በጎፋ ብሔረሰብ በጎፍኛ ቋንቋ የሚነገሩ ባሕላዊ ሥነቃሎች
ቀን 2021-12-15
በጎፋ ባሕል ዉስጥ ሥነቃል ትልቅ ቦታ የሚሰጠዉ እሴት ስለሆነ ጎበዝ አርሶ አደሮችን እና በተለያዩ የሙያ መስኮችም የተሰማሩ ዉጤታማ ሰዎችን ለማሞገስ እና ለማበረታት ሲጠቀሙበት በዚያዉም ልክ ሠነፉንም የስንፍናዉን ልክ ለማሳየት በሥነ-ቃላዊ አነጋገር ሸንቆጥ በማድረግ ከስንፍናዉ እንዲወጣ በማሰብ የሥነ-ቃላዊ የአነጋገርን ይጠቀማሉ፡፡ ለዛሬም በትንሹ ከጎፋ ስነቃሎች የተወሰኑትን ስነቃሎች እና ማስተላለፍ የፈለጉዋቸዉን መልዕክቶች እንደሚከተለዉ እናቀርባለን፡- 1) በምንጣሮ ጊዜ “ማንኤይ ሹሎ”! ፤-የመጀመሪያ እርሻ ተጀምሮ ከሆነ በብሔረሰቡ ዘንድ የትኛዉም ሥራ ሲጀመር ልጅም ሆነ አዋቂ ሳይመርቅ አልፎ አይሄድም በብሔረሰቡም ነዉር ነዉ (የተጣላም እንኳን ቢሆን ይህንን ሳይመርቅ አልፎ አይሄድም) ምክንያቱም ይህ በረከት ለሱም ሆነ ለሀገር የጋራ እሴት ነዉና መባሉ የግድ ነዉ፡፡ በተጨማሪም የሚመርቀዉም ግለሰብ በግልባጩ ምርቃቱ ለሱም እንደሚደርሰዉ በዕዝነ ልቦናዉ በማሰብ ይመርቃል፡፡ ከዚህ መነሻነትም ‹‹ማንኤይ ሹሎ››! ይላል 2) በስንጣቆ ጊዜ “ዎቆ ጋደይ ጋኮ”!፤- Wooqo gadey gakko ይህ ኩነት ከምንጣሮዉ በኋላ የመጀመሪያ ዙር እርሻ ወይም በስንጠቆ ጊዜ የመሚርቁት እና የተመነጠረዉ አረምእንዲበሰብስ እና ማሳዉ ለም እንዲሆን አየር እና ዉሃን በዉስጡ እንዲይዝ ታስቦ የሚመርቁት የምርቃት ነዉ፡፡ 3) ዘር ሲዘራ የተገኘ ከሆነ “ዶሎ”! “ካታይ ካሬቲ ሞኮ” ፤- Kathay mokko / የተዘራዉ እህል በጥሩ ሁኔታ እንዲበቅል አንድም የዘር ፍሬ እንዳይበላሽ የሚተላለፍ የምርቃት ነዉ፡፡ 4) በአረም ወይም በኩትኳቶ ጊዜ ከሆነ ”ካሬቶ”! ፡-“እራይ ቡኮ”! Kareeto Iray bukko፤- የሰብሉን ጤናማነት በመመኘት ለጥሩ ምርታማነት እንዲበቃ የሚባል ሥነቃ ...ተጨማሪ አንብብል ነዉ፡፡ 5) በመኸር ጊዜ ፡-“ባራቶ”! Kathay Baraato፤- ዓመቱን በሙሉ የተትረፈረፈ ምርት ይኑርህ የሚል ምርቃት ነዉ 6) በክምር ጊዜ ፡-“ባራቶ ሞማይ ኤሌ መንሶ”! Baraato Moomay Ele mentho/ ጎተራህ የተትረፈረፈ ይሁን የጎተራዉን ተሸካሚ ያስጨንቀዉ/ 7) ቤት ለሚሰራ ሰው፡- “መሄይ ኩሞ”! Mehey Kumo፤- ሀብት በሀብት ሁን፡፡ ቤትህን ከብት ይሙላዉ ተብሎ ይመረቃል፡፡ 8) ሸማ ለሚሰራ ሰው፡- “ዛርሞ”! Zarimo የሸማ ሥራዉ ዉብ እና ማራኪ ይሁንልህ ፤ ለለባሹም መልካም ልብስ ይሁንለት የሚል የምርቃት ዓይነት ነዉ፡፡ 9) ብረታ ብረት ለሚሰራ ሰው፡- “ሀሺያን ሀራ”! Hashiyan Haara/ በጥንት ጊዜ አንጥረኞች ለሚቀጠቅጡት ብረት ገንዘብ ከአርሶ አደሮች አይቀበሉም በመሆኑም ካሬ / በሚባል የጉልበት ዋጋ በመኸር ወቅት እህል ሲሰበሰብ ለአንጥረኛዉ ከየእህል ዓይነቶች ይሰጣቸዉ እና ይህንንም አንጥረኛዉ በገበያ ወስዶ በመሸጥ ገንዘብ በማግኘት ኑሮዉን የሚገፋበት ሂደት ሲሆን፤ ይህም ማለት በጉልበትህ ጥረህ ግረህ የልፋትህን አግኝ የሚል የምርቃት ነዉ፡፡ 10) እንሰት ለምትፍቅ ሴት፡- “እትማይ ኡቶ”! Itimay Utto/ እንሰቱ በሚፋቅበት ጊዜ ተፈላጊዉ ምርት ከእንሰቱ ላይ የሚገኘዉ ቡላ ስለሆነ ቡላዉ ይርጋ፤ ጥራት ያለዉ እንዲሆን በመመኘት የሚሰጥ የምርቃት ዓይነት ነዉ፡፡ 11) ልኳንዳ ለሚያርድ ሰው፡- “አሾይ አልኦ”! Ashoy Al770 / ከንግዱ ጋር በተያያዘ ገበያዉ በቶሎ ሥጋዉን እንዲያነሳ እና ተፈላጊ እንዲሆን፤ ከዋለ ካደረ ስለማይሸጥ ይህ እንዳይሆን የሚሰጥ የምርቃት ነዉ፡፡ 12) ቅርጫ ለሚያርድ ሰው፡- “አሾይ ወዶ”! Ashoy Wodho / ሥጋዉ ይበርክት የሚል ምርቃትን የሚያስተላልፍ ሥነቃል ነዉ፡፡ 13) ለመቃብር ቆፋሪዎች ፡- “ዱፎይ ማይኖ”! Duufoy Maynno፤- ሞት እርም ይሁን እንደማለት ነዉ ለብሔረሰቡ፡፡ 14) ሚስት ላገባ ወንድ፡- ”ሳዳን ወዳ ጋራቶ”! Sadan Wodha! Gaaratto!