣ ሰው ሊያደርጉን እንደሆነ ብዙ ይባላል፡፡ የፈጠራ ትርክቶችን /The Myth of African /Black inferiority/ በመቅረፅ አፍሪካውያንን እሰለጥናለን የሚል የሞራል መከራከሪያ አንግበው ነበር የቀረቡት፡፡ ይህ አመለካከታቸው በጣም በተደራጀ መንገድ እንዲሰርፅ ተደርጓል፡፡ በአፍሪካ ተግባራዊ የተደረጉ የትምህርት ፖሊሲዎች፣ ትውልዱ የተቀረፀበትም በዚሁ አቅጣጫ ነው፡፡ ብዙ አፍሪካውያን የመልካም ነገር ሁሉ መነሻው ምዕራባውያን ናቸው ብለው እንዲያስቡ አድርጓል(Mental colonization)። በሌሎች ሥራዎች በጣም የሚናደንቃቸው ታዋቂ ፈላስፋዎች ጭምር በዚህ ሀሳብ ላይ በተዛባ መንገድ እንድጽፍ ሆኗል ፡፡ በ17ኛው ክ/ዘመን የምዕራባውያንን ዕሳቤዎች በመቅረፅ ረገድ ጉልህ ድርሻ የነበራቸው እነ /John Lock, David Human, Immanuel Kant, Hegel/ ጥቁር ቆዳ ቀለም ያላቸው በነጮች መሠልጠን እንዳለባቸው ያመላከቱበት መንገድ ሲታይ ነገሩ ምንኛ ሥር የሠደደና ከባድ እንደሆነ ያሳያል፡፡ የአፍሪካ ክብር መልሶ ማምጣት ግን አሁንም በራሳችን በአፍሪካውያን እጅ ነው ያለው። ከቅኝ ግዛት ነፃ ለመውጣት ተግባር ላይ የዋለው የፓን አፍሪካኒዝም አዩድዮሎጂ በተሟላ መንገድ ተግባራዊ መደረግ አለበት፡፡ አፍሪካውያን የራሳችን ባህል፣ እሴት፣ ልምምድ ከዛሬው ሁኔታ ጋር ካጣጣምን በዓለም መደረክ ጎልተን የማንወጣበት ምክንያት አይኖርም። በዓለም ላይ ከቻይና ቀጥሎ በህዝብ ቁጥር ሁለተኛ ነን፡፡ 1.3 ቢሊዮን ህዝብ /ያውም እጅግ አብዛኛው ወጣት/ አንድ ላይ ከቆምን፣ አንድ ላይ ማጨብጨብ ከቻልን ድምፃችን ከፍ ብሎ መሰማቱ አይቀሬ ነው፡፡ የእርስ በርስ የንግድ ትስስር ማጠናከር ከቻልን አፍርካ ብቻውን ትልቅ ገበያ ነው፡፡አፍርካ አሁንም ትልቅ ተስፋ ያላት አህጉር ናት። ለአፍሪካ ህብረትና አንድነት ኢትዮጵያ የተለየ ታሪካዊ ኃላፊነት አለባት። የዐድዋ ድልን ተከትሎ መላው አፍሪካዊያን ነፃ እንዲወጡ የሥነልቦና ከፍታ ከመሆናችን በላይ በኢትዮጵያ መሪ በአፄ ኃ/ሥላሤ ጉልህ ሚና የዛሬ 59 ዓመት OAU አዲስ አበባ ላይ ተመስርቷል። ዛሬ አዲስአበባ የአፍሪካዊያን የፖለቲካ፣ የነፃነትና የዲፕሎማሲ ማዕከል ናት። ኢትዮጵያውያን ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር፣ ውስጣዊ ጥንካሬያችንን ከፍ ማድረግ ከቻልን ለአፍሪካውያን ተስፋ መሆን እንችላለን፡፡በአዲስ መንፈስ የአፍሪካ ህብረት እንዲሳካ ከፍተኛ ደርሻ መጫወት እንችላለን። በዚያውም አፍርካ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጎልቶ እንዲወጣ ኢትዮጵያ ሌላ የተለየ አስተዋፆ የማበርከት ዕድል አለ። በነገራችን ላይ የዘድሮን የህብረቱን ስብሰባ ማሳካት ትርጉሙ ብዙ ስለሆነ የተለየ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል። ቀጥሎ የፓን አፍሪካኒዝም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማጠናከር ፣አፍርካ በUN ፀጥታው ም/ቤት ቋሚ ውክልና እንድታገኝ ከሌሎች አፍሪካዊያን ጋር አብሮ መሥራት የነገ የቤት ሥራ ነው።
የጎፋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት በሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ዙሪያ የሴቶች ንቅናቄ መድረክ ተካሄደ
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ
ቀን 2022-01-26
ሣውላ፣ ጥር 18/2014 ዓ.ም የጎፋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት በሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ዙሪያ የሴቶች ንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል። በንቅናቄው መድረክ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ የሀብት ልማት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ደመቀ፣ የዞኑ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ማሩፋ መኩሪያ እና ሌሎችም በየደረጃው የሚገኙ የሴት አመራሮችና የመንግሥት ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል። የዞኑ የሴቶች ሊግ ጽሕፈት ኃላፊ ወ/ሮ እመቤት ንጉሴ የእንኳን በደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት በሁሉም መስኮች የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የጎፋ ዞን የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ማሩፋ መኩሪያ በንቅናቄው መድረክ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎና የአመራር ሰጪነት ሚናቸውን ለማጎልበት ፓርቲው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል። አቶ ማሩፋ አክለውም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፓርቲው ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል። የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የሀብት ልማት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ደመቀ በበኩላቸው ሴቶችን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ከወንዶች ጋር እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል። ሴቶች እንደማንኛውም ዜጋ በሕገመንግስቱ የተረጋገጠላቸውን የሠላም፣ የዲሞክራሲ፣ የልማት መብቶችና ተጠቃሚነት ዙሪያ ላይ ግንዛቤያቸውን ለማሳደግ የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። ሴቶች በውሳኔ ሰጪነት በብዛት የሚሳተፉበትና የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣት ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ በሀገር ግንባታ ሂደት ንቁና የተደራጀ ተሳታፊነታቸውን ለማጎልበት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ያግኙን
☏046-777-1536
ተዛማጅ ሊንኮች
Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved
Gofa,Ethiopia