የጎፋ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ አዋጁን ለማስፈፀምና የአከባቢውን ሠላም ለማስጠበቅ የተለያዩ ስራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ መምሪ
አቶ ብርሃኑ ጅፋሬ
ቀን 2022-01-17
ስራዎች የሚመሩት በተቋማዊ አሰራር ስርዓት፣ በፀጥታ ኮማንድ ፖስት እና ከመላው ህዝብ ጋር በሚደርግ የቅርብ ተሳትፎ መሆኑንም የሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊና የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ጅፋሬ አብራርተዋል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የተሰሩ ዋናዋና ተግባራትን በሁለት መልኩ ከፍሎ ማየት እንደሚቻል ሲገልፁ አንዱ "ህዝባዊ ሠራዊት አደረጃጀት በመፍጠር የአከባቢ ሠላምን ማስጠበቅ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአዋጁ ውስጥ የተደነጉ ጉዳዮች ላይ የህግ ማስከበር ተግባራት በመፈፀም እንደሆነ አስታውቋል። "ህዝባዊ ሠራዊት አደረጃጀት"ን ከመፍጠር አኳያ ከንዑስ ቀበሌ ጀምሮ እስከዞን ደረጃ ድረስ በዕዝ ሰንሰለት የሚመራ ሁሉንም ማህበራዊ መሠረቶችን ማለትም፦ የቀበሌ ሚሊሻ፣ ብሔራዊ ተጠባባቂ፣ የቀድሞ ሠራዊት አባላት፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ ኃይማኖት መሪዎችና ሌሎችም የተሣተፉበት ህዝባዊ ሠራዊት በድምሩ 6209 አባላት ያሉበት አደረጃጀት ተፈጥሮ በየአካባቢው ከፖሊስ ጋር በቅንጅት የስራ ስምሪት ተሰጥቷቸው የአከባቢ ሠላም ጥበቃ ስራ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። ለሠራዊት አደረጃጀቶቹ የተለያዩ የሥራ ማስጀመሪያ መድረኮች የተደረጉ ሲሆኑ አንደኛው፦ ስለአጠቃላይ አገራዊና አካባቢያዊ የፀጥታ ሁኔታ፣ ስላለንበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሁኔታ ግንዛቤ ስለመስጠት ሲሆን በሁለተኛነት በመምሪያው በተዘጋጀው የተግባር ስምሪትና ስልጠና መመሪያ ላይ ያተኮረ ተግባር-ተኮር ስልጠና ለሶስት ተከታታይ ቀናት መሠጠቱን ኃላፊው አብራርተዋል። በሌላ በኩል የአዋጁን ድንጋጌዎችንና ድንጋጌዎችን ማስፈፀሚያ መመሪያ መሠረት የቁጥጥር፣ ክትትልና ተጠያቂነት ተግባራትን መፈፀም ተችሏል። በዚህም በአሸባሪነት ከተፈረጁ ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚጠረጠሩ አካላትን ለይቶ ተጠያቂ ማድረግ፣ ሰዓት እላፊ ድንጋጌዎችን ማስተግበር፣ ባለሁለት እግር ታርጋ ያላቸውንና የሌላቸውን ሞተር መዝግቦ መያዝና ለሚመለከተው አካላት ማሳወቅ፣ ቋሚ ኬላ ፍተሻዎችንና ድንገተኛ ፍተሻዎችን ማጠናከር፣ ህገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ቁጥጥርን ማካሄድ... ወዘተ ሥራዎች እየተሠሩ የቆዩ መሆናቸውንም ኃላፊው አብራርተዋል። በመሆኑም ከህግ ማስከበር ተግባራት ባለፈ በተለይም የህዝባዊ ሠራዊት አደረጃጀቱ አከባቢዎችን ከተለያዩ ወንጀሎችና መረበሾች ሁሉ ነፃ በማድረግ ህዝቡ የተረጋጋ ሠላም እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ከህዝቡ ከተሰጠ ምስክርነትና ከሚመዘገቡ የወንጀልና የስጋት ቁጥሮችም ማረጋገጥ የተቻለ መሆኑን ገልፀዋል። እነዚህ ተግባራት ሲፈፀሙ የዞኑ አመራር በዘመቻ መልክ ስራውን በመደገፍ፤ የዞኑ ፀጥታ ኮማንድ ፖስት ዕለት በዕለት እየተገናኘ ተግባራትን እየገመገመ፣ በአካል ወርዶ ድጋፍ እያደረገ፣ በየደረጃው ባለው አፈፃፀም ላይ አስፈላጊውን እርምት እየወሰደ፣ የየአስተዳደር መዋቅሮቹም ፀጥታ ኮማንድ ፖስት በተከታታይ ስራዎችን እየገመገሙ የህዝብ ተሳትፎ እያደገ በመሄዱ መንግስታዊ ሌሎች የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች በተረጋጋ ሁኔታ እንዲመሩና ህዝቡ መደበኛ ህይወቱን በተረጋጋ ነባራዊ ሁኔታ እንዲመራ ኮማንድ ፖስቱም ሆነ አጠቃላይ ፀጥታ ሠራተኛው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ኃላፊው አክለው ገልፀዋል።
የጎፋ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ሀገርአቀፍ በጎነት ለአብሮነት የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ወጣቶች የአሸኛኘት ፕሮግራም ማካሄዱን አስታወቀ
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ
ቀን 2022-01-13
ሣውላ፣ ጥር 6/2014 ዓ.ም የጎፋ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ሀገርአቀፍ በጎነት ለአብሮነት የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ወጣቶች የአሸኛኘት ፕሮግራም ማካሄዱን አስታውቋል። በመርሃግብሩ ላይ የዞኑ ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጅፋሬ፣ የዞኑ ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ንክሰን ለማ እና የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ደቻሳ በተገኙበት ነው የአሸኛነት ፕሮግራሙ የተካሄደው። የዞኑ ሠላምና ፀጥታ መምሪያ የሰላም እሴት ግንባታ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ የሆኑት አቶ በላይ ሀብታሙ ሀገርአቀፍ 1ኛ ዙር በጎነት ለአብሮነት የወጣቶች አገልግሎት በዞኑ የተከናወኑ ተግባራት ማጠቃለያ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በቀረበው