፤- ሠርተህ አሸንፍ፤ በነገሮች ሁሉ ስኬታማ ሁን፡፡ Gaaratto! Malte;- ሁሉን አቀፍ በረከቶች እንዲገጥመዉ በመመኙት የሚነገር የምርቃት ዓይነት ነዉ፡፡ 15) ባል ላገባች ሴት፡- “ጋደይ ዶሶ”! Gadey Doso/ ፤- አከባቢዉ ዓየሩ ሕዝቡ ሁሉም ነገር ይቀበልሽ ተወዳጅ ሁኚ የሚል የምርቃት ነዉ፡፡ 16) ለወለደች ሴት፡- “ሀባ ኔ ወደረይ ሽቅስ”! Habba ne woderey shiiqis! ሀባ ኔ ወደረይ ሽቅስ! በእርግዝና ወቅት የነበሩ ሸክሞችሽ ሁሉ እንኳን ቀለሉልሽ እንደማለት የሚገልፅ የምርቃት አይነት ነዉ፡፡ • “ፐንጊያ ፋድን ክያ”፤- Penggiya Padhin ke7a! መልካም ጤንነትን እና ዉበትን ጨምረሽ ከአራስ ቤት ዉጪ የሚልን ምርቃት እንደሚገልፅ ፡፡ • “ማታ ማፆና ድጮ”! Maata Maxona Dicco!/ የተወለደዉ ሕፃን ሣይታመም ሙሉ ጤንነት እንዲኖረዉ፤ጤነኛ እና አምራች ዜጋ ሆኖ እንዲያድግ በሚል ምኞት የሚተላለፍ የምርቃት ዓይነት ነዉ፡፡ 17) በቅሎ ለገዛ፤- “ወድሪያን አቆ” /wodiryan Aqo/ ሀብቱ በእጁ እንዲቆይ እና ሀብቱም ዘላቂነት እንዲኖረዉ ታስቦ የመሚረቅ ምርቃት ነዉ፡፡ 18) በአክብሮት ከበቅሎ ወርዶ ሠላምታ ለሚያቀርብ ሠዉ፤- “ቶጋይ ፓጮፖ” / Togay Pacopo/ ክብርህ /ሠጋርህ አይጉደልብህ / ለዘር ማንዘርህ ይተላለፍ እንደማለት ነዉ፡፡ ይህም በሠጋር በቅሎዉ ላይ የነበረዉ ሠዉ ሠዉ አክባሪነቱን፤ትህትናዉን በተግባር የሚያሰይበት እና ቀጣይ በረከትን የሚያገኝበት ሲሆን ይህም በብሄረሰቡ ዘንድ ለሠዉ ክብር የሌለዉ ፤ትዕቢተኛ ከሆነ በቶሎ ተሰባሪ ስለሚሆን ፡፡ ይህንን ሳይፈፅም የሚሄድ ሠዉም እንደሚከተለዉ ይተረትበታል / Aawun Bayna Togay Affon Yedees! / ከወጉ ያፈነገጠ ሥርዓት አልበኝነት ወደ ገደል ይከታል እንደማለት ይሆናለ፡፡ 19) ለጦርነት የሚሄድን ሠዉ፤- “ኦላ ዎዳ” / Ola Wodha/ የጦርነቱ አሸናፊ ሁን ፤ አትሽሽ የሚል ትርጉምን የሚሰጥ ምርቃት ነዉ፡፡ 20) አዲስ ልብስ ለገዛች ሴት፤- “አጊ ዉሮ” / Aggi Wuro/ የሚገዛዉ ልብ ጊዜያዊ ሀብት እንደመሆኑ መጠን ፤ የልብሱ ባለቤት ረዥም እድሜ እንዲኖራት እና ልብሱ ቀድሟት እንዲያልቅ፤ ነገም ሌላ አዲስ እንድትገዛ የሚያደርግ የምርቃት ነዉ ፡፡ የፅሁፉ አቅራቢ አቶ በላይ በዛብህ እና አቶ ጣሊያን ጣሰዉ
አብሮ የመሥራት እና የመረዳዳት ባሕል በጎፋ ብሔረሰብ
ቀን 2021-12-15
የጎፋ ብሔረሰብ አብሮ በመኖር፤ በመሥራት እና በማደግ የሚያምን ኩሩ ሕዝብ ሲሆን ብሔረሰቡም በሕገ-ልቦና በመመራት የቅንነት እና የአንድነትን ፈለግን ሲከተል መቆየቱ ለአሁን ትውልድ የኑሮ መሠረት፤ የሕይወት መንገድ መሪ በመሆን እና የሀገርበቀል እውቀቶች ባለቤት ሆኖ የቆየ እንዲሁም የብሔረሰቡ ልዩ መለያ ምሶሶ የሆነው የእርስ በዕርስ መደጋገፍ አንድነት እሴቶቹ ሁሉንም ያስተሳሰረ፣ ለጋራ ስኬትም ይሁን ውድቅት፤ የራሱ የሆነ ጠንካራ ኃይል ያለው መሆኑ በሕብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ፡፡ አንድነት ኃይል መሆኑን የጥንት አባቶች ሲተርቱ “ጉንዳን ተባብሮ የውሃ ሙላትን ይሻገራል” (Zimanddoy zattidi haatha kixa pinnees) በማለት የሕብረትን /የአንድነትን/ ጥንካሬ ያስረዳሉ፡፡ አንድ ግለሰብ በጎፋ ብሔረሰብ ሰብአዊ ማንነቱ የሚለካው ባከማቸው የሀብት እና ባመረተው የምርት መጠን ሳይሆን፤ በማሕበረሰቡ ዉስጥ በገነባዉ የአብሮነት እና የአንድነት ዕሴቶቹ ነዉ፡፡ ምክንያቱም እራሱን ከማሕበረሰቡ ያገለለ እና በንቃት ያልተሳተፈ ማሕበረሰቡ ያገለዋል ተብሎ ስለሚታመን በልቅሶው፤ በሠርጉ፣ በደቦው እና በውዴው በትጋት መሳተፍ ግደታው መሆኑና ከሕብረተሰቡ ከሚደርስበት ማሕበራዊ ሥነልቦና ጫና ለመዉጣት በነዚህ ማሕበራዊ መስተጋብሮች መሳተፍ የዉዴታ ግዴታ ይታመናል፡፡ ደቦ dago አንድ ማሕበረሰብ ከሌላው ማሕበረሰብ የሚለይበት በኑሮ ዘይቤያቸዉ እንደመሆኑ ለምቶ እና ተጠብቆ ለትውልድ መተላለፍ ካለባቸው ጥሩ የባሕል እሴቶች አንዱ ‹‹ደቦ›› dago ሲሆን ይህም አብሮነትን በማስተሳሰር፣ በጎነትን በማጎልበት እና በማጠናከር ማሕበራዊ ትስስርን የሚፈጥር የመረዳዳትን፤ የመተጋገዝን፤ ስሜት እና ወኔን የሚሰንቅ የባሕል እሴት ነው፡፡ የሰው ልጅ ...