በጎፋ ብሔረሰብ የመስቀል በዓል ጨዋታ
ቀን 2021-08-23
የመስቀል በዓል በጎፋ ብሔረሰብ በዓመት አንዴ የሚከበርና በብሔረሰቡ ዘንድ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ከትንሽ እስከ ትልቅ ደሃውም ሆነ ሀብታሙ፣ በሁሉም ማህበረሰብ ያለውም ሆነ የሌለው በመስቀል በዓል አንድ የሚሆንበት ልዩ በዓል ነው፡፡ የመስቀል በዓል ቅድመ ዝግጅት በጎፋ ብሔረሰብ መስከረም ወር ሲገባ ዓመቱ ተጠብቆ የሚመጣውን የመስቀል በዓል ለማክበር የሚደረገው የቅድመ ዝግጅት እንቅስቃሴ ድንገት እግር ጥሎት ለመጣ ሰው የተለየ ትዝታ የሚጭር ነው፡፡ ለመስቀል በዓል 15 ቀናት ሲቀሩ እንኳን ሰው የቤት እንስሳትም እንዳይራቡ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ዝግጅት ይደረጋሉ፡፡ እያንዳንዱ አባወራ በቤቱ ለ7 ቀናት የሚበቃ የእንስሳት መኖ እና ውሃ የማቅረብ ሥራ ይሠራል፡፡ ማንኛውም አባወራ በመስቀል ሣምንት ከቤት የትም ርቆ ስለማይሄድ እቤት በዓሉ እስከሚያልፍ ድረስ በበቂ ሁኔታ የሚመገቡትን በየድርሻቸው ያዘጋጃሉ፡፡ በተለይም ሴቶች ጤፍ፣በቆሎ እና ሌሎች ለበዓሉ የሚሆኑ እህሎችን በመፍጨት ቦርዴ እና የጌሾ ጠላ በመጥመቅ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ሴቶች ለማገዶ እንዳይቸገሩ እንጨት ፈልጠው በማቅረብ እና ሌሎች ለበዓሉ የሚሆኑ ግንግና/Ginggina / የተባለው ጭራሮ በመለቀም፣የእርድ ቢላዋና እርዱ የሚፈፀሚበትን ቦታ በመወሰን የቅድመ ዝግጅት ሥራውን ማራኪ በሆነ መልኩ ያጠናቅቃሉ፡፡ ለመስቀል በዓል ካለው ከበሬታ የተነሳ ገና በዓመቱ እስከ ሚመጣ ታስቦ ቅድመ ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ ለልጆች ልብስ በዕለቱ የሚዘጋጅ ምግብና መጠጥ በተለይ ለመስቀል ሥጋ ተብሎ ዓመቱን በሙሉ በመቆጠብ በዕድር ዝግጅት ከመደረጉም ባለፈ ለመስቀል ተብሎ ለሚደረግ ነገር ሁሉ ሳይሰስት ማንም የሚፈጽመው ይሆናል፡፡ ለእርድ የሚሆኑ ሰንጋዎች ተገዝተው ይዘጋጃሉ፣ ለገንፎ የሚሆን በቆሎ ታምሶ ይፈጫል፣ቡላ ና ቆጮ እንዲሁም የሃረግ ቦዬ ይዘጋጃል፣ለቦርዴና ለጌሾ ጠላ የሚሆን ዝግጅት ይደርጋል፣ለጠጅና ለብርዝ ማር ይቆረጣል ይጠመቃልም፡፡ አከባቢው አዳይ አበባ ሲደመቅ በብሔረሰቡ አጠራር ቤላ ጭሻ /Bella