የጎፋ እድገትና ብልጽግና ማህበር በጎፋ ዞን ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች 200 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ
የጎፋ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ
ቀን 2022-12-01
የጎፋ እድገትና ብልጽግና ማህበር በጎፋ ዞን በተደጋጋሚ ባጋጠመው የእርጥበት እጥረት ምክንያት በሰብል መጥፋት እና ምርት መቀነስ የአስቸኳይ ድጋፍ ለተዳረጉ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለይም በዛላ ወረዳ ፣ ዑባ ደብረ-ፀሐይ ወረዳዎች ለአስቸኳይ እርዳታ የሚሆን 200,000 (ሁለት መቶ ሺህ ብር) ገቢ አድርጓል። ልማት ማህበሩ በዞኑ ስር በሚገኙ ወረዳዎች ማለትም በዛላ፣ ዑባ ደበረፀሐይ እና በከፊል በደምባ ጎፋ ወረዳዎች ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል። የጎእብማ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደግፌ ኃ/ማሪያም ይህ አስቸጋሪ ጊዜ እስከሚያልፍ ድረስ ልማት ማህበሩ ከዞኑ መንግሥትና ሕዝቡ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። በዞን ማዕከል እና በወረዳዎች ለምግብ እጥረት ለተጋለጡና አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሀብት ማሰባሰብ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል። #ተባብረን_ይህን_ክፉ_ቀን_በጋራ_እናልፈዋለን !!
በጎፋ ዞን ኦይዳ ወረዳ በታሪካዊው ጃውሻ ተራራ የዘንድሮ 17ኛው ዙር የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ
የጎፋ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ
ቀን 2022-11-29
በጎፋ ዞን ኦይዳ ወረዳ በታሪካዊው ጃውሻ ተራራ የዘንድሮ 17ኛው ዙር የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል "ሕብረብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሠላም" በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል። የኦይዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተገኝ አበበ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት የኦይዳ ብሔረሰብ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋውን በማስተዋወቅ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል የጎላ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የመሬት እምብርት ተብሎ የሚጠራው የ"ጃውሻ ተራራ"/ "ሳአ ጉልአ" ተራራ በጎፋ ዞን ኦይዳ ወረዳ ዑባ ዳማ ቀበሌ የሚገኝ ሲሆን በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ ተፈጥሯዊ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚታወቅ ታሪካዊ ሥፍራ ነው ሲሉ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ገልጸዋል። ጃወሻ ተራራን ጨምሮ በወረዳው የሚገኙ ተፈጥሯዊና ባህላዊ መስህቦች እንዲለሙ በማድረግ ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቁ የወረዳው መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። የጎፋ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ድንበሩ ድርቤ በዞኑ የሚገኙ ተፈጥሯዊ መስቦችን በማልማትና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተሰሩ ካሉ በኦይዳ ወረዳ የሚገኘው የጃውሻ ተራራ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል። የዘንድሮ ዞናዊ የማጠቃለያ የ17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ታሪካዊ በሆነው በጃውሻ እንዲከበር የተደረገበት ዋና ዓላማ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በአካባቢው የሚገኙ ተፈጥሯዊና ባህላዊ መስህቦችን ለማስተዋወቅ መሆኑን የመምሪያው ኃላፊ አስረድተዋል። የጎፋ ዞን ሕዝብ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ጠንክር ጠንካ የበዓሉ ዋና ዓላማ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የእርስ በእርስ ትስስር በማጠናከር በብዝሃነት ላይ የተመሠረተ ሕብረብሔራዊና ሀገራዊ አንድነት ሥር እንዲሰድ ለማድረግ የገቡትን ቃል ኪዳን በማደስ ለሠላም፣ ለልማትና ለዲሞክራሲ ግንባታ እንዲነሳሱ ማድረግ ነው ሲሉ ገልጸዋል። የዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች በየደረጃው በድምቀት እየተከበረ ይገኛል ብለዋል። የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል የሕዝቦችን አብሮነትና ወንድማማችነት ይበልጥ እንዲጠናከርና ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ እንዲታወቅ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን አስገንዝበዋል። በዞናችን የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች እንዲለሙ፣ እንዲታወቁና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲያበረክቱ የዞኑ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ዋና አስተዳዳሪው በመልዕክታቸው የመንገድና በየአካባቢው የሚነሱ ሌሎች የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ የሕዝባችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። በክብረ በዓሉ ላይ የጎፋ ዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የወረዳ ዋና አስተዳዳሪዎችና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የዞኑ ካቢኔ አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች፣ የባህል አምባሳደሮች፣ የመንግሥት ሠራተኞች ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
ከፌዴራል እና ከክልል አደጋ ሥጋት ተቋማት የመጡ ባለሙያዎች በጎፋ ዞን የመስክ ምልከታ በማድረግ ለዞኑ የአደጋ ስጋት ምክር ቤት አባላት ግብረ-መልስ ሰጥተዋል
የጎፋ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ
ቀን 2022-11-23
ከፌዴራልና ከክልል የተወጣጣው ቡድን በጎፋ ዞን የተወሰኑ ወረዳዎች በአየር መዛባት ለተከታታይ ዓመታት የተከሰተውን የምግብ እጥረት መነሻ በማድረግ በዛላ ፣ ዑባ-ደብረፀሃይ ፣ ደምባ ጎፋ እና መሎ ኮዛ ወረዳዎች ላይ ያደረገውን የመስክ ምልከታ ለዞኑ የአደጋ ስጋት ምክር ቤት ግብረ-መልስ ሰጥቷል። የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አብረሃም ዞራ መድረኩን የመሩ ሲሆን ከፌዴራል እና ከክልል የመጡ ባለድርሻ አካላት በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች ላይ የተከሰተውን የምግብ እጥረት የመስክ ምልከታ ግብረ-መልስ አቅርበዋል። ቡድኑ በዋናነት በጤና ፣ በንጹህ መጠጥ ዉሃ ፣በትምህርት ፣ በሴቶችና ህፃናት እና በግብርና ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የመስክ ምልከታ ማድረጋቸውን ገልፀዋል። ከዚህ በፊት የተጠናውን የዳሰሳ ጥናት መነሻ በማድረግ የመስክ ምልከታ ያደረገው ቡድን በዞኑ የተወሰኑ አከባቢዎች ከፍተኛ የምግብ እጥረት መከሰቱን በማረጋገጥ ከተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ የተራዲኦ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለህብረተሰቡ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታዎችን ለማድረስ እንደሚሠሩ ገልፀዋል። የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ በመድረኩ እንደተናገሩት ዞኑ ከተደራጀ አጭር ጊዜ መሆኑን በመግለፅ ከፍተኛ የሆነ የበጀት እጥረት ቢኖርበትም ለአጭር ጊዜ የሚሆን 1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልፀው አጠቃላይ አመራሩ ከደመዎዙ ከ 20% ጀምሮ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል ብለዋል። ምክትል አስተዳዳሪው አክለውም በዘላቂነት ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥት ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ የተራዲኦ ተቋማት የከርሰ ምድር ውሃዎችን ለማልማት የሚያስችሉ ድጋፎችን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ያግኙን
☏046-777-1536
ተዛማጅ ሊንኮች
Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved
Gofa,Ethiopia