ተጨማሪ አንብብ ማህበራዊ እንስሳ እንደመሆኑ መጠን አብሮነትን እንጂ ብቸኝነት የማይመቸው ፍጡር በመሆኑ የቀድሞ አባታችን አዳም ህያው ምስክራችን ሲሆን ከዚህም ተፈጥሯዊ ክስተት እና መነሻነት በጎፋ ብሔረሰብ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ የደቦ ሥነ-ሥርዓት በማሕበራዊውም ይሁን በፖለቲካዊዉ አደረጃጀቶች የጎላ አስተዋጽኦን ያበረከተ እና በተግባር ጭምርም ያሳዬን እሴት መሆኑ ሀቅ ነው፡፡ ይህም በስፋት ሲገለፅ በብሔረሰቡ አብሮነት ውስጥ መተሳሰብ አለ በመተሳሰቡ ውስጥም መፋቀር፤ መጠያየቅ እና መተራረም አለ፡፡ ታዲያ እነዚህን ሁሉ ጥሩ የባሕል እሴቶቻችንን ብናለማቸዉ እና ብንንከባከባቸዉ ሕዝባችንን በከፍተኛ ደረጃ ሊጠቅም እና ወደ ተሻለ ከፍታም ሊያደርሳቸዉ እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ሀቅ ነዉ ፡፡ Gofa (ጎፋ) በደስታም ሆነ በሀዘን እንዲሁም ከዚያም ውጪ ባሉ የሥራ ወቅቶች በሕብረት የሚያከውኗቸው ባሕላዊ የትብብር ዘዴዎቻቸዉ በሰለጠነው እና በዘመናዊው ማሕበረሰብ ውስጥም ቢሆን ተመራጭነትን እና ተቀባይነትን ሊያገኙ ስለሚችሉ፤ ጎፋዎች የራሳቸዉ የሆነዉን ባሕላዊ እሴቶቻቸዉን ይበልጥ እየተንከባከቡ ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በቀደሙት የጎፋ አባቶች እና እናቶች ዘንድ ‹‹ደቦ›› ደሬ ደቦ ፣ፁንቃ hashe (ሀሼ)፣ ጌሌፋ፣ ugare ኡጋሬ፣ አሎ (allo) madda (ማዳ) የሚባሉ በቡድን የእርሻ ልማትን፣ የቤት ሥራን፣ የልቅሶ ሥርዓትን የሚያካሂዱባቸው የመተጋገዝ እና የመረዳዳት አደረጃጀቶችም ባለቤቶች ናቸዉ፡፡ “ደቦ” በአንድ ቀበሌ ወይም በአንድ መንደር የሚኖሩ ግለሰቦች ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውን እና ክህሎታቸውን በማቀናጀት የግብርና ሥራቸውን የቤት ሥራቸውን ተራ በተራ በየግለሰቦች ማሳ እና መኖሪያ አከባቢያቸው እየተዘዋወሩ ለመስራት የሚያቋቁሙት የሕብረት ዓይነት (Dere dago) የሕዝብ ደቦ ይባላል፡፡ ሕዝብ ደቦ /Dere dago/ የራሱ የሆነ የደቦ ዳኛ ያለበት እና በዚህ የትስስር ሥርዓት ዉስጥ በአከባቢው ያሉ አቅመደካሞች እንኳን ሳይዘለሉ የትስስሩ አባል ተደርገዉ ይታቀፉና የቡድኑም ሁሉም አባላት መሬቶቻቸዉን ማረስ፣ እህል ማሰባሰብ፣ የቤት ሥራ……ወዘተ በየተራ ተራ ይሰራሉ፡፡ ‹‹Dere dago›› ሕዝበ ደቦ ስፋት ያለው በግል ጥሪ ማድረስ እና መቀስቀስ በማይቻልበት ጊዜ በደቦ ዳኛ አስተባባሪነት የደቦ ባለቤት የሆነው ግለሰብ በ ደቦዉ መድረኩ ላይ ህዝቡን የቀነ ቀጠሮ እንዲጠይቅ ይደረጋል፡፡ በደቦ ዳኛው እና በአባላቱም የቀን ቀጠሮ ከተቆረጠ በኋላ፤ ግለሰቡ የደቦውን ዓላማ መልክት ለአባላቱ እንዲያስተላልፍ ይደጋል፡፡ ይህም የመልዕክት ሥርዓት (Maata tooho) ለምለም ሣር በአባላቱ ፊት ቆሞ Maate! Maate! ‹‹ማቴ! ማቴ! በዚህ ዕለት የእኔን ጉዳይ እንድታስፈጽሙ! እንድታስደስቱኝ! አቤት! አቤት! አቤት!፤ አደራ! ማቴ! ማቴ! በማለት ይህንን ለምለም ሣር ወደ አባላቱ ይወረውራል፤ በዚህም ጊዜ ከሕዝቡ የሚሰጠው ቅፅበታዊ ምላሽ ከሁለት አንዱ (በአወንታ/በአሉታ) ስለሚሆን፤ ለግለሰቡ ከፍተኛ ደስታ ወይ ጭንቀት፣ የሞራል ውድቀትን ወይም ወኔን፣ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለዉ ወይም የሌለዉ እንደሆነ እና ግለሰቡ በየትኛው ጎራ እንዳለ የሚገመገምበት እና በሕዝቡ የማሕበራዊ ተሳትፎ ሚዛን የሚመዘንበት፤ ይባስ ብሎም በኖረባቸው ጊዜያት ሁሉ የሠራው እኩይ ተግባር ካለም በሕዝብ ፊት የሚነበብበት እና ብቻውን በሕዝቡ ፊት የሚቆምበት ከባድ እና ልዩ ዕለት ነዉ ፡፡ ከዚህም በዘለለ ግለሰቡ የፈፀመው ደባ ወይም ተንኮል ካለም ሕዝበ-ንሳሀ የማያስሰጠው ከሆነም ሙሉ በሙሉ ከሕብረተሰቡ እንዲገለል፣ ከማሕበራዊ ሕይወቱም እንዲታገድ እና በደስታዉም ሆነ በሀዘኑም ሕዝቡ እንዳይተባበረዉ ማዕቀብ ይጣልበታል፡፡ ይህም ሥርዓት (Kureth hileth) ይባላል፡፡ ‹‹paxan