ciisha / ጋራው ሸንተራሩ ሲያሽበርቅ አርሶ አደሩ በብሔረሰቡ ዘንድ በስፋት ከሚታወቀው ምርት በዋናነት ጤፍን በጊዜው ከአረም ነፃ የሚያደርጉበት ሰብሉን አብቦ የሚደምቅበት ነው፡፡ ወረሃ መስከረም መግቢያ የመስቀል በዓል መድረሻ ለመሆኑ መግለጫ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም መስቀል በዓል ሲቃረብ ልጆች በተሠማሩበት የሥራ መስክ ላይ ሆነው ከብቶችን በመጠበቅ ላይ፣ ለእንጨት ለቀማ፣ ውሃ ለመቅዳት እና ሣር ለማጨ ከአንድ በላይ ሆነው በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ያለማንም ቅስቀሳ ሲያዘሙ ይደመጣሉ፡፡ ሎያ ባይ ሎያ ባይ ሎያ ማሰቀላ ባይ ማስቀላ ኡፋይሳ ባይ ሙሳ ኡሻ ባይ ሲሎ ይዳመጣሉ፡፡ ይህ ማለት መስቀል እንኳን መጣህልን! የእኛ ደስታ!የዕኛ መዝነኛ መስቀል እንኳን መጣልህን!በማለት በጉጉት ስለሚጠባበቁት መስቀል በዓል ሲያዜሙ ይዳመጣሉ፡፡ በጎፋ ብሔረሰብ ለመስቀል በዓል የምግብና መጠጥ አዘገጃጀቱም ሆነ በሌላ የሚሰጠው ትኬረት ካሉት በዓላት ልዩ የሚያደረገው ሲሆን ለመስቀል ተብሎ የሚወጣው ወጪ የማንን በር የሚያንኳኳ እና ያለውን የሌለውም አመቱን ሙሉ በመቆጠብ ሳይሳሳ የሚያዘጋጅበት መሆኑ ነው፡፡ በተለያ በመስቀል በዓል ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠውን የቤትሰብ አባል ሆነው ተለያይተው የቆዩት የሚገናኑበት ከአከባቢው በተለያዩ ምክንያቶች ርቀው ያሉት በዳመራ ዕለት በመገናኘት ናፍቆታቸውን የሚወጡበት፣የተጣሉት የሚታረቁበት፣ሀዘን ውስጥ የነበሩ ሀዘኑን የሚረሱበት፣የተነፋፈቁየሚገናኙበት እና የትዳር ጓደኛ የሚይዙበት ዓይነተኛ ቀንና ጊዜ መሆኑን ልዩ ያደረገዋል፡፡ የምግብ ዝግጅት፡- በጎፋ ብሔረሰብ ለመስቀል በዓል የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች የሚዘጋጁ ሲሆን በዋናነት በዳመራው ዕለት የሚበላው ከበቆሎ የሚዘጋጅ ገንፎ ሲሆን ስያመውም / Masqqala dhote /በመባል ይተወቃል፡፡ አዘጋጃጀቱም ከሣምንት በፊት ወተት በማጠራቀም ምንም ውሃ ሳይታከልበት ከበቆሎ ዱቄት በተነጠረ ቅቤ፣በአይብና በቅመም የሚዘጋጅ ገንፎ ማለትም ነው፡፡ ይህ ገንፎ ከተዘጋጀ በኃላ ቤተሰቡ ሁሉ በአንድነት በመሰባሰብ እጃቸውን ወደ መሶቡ የሚሰዱበት ሥርዓት ከምንም በላይ ፈጣሪያቸውን የሚያስቡበትና የሚማፀኑበት ስለሆነ ማስቃላ የ! ዮ! እያሉ በጋራ የሚቀምሱበት፣በፍቅርና በአንድነት የሚበሉበት ሲሆን ከእንሴት ምርት የሚዘጋጀውን ቡላ /Ittima/ በአይብ፣የሐረግ ቦዬ በአዋዜ / Boyye/ በዋናነት በመስቀል በዓል ዕለት ለምግብነት የሚዘጋጁ የምግብ ዓይነቶች ናቸው፡፡ ከመጠጥ ዓይነቶች ደግሞ ቦርዴ /Bordde/ ከቦቆሎና ከጤፍ ሙጴ /Muudhe/ ጌሾ ፣ጤላ፣ ብርዝና ጠጅ የሚዘጋጅ ሆኖ ከዳመራ ዕለት ጀምሮ ስጠጡና ስጨፈሩ ቆይተው በ2ኛው ቀን ከወር መስከረም እስከ ነሐሴ መጨረሻ ድርስ በጋራ በመደራጀት የገዙትን የእርድ በሬ ለመስቀሥነል ሲጋ እርድ ይፈፅማሉ፡፡ ከደመራው በፍት የሚደረግ ሥነ -ሥራዓት፡- ከመስቀል በዓል በፊት በአከባቢው ወይም በቀበሌ ውስጥ ከቤተሰብ ሰው ሞቶባቸው በሀዘን ያሉ ካሉ የቀበሌው ሽማግሌዎችና አሮጊቶች ወደ ሀዘንተኛው ቤት ድረስ በመሄድ ለሞተው ሰው በማልቀስ ሀዘናቸውን እንዲያወርዱ ይጠይቃሉሀዘናቸውን ያወርዳሉ፡፡ የተጣሉም ካሉ ይታረቃሉ፡፡ ምክንያቱም ሀዘንተኛው ሀዘኑን ትቶ የተጣሉትም ታርቀው በፍቅርና በሠላም በጋራ የደስታ ተካፋይ እንዲሆኑ ለማድረግ ተብሎ በብሔርሰቡየሚደረግ ልዩ እና ዓይነተኛ ተግባር ነው፡፡ የደመራ ሥነ -ሥራዓት፡- በጎፋ ብሔረሰብ የመስቀል ዳመራ በውስጡ የተለያዩ መልዕክቶችን ያዘለ ነው፡፡ ከሣምንት በፊት ከቤተሰቡ በአባት ወይም በታላቅ ልጅ ለችቦ የሚሆኑና በራሳቸው ጊዜ የደረቁ ቀጥ ያሉ ጭራሮ ያዘጋጃል፡፡ የደመራ አዘገጃጀትን በተመለከተ በመጀመሪያ የደመራው እንጨት ቀጥ እያ መሆን እንዳለበት ይታመናል፡፡ ዓላማውም ዘመኑ መልካም ዘመን እንዲሆን ከበሽታ ከመቅሰፍት እንዲጠበቅ ልጆች በአስተሳሰብና በአመለካከት ቀና እንዲሆኑ በማሰብ ነው፡፡ስለሆነም በብሔረሰቡም ለቤት መሣሪያ አገልግሎት በስፋት ከሚጠቀሙት የጨፈቃ ዓይነት ሶልዜ /solize / ተብሎ የሚጠራው ሲሆን ለዚህ አገልግሎት ይውላል፡፡ የደመራ እንጨት አዘገጃጀቱም ከደረቅ ወደ እርጥብ እንዲሆን ተደርጎ ነው፡፡ይህም የሆነበት ምክንያት ዘመኑ የጥጋብና የሠላም እንዲሆን በማለት ነው፡፡ በደመራው እንጨት ጫፍ አደይ አበባው ይታሠራል፣ዓላማውም ተስፋ ውበትና በአበባ ውስጥ ዘርም ስለመኖሩ የደመራው ሥነ - ሥራዓት ለቀጣይ ትውልድ የማተላለፍ ሥራዓትን ያመላክታል፡፡ ዘራችንም ይበዛል ይሰፋል