ክልሉን የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ የፀጥታ መዋቅሩን ማጠናከር እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ አሳሰቡ
Gofa Zone Government Communication Affairs Department
ቀን 2024-03-16
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በ1ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 1 ሺ 35 ዕጩ የፖሊስ መኮንኖች በወላይታ ሶዶ ከተማ አስመርቋል። በምረቃ ስነ-ስርዓቱ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ክልሉን የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ የፀጥታ መዋቅሩን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው ይህን ለማሳካት የተለያዩ የሪፎርም ስራዎች እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ ህግን በአግባቡ በማስከበር የክልሉን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ ህዝቡን ባለቤት የሚያደርግ ፣በአዕምሮው የበሰለ፣ በአካሉ የጠነከረ እና በስነ-ምግባር የታነፀ የፖሊስ ሃይል እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም የደቡብ ኢትዮጵያ ፖሊስ ለህዝብና ለህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ የቆመ፣ መሰረታዊ መብቶችንና ነፃነቶችን የሚያከብርና የሚያስከብር፣ የዜጎችን ህይወትና ንብረት ለመጠበቅ ቁርጠኛ የሆነና ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት የፀዳ የፖሊስ ኃይል መሆን እንደሚገባዉ ጠቁመዋል። ዕጩ የፖሊስ መኮንን አባላቱ ሙያው በምጠይቀው ልክ ብቁ ሆነው ቀጣይ በሚሰማሩበት ፖሊሳዊ ኃላፊነት ህብረተሰቡን በቅንነት ማገልገል እንደሚጠበቅባቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው አሳስበዋል። በመርሃ-ግብሩ ርዕሰ መስተዳድሩ የላቀ ውጤት ላመጡ ተመራቂዎች ሽልማት ሰጥተዋል።
በጎፋ ዞን ከ130 በላይ ዜጎች የሥራና ክህሎት ስልጠና እየወሰዱ ይገኛል
Gofa Zone Government Communication Affairs Department
ቀን 2024-04-16
በጎፋ ዞን በሣውላ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በመጀመሪያ ዙር ከ130 በላይ ዜጎች ለተከታታይ 21 ቀናት የሚቆይ የሥራና ክህሎት ስልጠና እየወሰዱ ይገኛል። የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ፋንታዬ ለሰልጣኞች ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት ከተለያዩ የውጭ ሀገራት ጋር የስራ ውል ስምምነት በማድረግ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ወደ የተለያዩ ውጭ ሀገራት በመሄድ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። ዋና አስተዳዳሪው በመልዕክታቸው ሀገራችን ኢትዮጵያ ካላት ትልቁ አቅም የሰው ሃይል ሲሆን፣ በአምራች የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል። አዲሱ የሥራ ውል ስምምነት በሕገ-ወጥ መንገድ የሚደረገውን የሰዎች እንቅስቃሴ በዜጎች ላይ የሚያስከትለውን እንግልት ለመከላከል የጎላ ሚና እንደሚጫወት አቶ ዳዊት ተናግረዋል። አክለውም ወጣቶች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሰማርተው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የዞኑ መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። የጎፋ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተመስገን ጌታቸው በበኩላቸው በሕጋዊ መንገድ የተሰጠንን የውጭ ሀገር የስራ ዕድል በመጠቀም ህገወጥ የሰዎችን ዝውውር እየተከላከልን ለሥራ አጥ ዜጎቻችን በሃገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሀገር ውጭም ጭምር የሥራ ዕድልን መፍጠር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል። ሰልጣኞች የሚሰጠውን ስልጠና አጠናቅቀው የሥራ ሥምሪት እስከሚሰጣቸው ድረስ መምርያቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደምያደርግና ከስልጠናው በኃላ ስለሚያስፈልጉ ጉዳዮች ፖስፖርትን ጨምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ አቶ ተመስገን አረጋግጠዋል። በመጨረሻም ሰልጣኞች በይቻላል መንፈስ ሰልጥነው ወደ ስራ እንዲሰማሩና ለነገ የተሻለ ህልም እንድሰንቁ የመምሪያው ኃላፊ መልዕክት አስተላልፈዋል። መስፈርቱን የሚያሟሉና የሥራና ክህሎት ስልጠና የወሰዱ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ወደ የተለያዩ ውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት የሚሰጣቸው ይሆናል።
ለሰላም ስምምነቱ ትግበራ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተናገሩ
የጎፋ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ
ቀን 2022-12-07
በመንግስትና ህወሓት መካከል ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ትግበራ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተናገሩ፡፡ እንዲሁም አሸባሪው የሸኔ ቡድን ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያዩ ጥቃቶችን እየፈፀመ እንደሚገኝ የገለጹት አባላቱ መንግስት ሰላማዊ አማራጭን ሲከተል ቢቆይም ሕግን ለማስከበር እንደሚገደድ ተናግረዋል፡፡ ችግሩን ዘላቂነት ባለው መንገድ ለመፍታት እንደሚሠራም አሳውቀዋል፡፡ ለአራት ቀናት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የመከረው የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ተጠናቋል፡፡ የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አቅምን በውጤት ፈተናን በስኬት በሚል መሪ መልዕክት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው ቀዳሚ አጀንዳው ካደረጋቸው ጉዳዮች መካከል የአገሪቱ ሰላም አንደኛው ነው። በተለይም ከህወሓት ጋር የተደረሰው የሰላም ስምምነት የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያመላከተ በመሆኑ ለስምምነቱ ትግበራ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አቋም መያዙን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ ተናግረዋል፡፡ የሰላም ስምምነቱ ለአገረ መንግስት ግንባታው ፋይዳው የላቀ መሆኑንም አንስተዋል። መንግስት በመላው ኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ያነሱት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ÷ አሸባሪው የሸኔ ቡድን ግን ዛሬም በእኩይ ተግባሩ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡ ቡድኑ የመላው ኢትዮጵያውያን ጠላት በመሆኑ በጋራ በመሆን መመከት እንደሚገባ እና ችግሩን በዘላቂነት መፍታት እንደሚያስፈልግ አባላቱ ተናግረዋል። እንደ ኤፍቢሲ ዘገባ መንግስት የትኛውም ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ቁርጠኛ አቋም አለው ያሉት አባላቱ፣ ከሰላማዊ መንገድ ውጪ የሚደረጉ የትኛውም አማራጮች አክሳሪ መሆናቸውን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
ያግኙን
☏046-777-1536
ተዛማጅ ሊንኮች
Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved
Gofa,Ethiopia