hayqan darey oyichoppo! በደቦም ይሁን ከብቶቹም ከከብቶች ጋር አይገናኙ (Dagon wudiyan gahattoppo) ተብሎ እገዳ ይጣልበታል፡፡ በድንገት ከሕዝቡ ጋር ጥሩ ሕብረት እያለው ከእለት ወደ ዕለት እየተሳሳተ ወደኋላ የቀረ ሰው ከሆነ ግን ለቀጣይ ግለሰቡ ንሰሀ የሚያገኝበትን እና ሕይወቱ የሚታደስበትን፣ ከሕዝቡ ጋርም ዳግም የመኖር ተስፋው የሚለመልምበት ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ወደ ሕዝብ እቅፍ ውስጥ ዳግም የሚገባበት ዕድል ይሰጠዋል፤ ምክንያቱም አንድ ሰው ከማሕበራዊ ትስስር ውጪ በመሆን ብቻውን መኖር እንደማይችል የሚገነዘብበት በመሆኑም ግለሰቡ ያገኘዉ ንሰሃ ደስታውን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡ የ‹‹ማታ ቶሆ›› ሥርዓት በሕዝብ ፊት አንድ ሰዉ ይህንን ሥርዓት ሲፈፅም ተቀባይነት ያለው ከሆነ ‹‹saro gath! በደህና ያድርሰን ! ሲሉ፤ ነገር ግን ችግር ያለበት ከሆነ ‹‹ከሕዝቡ ምንም ዓይነት ምላሽ አይሰጥም! Zuuzumees ያጉረመርማሉ፤ የዚያኔ የዚህ ግለሰብ ጉዳይ በደቦ ዳኛች እና በሀገር ሽማግሌዎች በኩል ጥያቄ ቀርቦ አስፈላጊው ውሳኔ እንዲሰጥበት ተደርጎ ‹‹የማታ ቶሆ›› ቀነ ቀጠሮ ዕድል የሚሰጠው ፡፡ ከዚህ ሕዝባዊ ተግሳጽ በኋላ የትኛውም ጀግና፣ ተንኮለኛ እና አመፀኛ ቢሆን እንኳን ባሕሪውን በማሻሻል የሕዝበ ዓላማ በማንገብ በእውነተኛ ፍቅር እና ወኔ ሕብረተሰቡን የመቀላቀል ዕድል ስለሚሰጥ በጎ አስተዋጽኦዉ የጎላ ነው፡፡ ሕዝበ ደቦ ‹‹Dere dago›› ሕዝበ ደቦ Dere dago ውለታን መሠረት አያደርግም ምክንያቱም በትስስሩ ውስጥ አቅም ያለውም ሆነ የሌለው ስለሚካተት የሠራሁት ውለታ ይከፈለኝ የሚል ሕግ ስለሌለው አብሮነትን መሠረት በማድረግ በጋራ ዕድገት ላይ ብቻ ትኩረት የሚያደርግ ስለሆነ ከጊዜያዊ ጥቅሙ ይልቅ፤ በወደፊት ተስፋው ላይም በሚያጋጥመዉ ተፈጥሯዊ ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋ ሲደርስበት ይህ ማሕበረሰብ እንደመድን ዋስትና አስተማማኝ አጋርነታቸውን በተግባር ስለሚያረጋግጡለት ያለ ምንም ስጋት የመዳን ተስፋውን የሚያስቀጥልለት እሴት ነው፡፡ በ ‹‹ደሬ ዳጎ›› ትስስር የሚሳተፉ አባላት እንደግለሰቡ የእርሻ ማሳ መጠን፣ እንደ ሚሰበስበው የምርት መጠን፣ እንደሚሰራው የቤት ስፋት፤ እንደሚቆመው የምሶሶ ውፍረት እና ርዝመት ይወስናል እንጂ በቁጥር ይህን ያህል ተብሎ መግለጽ አይቻልም ምክንያቱም ጥሪው የተላለፈው ለሁሉም አከባቢ ነዋሪዎች ስለሆነ በ ‹‹ደሬ ደቦ›› የፆታ፣ የዕድሜ ልዩነት ሳይኖር ከልጅ እስከ አዋቂ በየደረጃው በመሳተፍ ለደቦው ስኬታማነት የበኩላቸውን ኃላፊነት በትኩረት እና በትጋት ይወጡታል፡፡ ‹‹ደሬ ደቦ›› የሥራው ክብደት እና ቅለት፣ የተግባሩ ሁኔታ እና የአሠራር አፈፃፀምን ይወስናል እንጂ፤ የተቆረጠ ሰዓትና ጊዜ የለውም፡፡ ዓላማውም የአንድን ግለሰብ የእርሻ ሥራው፣ ምሶሶው፣ የቤት ሥራውም ሆነ የሚሰበስበው ምርት በአግባቡ መከወኑ ነው፡፡ ሕዝበ ደቦ ‹‹ደሬ ደቦ›› ጠዋት ማለዳ፣ ቀትር ላይ፣ ከሰዓትም እንደ ሥራዉ ባሕሪይ ሊከወን ይችላል፡፡ ስለዚህ ውሳኔ ሰጪው የሥራው ሁኔታ መሆኑ ይታመናል፡፡ በሕዝበ ደቦ የሚከወኑ የተግባር ዓይነቶች፤- Boora dago (zeretha dago) Manned ago Gaadhe Badalla xunggo Gaashe cako Badalla goozo (mol77a) Tuussa gooshanne kaara shireshi Goda dago Hoota Gata dago ወዘተ ሲሆን የደቦ ሥነ-ሥርዓት በመሎ አካባቢ ፔሾ ደቦ / Peesho dago:- በመሎዎች ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው እና ድሀውንም ሆነ ሀብታሙ ባለው አቅም ለመሳተፍ ከፍተኛ ጥረት የሚደርግበት፤ጠንካራ የሆነ ሕብረት ሲፈጠር በየዘርፉ ያሉትን አባላትን ባካተተ መልኩ ተግባራትን ይወጣሉ፤ ይህም እንደ አባወራው የማሣ መጠን እና እንደ ዝግጅቱ ስፋት የሚወሰን ይሆናል ፡፡ ለምሳሌ፡- የቤት ሥራ ዛፌ ከሆነ በእያንዳንዱ ተግባር በደጎ ዳኞች አማካኝነት የተግባር ሥምሪት ይሰጣቸዋል፡፡ ለጨፈቃ /ለቀርከሀ/ ከ50-100 አባላትን ለግድግዳ / ከ100-150 አባላትን ለሰንበሊጥ/ ከ100 -200 አባላትን ለወፍቾ/ ከ50-60 አባላትን በጠቅላላው እስከ 500 አባላትን እንደየአቅማቸው በማሠማራት ሁሉንም ተግባራት በስኬት እንዲከናወን ከፍተኛ ኃላፊነትን ይወጣሉ፡፡ Peesho dago:- “ፔሾ ዳቦ” የውሎ ደቦ በ “ፔሾ ዳጎ” ለታላቅ እና ለተቸገረው ሰው ቅድሚያ በመስጠት የከበደውን ሸክም የሚያቀሉበት ሥርዓት ሲሆን በየትኛውም ወቅት እና ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለሥራው ስኬታማነት የራሳቸውን ዋጋ እና መስዋዕትነትን ይከፍላሉ፡፡ “በፔሾ ዳጎ” ሥርዓት ውስጥ “ዶፋ ፓርሶ” Dhofa parsso “ዶፋ ጠላ” የመጠጣት ሥርዓት ሲኖር ይህን ጠላ የሚጠጡ ትጉና ታታሪ የሆኑ እና በተክለ ሰውነታቸውም ፈርጠም ፈርጠም ያሉት ሥራውን የማቀላጠፍ ብቃት እና ሌሎችንም የማበረታታት፤ ለሥራዉ የማነሣሳት ወኔ ያላቸው እና በአጫዋችነታቸውም ወደር የሌላቸው ጀግና የሆኑ ወጣቶች እና ድምፃዊያን Dhofa parsso “ዶፎ ፋርሶ” እንዲጠጡ እና ኃይል እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ በመሆኑም እነኝህ “ዶፎ ጠላን” የጠጡት በማሣው ላይ ከደቦው በፊት ቀድመዉ የሚገኙ እና ለደቦዉ ስኬታማነት የበኩላቸውን ድርሻ በአግባቡ የሚወጡ፤ በመጨረሻም ስኬታማነቱን በጋራ የሚገመግሙ እና ለቀጣይ ባለ አደራ የራሳቸውን ዝግጅት የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ‹‹አካላቶች›› Achcha Asa Achcha Asa “አቻ አሳ”፡- እነኝህ የመጀመሪያውን ጠላ የጠጡ ወይም የተጋበዙ ጀግኖች የሥራውን ስፋት እና ጥበት የሚወስኑ አካላት ሲሆኑ፤ ከሥራው ስኬታማነት ባለፈ ምን ያህል ሄክታር ሸፈነ ምን ያህል ተሠራ? የምንለውን ጥያቄ ለመመለስ ዋና ተዋናዮች ‹‹ አቻ አሳ›› የሚያካልሉ ሰዎች ናቸው፡፡ እነኝህ ሰዎች (ጀግኖች የደቦ ባለቤት ማሣዉ ከታቀደው በላይ እንዲከናወን በመጀመሪያ የሥራውን መነሻ “አቻ” ሰፊ አድርገው ከዳርና ዳር ከመሀልም እንዲሁም በሁሉም ቦታዎች በመበታተን እና ከሌሎች ጋር በመቀላቀል በአጭር ጊዜ ሠፊ ሄክታር ሥራ እንዲሠራ የመጠርነፍ ሥራን የሚሠሩ ከፍተኛ ባለውለታዎች ናቸው፡፡ አንዳንዴም ‹‹የአቻ ሰዎች›› የሥራው መሀንዲሶች ተብለውም ይሰየማሉ፡፡ የራሳቸውንም ጉልበት ከማፍሰስ ባለፈ የተለያዩ አነቃቂ ስንኞችን በመደርደር፣ ኮሶ /የእርሻ መሳሪያዉን/ ወይም ዶማውን በማጋጨት፣ ባለቤቱን በማወደስ ለደቦ አባላት ተጨማሪ ምግብና መጠጥ በመሆን ጉልበታቸውን ስለሚያነቃቁ ከፍተኛ ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡ “ሞልአ” Mol77a በሕዝበ ደቦ ከሚከወኑ ተግባራት ‹‹Mol77a›› የተሰኘው የበቆሎ፣ የጤፍ፣ የዘንጋዳ፣ ማሽላን በሕብረት የማጓጓዝ /የመሰብሰብ/ ሂደቱንም ስንመለከት ሁሉንም ፆታዎች እና የእድሜ ደረጃዎች ባካተተ መልኩ ይከናወናል፡፡ የ”ሞልአ” የእህል መሰብሰቢያ ተግባር በአብዛኛ ከንጋቱ 10፡00 ሰዓት በየአቅጣጫው በአስተባባሪዎች ከፍተኛ ድምጽ እና ወኔ ባላቸው ወጣት ወንዶች “Denthetho Ankkes” ሲጀመር እያንዳንዱ እህሉን ለመሸከም እና ለማዘል ያዘጋጇቸውን ቁሶች ማለትም፤- ወንዶች፡- ዋሌ (መመንጠሪያ) ማጭድ፣ Shedhe (ሸዴ)፣ የበግ ሌጦ (Ite) ሴቶች፡- ማዘያ ወፍቾ እና ጨርቅ ይዘው በቅፅበት እየተጠራሩ በመውጣት በአንድ የመገናኛ ቦታ “ቃኤ” አምባ ላይ ተሰብስበው እያዜሙ ወደ ቆላ በመውረድ የየአቅማቸውን ተሸክመው እና አዝለው “Bayide” ባይደ›› የተሰኘውን ባሕላዊ ዜማ፡- -Bayde baqule – Oho--- hoo! -Shanbbara gadiyan Badalla ba77a zekkeke! Ohoo—hoo! እያዜሙ ምርታማነቱን እያወደሱ፣ የአከባቢውን /የመሬቱን ለምነት/ እያንፀባረቁ ሴቱ እና ወንዱ እየተጠባበቁ በአብሮነት መንፈስ ምርቱን ከማሳው እስከሚያልቅ ድረስ የትኛውንም መስዋትነት በመክፈል ይከዉኑታል፡፡ ስለዚህም አባቶች በየአባወራው ደጅ በጋራ ሆነው ልጆቻቸዉን በማበረታታት እና በመመረቅ ወኔ እንዲሰንቁ ፡- - Harggey Booley hinttena xaallo! - Olite! wodhite! Kanthite!