የቱርሞ ዋሻ
ቀን 2021-12-14
ቱርሞ ዋሻ፡- የሚገኘው በመሎ ኮዛ ወረዳ በቶባ ቀበሌ ሲሆን 3 ሜትር ቁመት፣ 600 ካሬ ሜትር ሥፋት ያለው እና 300 ሰው የመያዝ አቅም ያለው ታዋቂ ዋሻ ነው ፡፡ የቱርሞ ዋሻ የአካባቢዉ ሰዎች ሲናገሩ በዋናነት ዋሻዉን የሚጠቀሙት በመንግሥት ለውጥ ጊዜ ወይም በጦርነት ጊዜ ለመሸሸጊያነት እንደሚጠቀሙት የሚነገር ሲሆን፤ የዋሻው በስተቀኝ እና በስተግራ በኩል በሁለት ፏፏቴዎች መሀል በመገኘቱ፤ በሌሎች አከባቢዎች ካሉ ዋሻዎች ሁሉ በዓይነቱ ለየት ያደርገዋልል፡፡ የዋሻዉ ግድግዳው፤ ጣሪያው እና ወለሉ በዓለት ላይ የተሠራ ጠፍጣፋ የሊሾ ወለል ወይም በሴራሚክ የተነጠፈ ምንጣፍ ይመስላል፡፡ ይህ ዋሻ የአከባቢዉን ሕዝብ ከጠላት ይሁን ከሌላም ከሚያጋጥማቸዉ ንብረቶቻቸዉን ይዘዉ የሚጠለሉበት ዋሻ ሲሆን፤ ከብቶችን ግን ይዞ መግባት እንደ ማይቻልም (አቶ ታዬ ቶራ) ይናገራሉ፡፡ ይህ ድንቅ ዋሻም የሚገኘዉ በመሎ ኮዛ ወረዳ በቶባ ቀበሌ ነዉ፤ ከወረዳዉ ዋና ከተማም ወደ ቶባ ሲኬድ ሦስት ትላልቅ ወንዞችንም ማቋረጥ የግድ ነበር፤
የበልጣ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስያን
ቀን 2021-12-14
በ1818 ዓ/ም የተመሠረተ ይህ ዕድሜ ጠገብ የበልጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክን ታቦቱ በመጀመሪያ ከወደ በልጣ አቅራቢያ “ቦላ ጋባላ ቦህታማ” በሚባል ሥፍራ መጥቶ እንዳረፈ የቤ/ክያኑ ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ በ1818 ዓ/ም አሁን በሚገኝበት ቦታ የሣር ኪዳን ቤት ሠርተው እስከ 1940ዎቹ ድረስ አቆይተዉታል፡፡ ከ1940ዎቹ በኋላ በአፄ ኃይሌ ሥላሴ ዘመን አሁን ላይ የሚታዬው ቤ/ክያን በድንጋይ እና በቆርቆሮ የተገነባ ሲሆን፤ በአሠራሩም የመጀመሪያውን የቤተክርስቲያኑን የሣር ኪዳኑ ቅርፅ ሳይቀየር ተሰርቷል፡፡ በሰዓቱ ደብሩን ይመሩ የነበሩ መሪ ጌታ አባ ገብረ ኢየሱስ ፤ መሪ ጌታ አባ ሚካኤል፤ እና አባ ገላዬ የሚባሉት አባቶች በተከታታይ ቤተክርስቲያኑን ከሸዋ በመምጣት በመምሕርነት ያገለገሉ እንደሆነም ይነገራል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ቤተክርስቲያኑ ለቱሪስት መስሕብነት ታሪካዊ እና ማራኪ ሆኖ ይገኛል፡፡ የቤተክርስቲያኑን መግቢያ በሮች ስንመለከት ሦስት በሮች እንዳሉት፤ በውስጡም ከሚገኙት አብያተ ንዋያት ከ20-30 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ሲደወል ድምፁ የሚሰማ ደወል፣ የብራና መጻሕፍት፣ ትልቁ መስቀል ከታቦቱ ጋር የሚቀመጥ ( ከታቦቱ ጋር አብሮ የመጣ መስቀለኛ የብረት መቆሚያ ያለዉ)፣ ትልቁ ከበሮ፣ ፅናፅል፣ የታቦቱ አልባሳት፣ የታቦቱ ድንኳን ወዘተ… ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በወቅቱም በመሎ ኮዛ ወረዳ ውስጥ ትምህርት ባለመጀመሩም በ1944 ዓ.ም በዚህ ቤቴክርስቲያን የቄስ እና የድቁና ትምሕርት መስጠት ተጀመረ፡፡ በ1956 ዓ.ም የሥነ-ጥበብ ትምሕርት በአከባቢዉ መስጠት እንደተጀመረ እና ብዙ አዋቂያን እንደተፈጠሩ የቤተክርስቲያኗ ታሪክ አዋቂዉ (አቶ ስዩም ጥላዬ) ይናገራሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ከቤተክርስቲያኑ ጋር አብረዉ የቆዩ፤ ዕድሜ ጠገብ ዛፎችም የቤቴክርስትያኑ ዙሪያ ከበዉ ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ዶቆማ፣ የባሕር ዛፍ፣ ዝግባ፤ ብሳና፤ ጥቁር እንጨት እና ለሎችም ይገኛሉ፡፡ እነሱም በሰው መቃብር የተተከሉ ሲሆኑ አራት አምስት ትውልድ ያስቆጠሩ ናቸው፡፡ ቤ/ክያኑ በጥር 10 የፀበል አገልግሎት ለሕዝቡ እንደሚሰጥ ይነገራል ፡፡ እስከ አሁኑ ድረስ ጥናት ባለመደረጉና የማስታወቂያ ሥራዎች ባለመሠራታቸዉ ምክንያት እንደ ሀገር ደረጃ ለቱሪስት መዳረሻ መሆን ሳይችል ቀርቷል፡፡
የቡልቂ ከተማ አልኑር መስጂድ
ቀን 2021-12-14
የእስልምና እምነት/ኃይማኖት ለመጀመሪያ ጊዜ በምስራቁ እና በረጅሙ በዘይላ የንግድ መስመር ወደ ሀገራችን እንደገባ እና በኢትዮጵያም የመጀመሪያዉ የአስልምና መደላደያ በሸዋ የማክዙማይት ሥረወ-መንግስትን በ9ኛዉ ክፍለ ዘመን እንደተመሠረተ (Sergew Hablasellase; the Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270 (1972) Addis Abeba university; p124) በፅሁፉ የሚያስረዳን ሲሆን፤ እስልምና ወደ ጊቤ ግዛቶች በግራኝ መሐመድ ወረራ ጊዜ እንደተስፋፋም በብዙ ምሑራን በስፋት ተፅፏል ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለም የአከባቢያችን ተማራማሪዎች፤ በጣሊያን ወረራ ወቅት የእስልምና ኃይማኖት ወደ ዞናችን በመግባት የመጀመሪያዉን የቡልቂ ከተማ አልኑር መስጂድ የገነቡበትን ሂደት እንዳለ ስንረዳ በቀጣይ ደግሞ ለተመራማሪዎቻችን በአከባቢያችን የኃይማኖቱን መስፋፋት በጥናት በማስደገፍ እንደሚያስረዱን ክፍት በማድረግ አሁን ስለምጂዱ ትንሽ እንበል፤- አባቶች እንደሚናገሩት የቡልቁ ከተማ አልኑር መስጂድ በ1928 ዓ.ም የኃይማኖቱ ኢማም/መሪ በነበሩት በሼህ ሙዘይን ሱሌይማን እና በአባኑሩ መሀመድ፣ በሀጂ አሕመድ መሀመድ እና በሀጂ ጣሂር የተቋቋመ ሲሆን በውስጡም ጥንታዊ ቁርአኖች፣ ሀዲሶች፣ የፊቂህ ኪታቦች (የጠቅላላ ዕውቀት ኪታቦች)፣ የመንዙማ ኪታቦች (በግጥም መልክ አላህን እና ነቢዩን ለማወደስ የተዘጋጀ የግጥም መድብል)፣ ተንቢህ/ሰለዋት የሚገኙ ሲሆን ጥንት በእጅ የተጻፉ ኪታቦች እና ቁርአኖች በሼህ ሙዘይን ሱለይማን ቤተሰቦች እጅ እንደሚገኝ የሐይማኖቱ አባቶች ይናገራሉ፡፡ (ምንጭ፤- የቡልቂ ከተማ ባ/ቱ/ስ/ጽ/ቤት)
ያግኙን
☏046-777-1536
ተዛማጅ ሊንኮች
Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved
Gofa,Ethiopia