ሪፖርት ላይ ሃሳብና አስተያየት ተሰጥቶበታል። ወጣቶቹ በዞኑ በነበራቸው ቆይታ የአረጋውያንን ቤት የመጠገንና ማደስ፣ ወላጅ አጥ ሕፃናትን በመርዳትና የአረንጓዴ አሻራ ልማት ችግኝ በመትከል እንዲሁም ሌሎችንም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸው በሪፖርቱ ተገልጿል። በአጠቃላይ በዞኑ በሁሉም መዋቅሮች በወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተከናወኑ ተግባራት በገንዘብ ሲተመን ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት መሆኑንም በሪፖርቱ ተጠቁሟል። የዞኑ ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጅፋሬ በመርሃግብሩ ላይ እንደገለጹት፣ በሰላም ሚኒስቴር አማካኝነት የበጎ አድራጎት ወጣቶች በዞናችን በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል። የመምሪው ኃላፊ አክለውም ወጣቶች በዞናችን በቆዩባቸው ጊዜያቶች ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በራሳቸውና በዞኑ አስተዳደር ስም ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፣ በሄዱበት ቦታ ሁሉ ቸር እንዲገጥማቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። የዞኑ ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ንክሰን ለማ በበኩላቸው ወጣቶች በዞኑ በነበራቸው ቆይታ ከመንግሥት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት በተማሩበት የሙያ መስክ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ሕዝባችንን በማገልገል ላሳዩት የበጎ አገልግሎት ሥራዎች ምስጋና አቅርበዋል። ወጣቶቹ በበኩላቸው በዞኑ እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል ቆይታ ማድረጋቸውን በመግለጽ፣ የጎፋ እና ኦይዳ ህዝብ አቃፊና እንግዳ አክባሪ መሆኑንም ጭምር በተግባር ያየንበት ጊዜ ነበር ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የብሔራዊ የማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ፕሮግራም ላይ በመጀመሪያ ዙር ለ45 ቀናት የተሰጠውን የስብዕና ግንባታ ስልጠና አጠናቅቀው ለ10 ወራት በተማሩበት የሙያ መስክ የተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ሲሰጡ ለቆዩት የበጎ አድራጎት ወጣቶች የምስጋና የእውቅና ሰርቲፊኬት ተበርክቶላቸዋል።
በየጊዜው የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ አደረጃጀቶች በጋራ ሊሠሩ ይገባል ተባለ
በአካባቢው በየጊዜው የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን መፍታት ያስችል ዘንድ የጎፋ ዞን፣ የደቡብ ኦሞ ዞን እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የ
ቀን 2021-12-20
በጎፋ ዞን፣ በደቡብ ኦሞ ዞን እና በባስኬቶ ልዩ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ አዋሳኝ አካባቢዎች ሲከሰቱ የቆዩ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ የተገኙት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ጌትነት በጋሻው÷ በሦስቱ አጎራባች መዋቅሮች የሚገኙ ህዝቦች በባሕል፣ በወግ፣ በልማድና በልዩ ልዩ እሴቶች ተመሳሳይ የሆኑና ይህንንም ለረዥም ዘመን ጠብቀው የቆዩ በህገወጦችና ወንጀለኞች አጀንዳ እየተቀረፀ አከባቢዎቹ ሠላም እንዲርቃቸው ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡ የአካባቢዎቹን ሠላም ማስጠበቅና ወደ ቀደመ ሠላማቸው መመለስ ሀገሪቱ አሁን የገባችበትን ፈተና እንድትወጣ አስተዋፅኦ ያበረክታል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው÷ አመራሩ ከምንጊዜውም በላይ ቆራጥነቱን ማሳየት እንዳለበት ጠቁመዋል። አሁን ያለንበትን ወቅታዊ ሁኔታ ማሰብና አካባቢዎቻችንን በንቃት መጠበቅ ይኖርብናል ያሉት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ንጋቱ ዳንሳ ናቸው። መራሩ አንድ ሲሆን ህዝቡ አንድ ይሆናል፤ ህዝቡ አንድ ሲሆን የገጠሙንን ጥቃቅን ችግሮች በቅንጅት በማለፍ የህዝብ ለህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እናረጋግጣለንም ብለዋል፡፡ የባስኬቶ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ታመነ ታሚርሶ በበኩላቸው÷ “ቀደም ሲል አካባቢያችን የተረጋጋና ሠላም የነበረበት እንዲሁም የእርስ በእርስ ግንኙነቱም የጠበቀና ወንድማማችነት የሚታይበት እንደነበር አንስተዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎች ለዘላቂ ሠላም መገንባት የጋራ ዕቅድ መንደፍ፣ የውይይትና የዕርቀ ሠላም ኮንፈረንሶችን ማካሔድና የተቋረጡ የማህበረሰብ ግንኙነቶችን ማስቀጠል የአመራሮችና ባለድርሻ አካላት ሚና ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በማቴዎስ ፈለቀ አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!
ያግኙን
☏046-777-1536
ተዛማጅ ሊንኮች
Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved
Gofa,Ethiopia