----- እንዲህ እያሉ በማዜም የየድርሻቸውን ይወጣሉ፡፡ “ሞልአ” የመስቀል በዓል መቃረቢያ እና ዋዜማም ስለሆነ (ጋዜ)ን እያዜሙ የአዲስ ዓመት መቀበያን እና የመስቀል መዳረሻን በይፋ እያበሰሩ በጋዜው ሴት እና ወንድ ጥንድ ጥንድ ሆነው የባሕል ጭፈራውን ያደምቁታል፡፡ በመሆኑም ወቅቱ ምርት የሚሰበሰብበት ወቅት ከመሆኑም ጋር ተያይዞ “ሞልአ” የመተጫጭያ፤ የፍቅር ጓደኛ መፈለጊያ “Washa wode” ስለሆነ የነበራቸውን ውስጣዊ ፍቅርን በሞልአ ዜማ ልጃገረዶችን በማወደስ ፍላጎታቸውን ይገልፃሉ፡፡ በዚህም መሠረት፡- Kocera dagga agenee Malara xoossa galatee መልኳን ከጨረቃ ጋር በማወዳደር፣ የልጅቱ መልክ የፈጣሪ ጥበብ የታከለበት መሆኑን በማንፀባረቅ ንጹህ ፍቅራቸውን በዜማ ይገልፁላታል፡፡ ልጃገረዶችም እርስ በዕርሳቸዉ በመጠቃቀስ የግጥሙ ስንኙ የተገጠመዉ፤ በእነሱ ላይ ማነጣጠሩን እና በየትኞቹ ላይ እንዳተኮሩ በቀጣይ ስንኞች ይለያሉ ፤- ረጃጅሞችን፡- Miixa tucha pargguissee Qayixe Dosonna suule eqaame ቀጫጭኖችን ፡- Yooshsha yolole Xeessara kafo enxxarssee አጫጭሮችን፡- Urqqara cadda agunthe Saapho sitike suI77e geela7e ለአቅመ ሄዋን የደረሱ ልጃገረዶችን በእንደዚህ መልክ በግጥም ስንኞች ለፍቅር በማነሳሳት የሕብረት ሥራውን “ሞልአ” በከፍተኛ ጉጉት እና ፍቅር በእውነተኛ ወኔ እንዲከናወን እና በመጨረሻም ሲጠቃለል ምግብ መጠጡ ተዘጋጅቶ በአባቶች ምርቃት ለዓመቱ ያብቃን ከቁጥር አያጉድለን በማለት መልካም ምኞታቸውን በመለዋወጥ ይለያያሉ፡፡ የሞልአ” ወግን በአጭሩ እንዲህ ካስቃኘናችሁ ከ‹‹ሞልአ›› ወግ እንመልሳችሁ እና ወደ “ሕዝበ ደቦ” እንውሰዳችሁ፤ የእያንዳንዱንም ድርሻ እናውጋችሁ፤ የአባቶች ድርሻ፡- ታላላቅ አዛውንቶች በሕብረት ሆነዉ ለብቻቸዉ ይቀመጣሉ ከነሱም ጋር Baltteeta “ባልቴታ” ሴት እናቶች ተቀምጠው ለብቻ ለእነሱ የተዘጋጀ “ቦርዴ” ጠላን እየጠጡ የአብሮነታቸውን ጊዜ ዕድሜ እንደማይገድባቸዉ ያረጋግጣሉ፡፡ አባቶችም እንዲህ ብለው ይመርቃሉ፡- Zin77ay dhubboppo eqqay caddoppo Min uusayo uyin dee7iso Oosoy ushachecho-------- በማለት መልካሙን ይመኛሉ፡፡ Baltteeta:- ያረጁ መውለድ ያቆሙ ሴቶች (Shoddidayssata) እናቶች፡- ለባለ ደቦዋ ባለቤት ለሆነችው ሴት፤- በጉልበትም ሆነ በቁሳቁስም አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ፣ በርበሬውን በመዳጥ፣ ቂጣ በመጋገር፣ ማባያውን በማብሰል፣ ጠላውን በመጥመቅ “Dinbbo Daathi parsso ago dago” ላይ በንቃት በመሳተፍ የተጣለባቸውን የሥራ ድርሻ በትጋት ይወጣሉ፡፡ ወጣቶች ፡- ሴቶችም ሆኑ ወንዶች የደቦው ዋና ተዋናይ ስለሆኑ ድርሻቸው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ይህም፡- ወጣት ሴቶች ምግብ በማቅረብ፣ የማገዶ እንጨት በማምጣት፣ ውሃ በመቅዳት፣ እና ጠላውን በመቅዳት በዋጋ የማይተመን ድርሻቸውን በብቃት በመወጣት ልዩ የደቦዉ ማድመቂያ ውበት ይሆናሉ፡፡ የልጆች ድርሻ፡- መጠጫ እና መመገቢያ ዕቃዎችን በመሰብሰብ፣ መቀመጫዎችን በማዘጋጀት፣ አካባቢዉን በማጽዳት አቅማቸዉ የፈቀዳላቸውን ሥራ በመሥራት የደቦውን ሥርዓት እና ወግ በመለማመድ የነገ ሀገር ተረካቢነታቸውን እና አብሮነታቸውን በማጠናከር የድርሻቸውን ይወጣሉ፡፡ ይህ ሁሉ ትስስር በሕብረተሰቡ ዘንድ ዘመን የማይሽረው ዕድሜ የማይገድበው፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ እና ለዛሬዉ ፖለቲካዊ ሆነ ማሕበራዊ አደረጃጀቶች፤ የራሱ የሆነ ጉልህ ድርሻ ያለው እና ስያሜው ይቀየር