ለማለት ታስቦ ሲሆን የችቦ አስተሳሰርና የደመራ አቆራረጥ የቤተሰብ ቁጥር በዕድሚያቸው መሠረትና መጠን ይወስናል፡፡ ይህም በመካከላቸው መደማመጥና መከባበር እንዲሰፍን ያደርጋል፡፡ የችቦ አለኳኮስን በተመለከተ በመጀመሪያ ቀኑ ደንገዝገዝ ወይም ለዓይን ያዝ ስል አባወራው በወንድ ቁጥር የታሰረውን ችቦ አጠቃላይ በመያዝ ምሶሶ ካለበት ጎጆ ቤት ውስጥ ለገንፎ ከተጣደው ድስት ስር ከሚነድ እሳት የሁሉም ችቦ ከለኮሰ በኃላ በቀኝ በመታጠፍ ምሶሶሰውን በመዞር ምሶሶሰውን የከብቶች ጋጣና በበሩ ላይ በቀኝና በግራ የቆሙትን መሪ ግድግዳዎችን ማስቃላ ዮ! ዮ! እያሉ በተለከሰው እሳት እየነካካ ከቤት ወደ ደጅ ይወጣል፡፡ አባትም ማስቃላ ዮ! ዮ! እያለ ችቦን በዕድሜ ደረጃቸው ካካፈለ በኃላ መሃል ላይ ሆኖ በወንዶች ታጅቦ ማስቃላ ዮ! ዮ! ዳናው ዳና እያሉ በዱቡሻው ስር ወደ ተተከለው ደመራ ደርሰውን ዳመራውን ዞረው አባት በመጀመሪያ ችቦን ሲያስቀምጥ ሌሎች በዕድሜያቸውመሠረት ያሰቀምጣሉበህላዊ ጨዋታዎችን ይጫወታሉ ይጨፈራሉ፡፡ ችቦ ሲታሰርና ዳመራው ሲተከል ከወንዶቹ መካከል በዕለቱ መገኘት ያልቻለ ቢኖር የለም ተብሎ ደመራ ሳይወጣለት አይቀርም፡፡ ለሌሎች የሚደረገው ሁሉ ለእርሱም ይደረግለታል፡፡ በሌላው ልጅ ምትክ የታሰረውን ችቦና ዳመራ አባት ይይዛል፡፡ ዳመራው ከተለኮሰ በኃላ ማስቃላ ዮ! ዮ! እያለ ወደ ቤት ተመልሶ ከእናት ከእህቶቻቸው እና ከባለቤቶቻቸው ማስቃላ ዮ! ዮ! ከተባባሉ እንደገናችቦቻቸውን በመያዝ በባህላዊ መሪ ወደ ተተከለው ዳመራ ቦታ ያመራሉ፡፡ እዚያው ማስቃላ ዮ! ዮ! እያሉ በባህላዊ መሪው ተመርቀው ወደ የቤታቸው ይመልሳሉ፡፡ በዋናነት በህላዊ መሪው ቢታ ብታንቴ ነው፡፡ ቢታ ብታንቴ የሚባለው በአካባቢው ባላባት የዚያ ቀበሌ የመሬት አስተዳደር እና ባህላዊ መሪ እንዲሆን የተመረጠ ወይም የተሾመ ማለት ነው፡፡ ማስቃላ ዮ! ዮ! /Masqqala Yoo!Yoo!/ እያሉ የተለያዩ የበረከት ሀሳቦችን ይለዋወጣሉ፣ /መስቀል እንኳን መጣህልን/ ማለት ነው፡፡ አሰከትለውም እየደጋገሙ ማስቃላ ማስቃላ ዮ! ዮ! ዳናው ዳና አልባ ዙማዳን ዳና (አልባ ዙማ በአከባቢው የሚገኘው ትልቅ ተራራ ሲሆን እንደሱ እንኖራለን እንደ ማለት ነለን ው፡፡) ክንቲ ሻላዳን ዳና (ክንቲ ሻላ ማለት በአከባቢው የሚገኘው ትልቅ አለት ሲሆን እንደሱ እንኖራለን እንደማለት ነው፡፡) መርናው ዳና(ለዘለዓለም እንኖራለን) ማለት ነው፡፡ ሀረይ ካጨ ከሳናዳን (አህያ ቀንድ እሰከ ሚያበቅል ድረስ እንኖራለን በማለት ነው፡፡) ገላኦይ ገል ውራናስ ዳና ( ልጃገረዶች አገብተው እስኪያልቁ) ድረስ እንኖራለን፡፡ እንዲህ እያሉ እርስ በርስ ይሸካከማሉ ይተቃቀፋሉም፡፡ የመሰቀል ጊዜ ወጪ የማንንም በር የሚያንኳኳና ሀብታምና ደሃ የማይል ዓመቱን ሙሉ ተዘጋጅቶናቆጥቦ በመገኘት አንድ የሚሆኑበት መሆኑ በዓመቱ ውስጥ አንድ በሞት የተለየ ዘመድ አዝማድ ወይም ቤተሰብ ብኖር የመስቀል ደመራ ከመውጣቱ አስቀድሞ ይለቀስና ለመጨረሻ ጊዜ ከሀዘን የሚወጡበት ሥርዓት መኖሩ ድንገት በመስቀል ደመራ ዕለት ሰው ሞቶ ቢገኝ በብሔረሰቡ በመስቀል ደመራ እሳት ተበልቷል በሚል የማይለቀሱበት ሥራዓት መኖሩ፣የመስቀል ጊዜ ዘፈንና ጭፈራ የምግብና የመጠጥ ዝግጅቶች የመስቀል በዓል ደመራን ሥነ-ሥራዓት ልዩ የሚያደረጉ ናቸው፡፡ በጎፋ ብሔረሰብ የመስቀል ዘፈኖችና የአጨዋወት ሥራዓቶች የተለየ የሚያደርጋቸው ልዩ ባህሪያት አሉ፡፡ ከእነዚህም ለአብነት፡- • የመልከአ ምድር አቀማመጥንና የመሬቱን ለምነት መግለጫ የመሆኑ፣ • የብሔረሰቡ ተወላጆች የተለያዩ ሰብሎች አምራችና የሥራ ተነሳሽነታቸው ከፍተኛ መሆኑን አመላካችነቱ፣ • በግል ከመሠራት ይልቅ ተሰባስበው በጋራ የማምረት ልምድ ያካበቱ መሆናቸውን፣ • የሠላም ማብሰሪያ የደስታና የፍቅር መግለጫ ዋነኛ ድልድይ የመሆኑ፣ • የትዳር ጓደኞችን የመምረጫ ሁነት ስለመሆኑ በዓይነተኝነት ሊጠቀሱ የሚገቡ ናቸው፡፡ የመስቀል ዘፈኖችና አጨዋወት ሥራዓቶች ከባህሪያቸው አንጻር በ3 የከፈላሉ፡፡ እነዚህም፡- በመስቀል ከጅማረው ቀን እስከ መጨረሻው ወይም እስከ ሽኝት ቀን ድረስ የሚዘፈኑ/ጋዜ/ ኢኤ/ ጋሼ፣ሎያ፣ጋሳሊያ ኦይካ ጊሶሌ እንደትንፋሽ መሰብሰቢያ ዘፈኖች ሲበሉና ሲጠጡ የሚዘፈን ወይም የሁል ጊዜ ዘፈኖች ተብሎው ሊጠቀሱ የሚችሉት ደግሞ፡-ባራንቼ፣ላሌና ሄሎ ሄራሳ የሚባሉው እና በዋናነት የመስቀል በዓል የመጨረሻው ቀን ለሽኝት /ሞይዞስ/ የሚዘፈን፡- በብሔረሰቡ አጠራር "ሆሴ" /Hosse/ ናቸው፡፡ መስቀል በጎፋ ብሔረሰብከዳመራው ዕለት ጀምሮ በቀጣዮች 7/ሰባት ቀናት ማለትም እስከ መስቀል ሽኝት ቀን ደረስ ባለው በከፍተኛ ድምቀት የሚከበር ሲሆን በዚህ ጊዜ አዳዲስ ክስተት ስፈፀም ወይም የሚከናወን ሥራዓት አላቸው፡፡ እንደአጋጣሚ ሆኖ በሚያከብሩበት አከባቢ በደመራው ዕለት ሰው ቢሞት ቀብርና ሌሎች ሥራዓቶችን በሟቹ ደጅ ላይ ነዋሪዎች ተሰብስበው ይፈፅሙና የማይለቀስበት በመስቀል እሳት ተበልቷል በብሔረሰቡ አባባል ማስቃላ ታማን ሜተትስበማለት ለቀስተኞች ሀዘናቸውን እንዲያወርዱ በማድረግ ማስቃላ ዮ! ዮ! እያሉ ወደ ተጀመረው የመስቀል በዓል ሥነ-ሥራዓት የሚመለሱበት ሥራዓት አላቸው፡፡ሌላው ደግሞ የመስቀል ደመራ እሳት ከተሎከሰበት ቀን ጀምሮ 7 ተከታታይ ቀናት በመቁጠር በቤቱ መጠጥና መብል ያዘጋጀው አባወራ ብኖር ተጫዋቾችን ወደ ራሱ በራፍ በመጋበዝ እዚያው እንዲጨፈሩ እና እንድጫወቱ የሚደረግ ሲሆን በዋናነት ያለማንም ቅስቀሳ በራሳቸው በጎ ፍቃድ በሚኖሩበት አከባቢ ባለው አደባባይ ወይም በብሔረሰቡ አገላለፅ ቃኤ/ Qaa77e/ ላይ ወተው በአንድነት የሚጫወቱ ይሆናል፡፡ ታዲያ በትልቅ ጉጉትና ጥበቃ የመጣውን መስቀል በዓል ብሔረሰቡ በታላቅ ክብርና ወግ ሲያከብሩ ቆይተው መስቀል በሚሸኝበት ጊዜ እንደ አቀባበሉ ለሽኝቱም የሚፈፀማቸው ልዩ ልዩ ተግባራት ያደርጋሉ፡፡ በጎፋ ብሔረሰብ በመስቀል በዓል ወቅት አዘውትረው የሚጫወቱባቸው ጫዋታዎች፡፡ 1ኛ.ጋዜ (እኤ) ጋዜ ማለት ደስታ መልካም በዓል እንደ ማለት ነው፡፡ የጫወታው ሥራዓት፡- በቡድንየሚጨዎቱ ሲሆን በቡድን ውስጥ ወንዶችና ሴቶች ጥንድ ጥንድ ሆነው ቦታ በመቀያየር ይጫወታሉ በዚህ ጨዋታ በጎፋ ተወላጆች ምርታማ መሆናቸውን ለሥራ ያላቸውን ተነሳሽነት መልከአ ምድራዊ አቀማመጥ እያነሱ ይዘፍናሉ፡፡ ይህ ጫውታ ገና ለመስቀል ከ1 ወር በፊት እያለ እንደ ዋዜማ እየተዘፈነ ይቆይና ልክ የደመራው እሳት እንደተሎኮሰ እጅግ እየደመቀ ይቀጥላል፡፡ 2ኛ. ጋሼ የጨዋታው ሥራዓት፡- ይህ ጨዋታ በተለይ ኦ ሆያ ጋሼ ማለትም ጎፋ ብሔረሰብ በጤፍ አምራችነቱ የሚታወቅ መሆኑን የሚገልፅ ሲሆን የጤፍ ነዶ ክምር በኩንታል ያመረተዉን ለሁሉም በማድረስ ባለፀጋ መሆኗን ለመግለፅ የሚጠቀሙብት የጨዋታ ዓይነት ነዉ፡፡ ሁሉም ጭፈራዎች ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፈዉ ክብ ሠርተዉ ኦ ሆያ ጋሼ እያሉ ያጫወታሉ፡፡ 3ኛ. ጋሶሊያን ኦይካ፡- ይህ ጨወታ በተለይ መስቀል ከመድረሱ በፊት የቦቆሎ ምርት እያጋዙ የሚጨፈሩ ሲሆን ሥራውን ለማቀላጠፍ ስሉ ይህን ጭፈራ በመጨፈር የመስቀልን መምጫ በማወደስ ሂደታቸውን ይወጣሉ፡፡ አጨፋፈሩን በተመለከተ አ/አደሩ ደጅፍ በህብሬት ሆኖ እየጨፈሩ ካደመቁ በኃላ በሕብረት ወደ ቆላ ይመለሳሉ፡፡ በዕለት የተዘጋጀውን ቦረዴ እየጠጡ ይደሰታሉ፡፡ 4ኛ. ግሦሌ (ሆይግሶሌ)የጨዋታው ሥራዓት፡- ግሦሌ ፅንስ ሀሳቡ የጥጋብና ብሩህ ዘመን መሆኑን መቀበያ እርቅ ማድረጊያ በአዲስ ዓመት አዲሱን ጤፍ አስፈጭተው (አሽቶ) ማቡካትን (ጊንዴሳ) በአጠቃላይ የደስታ መግለጫነት ሲሆን በተጨማሪም (ሎሚ፣የሸንኮራ አገዳ ጥሬ ስጋ ወዘቴ…. እርስ በርስ በማቀባበል የአንድነትና የፍቅር መግለጫ ያደርጉታል፡፡ ወንድና ሴት ተመራርጠው ከሚወዱት ወይም ከሚትወዱት ጓደኛ ጋር በመሆን ዳሌ ለዳሌ እያገጫጩ የሚጫወቱት ጨውታ ሲሆን እጅግ ማራክ እና ውብ ጨዋታ ነው፡፡ 5ኛ. ሄራሳ(ሄሎ ሄራሳ ሥራታ፡- ይህን ጨውታ ከሁሉም ለየት የሚያደርገው ጨዋታው ለመስቀል ቦርዴ ዝግጅት ላይ በደንቦ(ፖጎሎ) በመዳጥ በመስቀል ዋዜማ ሴቶች ይጫወቱታል፡፡ ወንዶች ደግሞ ያልተጨመቀውን(ኦርጮ)እየተመገቡ በጭፈራ ያደምቁታል፡፡ በማግስቱ በልተውና ጠጥተው ሲያበቁ አባቶች ወደ እርድ ሥራዓት ይሄዳሉ፡፡ 6ኛ. ሆሴ/Hosse / የጨዋታው ሥርዓጥ ይህ ጨዋታ ከመስቀል ዋዜማ አንሥቶ እስከ ማብቀያ (ሽኝት) ጊዜ ድረስ የሚጫወቱት የመስቀል ጨዋታ ሲሆን መስቀል የሚሸኝበት ጊዜ ከበፊቱ ይልቅ ያለ የሌላ ኃይላቸውን አሟጠው በመጠቀም ወንዶችም ሴቶችም እየደጋገሙ ይጫወታሉ፣አጨዋወቱም 5 (በአምስት)ሜትር ልዩነት 2 (በሁለት) ቡድን ተካፍሎ የሚጫወቱበት ሲሆን ከአንደኛው ቡድን ወንዱ እየጨፈረ ሄዶ ከላለኛው ቡድን የሚወደውን ጓደኛ እየጨፈረ ይዞ ይመጣል፡፡እንግዳዋን (ሴቷን) እንደተቀበሏት ጭፈራውን ያደምቃሉ፡፡ በሌላ በኩል ከሌላኛው ቡድን ወንዱ እየጨፈረ መጥቶ ደስ ያለትሴት ልጃ ገረድ አቅፏት እየጨፈረ ይዟት ወደ ቡድን ይመጣል፡፡ የተወሰደበት ቡድን ወንዱምላሹን ያችን ልጃገረድ አቅፏት እየጨፈረ ይመልሳል፡፡በዚህ ዓይነት ጨዋታው ለመተጫጨትም መነሻ ይሆናል፡፡ 7ኛ. ባራንቼ፡- ባራንቼ ማለት ሠላም፣ፍቅር ማለት ሲሆን አገልግሎቱም የተጣሉትን ለማስታረቅ፣ቂም በቀል የለም፣ቂም ያሰበ ቢሮር እንደመረገም ስለሚቆጠር ጓደኛውን ለማስታረቅ፣ እርስ በርስ መግባባት እንደሚችል እነዚህ ሁለቱ ጨዋታዎች በጎፋ ብሔረሰብ የጨዋታ ሥርዓት ለመስቀል፣ለጥምቀትና ለደቦ ሥራ ጊዜ እየበሉና እየጠጡ ለመዝናናት(ባሎቴሳስ) የሚጫወቱት የጨዋታ ዓይነት ነው፡፡ 