በጤናው ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገጸ
የጎፋ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ
ቀን 2022-11-06
የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ "የወባ በሽታን ማጥፋት ከእኔ ይጀምራል" በሚል መሪ ቃል የ2014 ዓ.ም እና የ2015 ዓ.ም አንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የወባ በሽታ መከላከል የንቅናቄ ጉባኤ አካሂዷል። የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ማኖቴ በመድረኩ እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት በዘርፉ የታዩ ድክመቶችን በማረምና ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ በማስቀጠል በ2015 ዓ.ም የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ጉባኤው ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል። በተያዘው በጀት ዓመት የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት ሞት ለመቀነስ መምሪው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። በአንዳንድ መዋቅሮች የተጀመሩ የጤና ተቋማት ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቅ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል። የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው የጤና ሴክተር ውጤታማ እንዲሆን የአመራሩና የባለድርሻ አካላት ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። የወረዳና ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤትና የጤና ተቋማት አፈፃፀም በመገምገም ተቋማት የተሻለ አፈፃፀም እንዲያስመዘግቡ በየጊዜው ክትትልና ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል። የጉባኤው ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሁሉም መዋቅሮች ያሉ አምቡላንሶች ለታለመለት ዓላማ ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በጤና ተቋማት ብቻ የሚሸጡ ነገር ግን በሕገወጥ መንገድ ከጤና ተቋማ ውጪ የሚገኙ መድኃኒቶችን ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ለዘርፉ ውጤታማነት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ተናግረዋል። የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ እና የወረዳና ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤቶች የጤናው ዘርፍ በ2015 ዓ.ም መሪ ዕቅድ ላይ የግብ ስምምነት ተፈራርመዋል። በመጨረሻም በ2014 በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ያስመዘገቡ የወረዳና ከተማ አስተዳደር ጤና አጠባበቅ ጣቢያዎች፣ የጤና ኬላዎች እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች የዋንጫ ተሸላሚና የእውቅናና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል። ተሸላሚ ተቋማትና የጤና ባለሙያዎች በሰጡት አስተያየት በተሰጣቸው እውቅና መደሰታቸውን ገልጸው፣ በቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም እንዲያስመዘግቡ አቅም እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የትግራይ ታጣቂዎች አዛዦች ናይሮቢ ላይ ተገናኙ
የጎፋ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ
ቀን 2022-11-06
በሰላም ስምምነቱ ውስጥ በ5 ቀን ውስጥ ወታደራዊ አመራሮች እንዲገናኙ በሚያዘው መሠረት የአዛዦቹ ውይይት ዛሬ በናይሮቢ ተጀምሯል። እስከ አሁን በስምምነቱ ሂደቱ በመልካም ሁኔታ እየሄደ ነው።
የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ "የወባ በሽታን ማጥፋት ከእኔ ይጀምራል" በሚል መሪ ቃል የወባ በሽታ መከላከል የንቅናቄ ጉባኤ እያካሄደ ነው
የጎፋ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ
ቀን 2022-11-05
የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ "የወባ በሽታን ማጥፋት ከእኔ ይጀምራል" በሚል መሪ ቃል የ2014 ዓ.ም እና የ2015 ዓ.ም አንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የወባ በሽታ መከላከል የንቅናቄ ሴክቶሪያል ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል። የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ማኖቴ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት በሕወሓት ጠንሳሽነት ተገዳ ከገባችበት ጦርነት ወደ ሠላም የመጣችበት እንዲሁም የኢፌዴሪ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ለመጀመሪያ ጊዜ በጎፋ ዞን ጉብኝት ባደረጉበት ማግስት ጉባኤ ማካሄዳችን ለየት ያደርገዋል ሲሉ ገልጸዋል። መምሪያው ሕዝባችንን በጤናው ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግና ሞዴል መዋቅሮችን ለመፍጠር እየሰራ መቆየቱን ተናግረዋል። የእናቶችና ሕፃናት ሞት ለመቀነስ፣ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ቀበሌያትን ሞዴል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት የመምሪያው ኃላፊ ከፍተኛ አፈፃፀም ያላቸውን የመጀሪያ ደረጃ ጤና ጣቢያዎችንና ሆስፒታሎችን ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። የማህበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸው ተግባራት በአንዳንድ መዋቅሮች ተስፋ ሰጪ ውጤት መመዝገብ መቻሉንም አስገንዝበዋል። የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው ባስተላለፉት መልዕክት የዞኑ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው የማህበራዊ ዘርፍ አገልግሎት መካከል የመጀመሪያው የጤና ሴክተር መሆኑን ተናግረዋል። የማህበረሰቡን ጤና ለማሻሻል የፈውስ ሕክምና አገልግሎቶችን በፍትሐዊነት ተደራሽ ከማድረግ አንፃር በተለይም የማህበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲጀመርና ቀጣይነትን ከማረጋገጥ አንፃር የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል። የወሊድ አገልግሎት ከሚጠበቀው በታች 75 በመቶ ሆኖ ይገኛል ያሉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ፣ የፕሮግራሙ ማሳኪያ የሆኑ የነፍሰ ጡር እናቶች አገልግሎት ያለመኖር፣ የእናቶች ፎረም ያለማድረግ እንዲሁም ለእናቶች ወሊድ አገልግሎት ለማሳለጥ ተብሎ የተሰጡ አምቡላንሶች ለሌላ ዓላማ ማዋል ለተግባሩ ውድቀት ዋነኛ ምክንያት ናቸው ብለዋል። በመሆኑም የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት ሞት ለመቀነስ እንዲሁም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ በመከላከል ሕብረተሰቡን በጤናው ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረጉ ቅንጅታዊ ሥራዎች ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል። በጉባኤው የዞኑ ሕዝብ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ጠንክር ጠንካን ጨምሮ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ የወረዳ ዋና አስተዳዳሪዎችና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ የጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የዘርፉ አስተባባሪዎች ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተሳትፈውበታል።
ያግኙን
☏046-777-1536
ተዛማጅ ሊንኮች
Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved
Gofa,Ethiopia