እንደሆን እንጂ የባሕል እሴትነቱ ራሱ መሆኑ የማያጠራጥር ሀቅ መሆኑን ልብ ልንለው ይገባል፡፡ የአብሮ መሥራት (ደሬ ደጎ) የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አረጋዊያንን የዕድሜ ጣሪያንም ያረዝምላቸዋል የሕዝብ ትስስርን ያጠናክራል፤ የእርስ በዕርስ የመደጋገፍና የመረዳዳት ስሜትን ያዳብራል ደቦ መዝናኛም ስለሆነ ጭንቀት እና ድብርትን ይቀንሳል በሕዝባዊ ጉዳዮች የመወያየት እና መፍትሔ የመስጠት፤ ባሕልን ያዳብራል ጤናማ አምራች ሕብረተሰብን ይፈጥራል የሀብት ብክነትን በማስቀረት ኢኮኖሚውን ከፍ ያደርጋል የመደማመጥ፣ የመከባበር እና የመታዘዝ ስሜትን ይፈጥራል ስደትን፣ ተመጽዋችነትን ያስቀራል አብሮነትን በማጠናከር ከግለኝነት ይልቅ ሕዝባዊ ስሜትን ይፈጥራል “Biittay biitta ayisees” ማለት በየትኛውም ሁኔታ የአንድ ማሣ ታርሶ የአንዱ ማሣ ሳይታረስ ቢቀር ተፈጥሮ ራሱ ቅር ይሰኛል ተብሎ ስለሚታመን በሕመምም ይሁን በሌላ ማሕበራዊ ችግር፤ አባወራዉ ከእርሻው ሳይውል ቢቀር መሬቱ እርስ በዕርስ መዛመድ አለበት በሚል እምነት በሕብረት ሆነው የሌላውን ማሣ በማረስ፣ መዝራት በማረም እስከ ምርት መሰብሰብ፤ የትኛውም መስዋዕት በመክፈል ሕይወቱን የተቃና ስለሚያደርገዉ ነው የደቦ ሥርዓት ግለሰባዊ ስሜትን ሳይሆን ሕዝባዊ ስሜትን ስለሚያንፀባረቅ “ቭታይ ቭታ አይሴስ” ሳይሆን ቢቀር “Biitay gomees” ለዚህ ነው የሌላው መሬት ሲታረስ የሁሉም አባወራ ሆነ እማ ወራ ማሣ መታረስ እና መቅላት አለበት የሚል የአብሮነትን ስሜትን የሚፈጥር እሴት ያለው ኩሩ ሕዝብ ነው፡፡ ይህም ሥርዓት ቀስ በቀስ ከመቅረቱ የተነሳ፤- የደቦ ሥርዓት በባለመተገበሩ እያጋጠሙን ያሉ ችግሮች የሀገር ሽማግሌዎች ተቀባይነት እና ተሰሚነት ቀንሷል፤ ደካማ ሥራ ፈት እና ከሥራ ንቅል የሆነ ዜጋ እንዲፈጠር አድርጓል፤ ከገጠር ወደ ከተማ ፍልሰትን ጨምሯል፤ ሕዝባዊ ወኔን ይቀንሳል፣ ግለኛ እና ራስ ወዳድ ዜጋ እንዲፈጠር አድርጓል፤ ኢኮኖሚውን በመቀነስ የመግባባትን ስሜትን መቀነስ ፈጥሯል፤ አብሮ መብላትን፣ መጫወትን እና መዝናናትን በመቀነስ የሀገር ሽማግሌዎችን ዕድሜንም በማሳጠር፤ ታሪክ አልባ ትውልድ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ የእርስ በእዕርስ መደጋገፍ ካለመኖሩ የተነሳ በሕዝቡ ውስጥ ያልተመጣጠነ ኢኮኖሚን በመፍጠር አንዱ ለሌላው ጥሩ አመለካከት እንዳይኖረው አድርጓል፡፡ አረጋዊያን በጋራ የሚዝናኑበት ሥርዓትም እንደነበረና አሁን ተቀባይነታቸው ከመቀነሱ ጋር ተያይዞ የእድሜ ባለፀጋ አባቶች እናቶች ያለጊዜ እንዲጠፉ በር ከፍቷል፡፡ 2.9.6 የ‹‹ደሬ ደጎ›› በጎፋ ከሌሎች ልዩ የሚያደርጉት የራሱ የሆኑ ባሕሪያት ከፍተኛ የሆነ ሕዝባዊ ውግንና ያለበት መሆኑ፡- አንድ በደቦ ትስስር አባል የሆነ በደረሰበት የጤና መታወክ ይሁን በማህበራዊ ችግር ሁል ጊዜ የማይሳተፍ ከሆነ በሀገር ሽማግሌዎች ጥያቄ የደቦ ዕድል (Maata) ተራ ይሰጠዋል፡፡ የእሱ ቅርብ ጓደኛ የተፈቀደውን ዕለት በማስመልከት (Maata tooho) መልዕክቱን ካስተላለፈ ሁሉም በበጎነት በመቀበል ከጤነኛው አባል በበለጠ ምግብ መጠጡን ሕዝቡ ራሱ ችሎ ከእርሻዉ ዕለት እስከ ምርት መሰብሰብ ድረስ ያለዉን ተግባር ሀደራውን ይወጣል፡፡ ቂም በቀል በዉስጡ የሌለዉ መሆኑ፤ አንድ ጊዜ አጥፍቶ ሕዝበ-ንሰሀን ያገኘ ግለሰብ ካለ ከዚህ በፊት የትኛውንም በደል ቢያደርስም እንዲህ በድሎናል ብሎ የመበቀል ርምጃ አይወሰድበትም፡፡ በለምለም ሣር አደራ መሸከሙ፤- በአንድ ጥሪ ብቻ ሕዝብን ካሳወክ የዕለት ተግባሩ አድርጎ ይንቀሳቀሳል፤ ይህም በየትኛውም ወር እና በየትኛው ቀን እንደሆነ ሁሉም ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ‹‹የእከሌ Maata ማታ-ቶሆ›› አለ ብለው እርስ በዕርሳቸዉ ተጠራርተው ይጠባበቃሉ፡፡ ሥርዓቱ ሕዝባዊ ውግንናን እንጂ የግለሰብ ውለታን አይመዝንም፣ ምክንያቱም ዓላማው መደጋገፍ ስለሆነ የደቦ ውለታን እንደ ልግስና እንደ አብሮማደግ እንጅ እንደ ዕዳ ይከፈልልኝ፣ ይደረግልኝ የሚል ጫና እና ፍላጎት የሌለው መሆኑ፡፡ Dago maso (“ዳጎ ማሶ” ጥሪን በፀጋ መቀበሉ) “ደጎ ማሶ” ማለት በደቦው ሥርዓት ለመሳተፍ ፍላጎት እያለው ባጋጠመው እክል ይሁን በጤና መታወክ ሳይሳተፍ ቀርቶ ማሕበረሰቡን የበጎ አገልግሎት አስተዋጽኦ እንድደረግለት ሲጠየቅ ይህንን ጥሪ በፀጋ በመቀበል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የከበደውን ሸክም በማቅለል ህዝባዊ ውግንናቸውን በተግባር ያረጋግጣሉ፡፡ Qodha (ቆዳ) Qodha(ቆዳ)፡- በብሔረሰቡ ዘንድ ከየትኛውም መደበኛ ተግባር ወይም የሥራ ሰዓት እና ሁኔታ ወጣ ባለ መልኩ የሚከናወን ተግባር፣ ወይም የሚገኝ ትርፍ ተብሎ ይታመናል፡፡ “ቆዳ” አንድ አባወራ ብቻውን የቤተሰቡን አባላት በማቀናጀት ወደ ሌላኛው የሕብረት ሥራ ከመሄዱ አስቀድሞ ማልዶ በመነሳት እንደ ሰውነት ማሟሟቂያ የቤተሰቡን አቅም እና የራሱንም አቅም የሚፈትሽበት ሂደት ነው፡፡ በዚህ ዓይነት የሕብረት ሥዉ በአብዛኛው ጊዜ የጓሮ አትክልት፣ የቅርብ ማሣዎች፣ እንዲሁም ከዚህ በፊት በሕብረት ወይም በደቦ ሲሰሩ ሳይጠናቀቁ የቀሩ ተግባራት በጎፍኛ (Gaxa bayizo “ጋፃ ባይዞ” የማጠቃለል ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ Hashe “ሀሼ” “ሀሼ” Hashattos “ሀሼቶስ” ፡- እንተባበር፣እንተጋገዝ ከሚል ዓላማ እና አንድነት በመነሳት ባልበዛ፣ ባልረዘመ እና ባልሰፋ ሁኔታ ተግባርን ለማሳለጥ ብሎም ብዙ ብክነትን እና ወጪን እንድሁም ቅንጦትን እና ወኔ ሳይኖር ተግባርን ብቻ መሠረት በማድረግ በጋራ የሚሰለፉበት የሕብረት የሥራ ዓይነት ነው “ሀሼ” “ዩርፌ” በልብ ወዳጅነት፣ በጓደኝነት እና በኢኮኖሚ ቅርርብነት በባልንጄራነት የሚፈጠር የሕብረት ዓይነት ነዉ፡፡ ምክንያቱም አንዱ ለሌላው ተጎድቶም ሆነ ተርቦ ቢመቸውም ባይመቸውም ተጠምቶም ይሁን ተርቦ ከችግር ለማውጣት የሚፈጠር የሕብረት ዓይነት ሲሆን፣ በተወሰነ ደረጃ በማሣ እና በድንበርተኝነት የጋራ ጥምረትን በመፍጠር ተግባራቸውን ይወጣሉ፡፡ ‹‹ሀሼ››/ዩርጌ/›› ውለታን መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ ማሕበራዊ ችግር እስከ ሚገጥማቸው አንዱ ለሌላው የሠራውን ውለታ በየሣምንታቱ ውስጥ የራሱን ድርሻ መቀበል አለበት የሚል እምነት ያለው የህብረት ዓይነት ነው፡፡ “ሀሼ” ከ3-6 ያሉ አባላትን ሲያካትቲት በተለይ የሣምንቱን የሥራ ቀናትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ይቀናጃሉ ‹‹ሀሼ›› ሌላ ተደራቢ ፕሮግራም ‹‹ደቦ›› ከሌለ እንደ ዕለቱ ሁኔታ የሥራ ሰዓቱ ይወስናል፡፡ Gelefa Zafe --Aldde ‹‹ጌሌፋ›› ወይም ዛፌ፡- በመሎ ‹‹አልዴ›› በግዜ በየአካባቢው የስያሜ ልዩነት ይኑረዉ እንጂ ከዓላማ አንፃር አንድዓይነት እና ተመሳሳይ ግብ አላቸዉ፡፡ ‹‹ጌሌፋ›› ዛሬ ‹‹አልዴ›› በይዘቱ ከደቦ ጋር ተመሳሳይነት ሲኖረው ከመጠን፣ ከስፋት እና ከዝግጅት አንፃር ልዩነቶች አሉት፡፡ ዓላማው፡- ትልቁን ደቦ ለማዘጋጀት የአቅም ማነስ፣ የሥራው መጠን ሰፋ ያለማለት ምክንያቶች ያገጠሙ እንደሆነ፤ የዚህ ዓይነት ሕብረት እንዲደራጅ ግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም በየትኛው የኢኮኖሚ ደረጃ ውስጥ የሆነ ሁሉ እንደየአቅሙ መጠን ሕብረቱን መቀላቀል ይችላል፡፡ “ጌልፋ” ዛሬ ና አልደ፡- አንድ አርሶ አደር በዓመት ውስጥ የእቅዱ አካል አድርጎ ይዘጋጅበታል፡፡ በብሔረሰቡ ዘንድ በየትኛውም የአዝመራ ወቅት ያለሕብረት የሚሳካ የሥራ ዓይነት ወይም ተግባር የለም፡፡ የፅሁፉ አቅራቢ አቶ በላይ በዛብህ
ያግኙን
☏046-777-1536
ተዛማጅ ሊንኮች
Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved
Gofa,Ethiopia
By logging in you agree to our Terms and Conditions and Privacy Policy
By logging in you agree to our Terms and Conditions and Privacy Policy