8ኛ. ላሌየላሌትርጉሙም፡- ሀገርን ከሀገር ጋር በማወዳደር ጀግንነት ምርታማነትን ለማሳየትና ለማወዳደር ህብረተሰቡም ሆነ ግለሰቡ ይሞግሳል፣ይወደሳል፡፡ የብሔረሰቡ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ይዘትን ለመግለጽም ያገለግላል፡፡ ጨዋታውን ድምፃዊያን (አውጪዎች) ተራ በተራ ሆኖ ሲያቀነቅኑ ታዳሚዎች ይቀበላሉ፡፡ ወንዶችና ሴቶች ከድምፁ ጋር ዜማንና ምቱን አዋህደው ይጨፍራሉ፡፡ 9ኛ. ሄላሎ /Heelalo/ ሄላሎ ይህ ጨዋታ መስቀልን በደስታ ከተቀበሉ በኃላ ከሦስትና ከአራት ቀን በኃላ የሚጫወቱት ጨዋታ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ዋና ምክንያት በጉጉት ሲጠባበቁ የቆዩትን የመስቀል በዓልን በደማቅ ሁኔታ ሲቀበሉ በደስታ እየጨፈሩ እየዘለሉ በሁለት እና በሦስት ቀን ናፍቆታቸውን ሲወጡ ይደክማቸዋል፡፡ የሄላሎ ጨዋታ ግን እርስ በርስ በመተቃቀፍ ክብ ሠርተው በእንድነት በተረጋጋ መንፈስ የሚጨፈሩት በመሆኑ ይመረጣል፡፡ 10ኛ. ወሎ ቦላዶ /Wollo Bolado/፡- ይህ ጨዋታ ከላይ በተራ ቁጥር ዘጠኝ ላይ ከተጠቀሰው ሄላሎ ከሚባለው ጨዋታ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን ዜማውም ሆነ አጨፋፈሩ ከሄላሎ ጭፈራ የመፍጠን ዓይነት ሁኔታ ሲኖረው እጅግ ማራክና ቆሞ ለሚመለከት ሰው ቀልብ የሚስብ የመስቀል ጊዜ ጨዋታ ነው፡፡ 11ኛ. ሊላ / Liilla/፡- ሊላ ሆያ ኤራ ሊላ ሊላ ማስቃላ ማታ ማስቃላ ሆምቦጫ ከሰሳ ሊሊ ሉትሻ ኩታ ሊላ-ሆ-ያ ኤራ ሊላ ማለት ሊላ ናልን እንጂ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ እንዲህ እንዲያ እያሉ በዜማ እያዘሙ ይጨፍራሉ ትርጓሜውም መስቀል እንኳን መጣልን ከሚለው ጋር የሚመሳሰል ሲሆን የመስቀል ጊዜ ያለው ደስታ የሚበላው የሚጠጣው መጠጥ በተለያዩ ጨዋታዎች ሀሴት በማድረግ በአጠቃላይ መስቀል ሲቀበሉ በጎፋ ብሔረሰብ ያሉው ደስታ ወደር እንደሌለው በመግጽ የሚጫወቱት ነው፡፡ 12ኛ. ሎያ ባይ ሎያ ባይ፡- ይህ ማለት ትርጓሜው የመስቀል በዓል ጥሩ ነው እንደ ማለት ነው፡፡ ታዲያ ይህ ጨዋታ የመስቀል በዓል መድረሻ መባቻ ስለመሆኑ የሚገልጽ ልዩ መልዕክት ያለው ነው፡፡ መስቀል ሲመጣ በዓመቱ በጎፋ ብሔረሰብ በአከባቢው ሳይጠይቅ የሚናገሩ የተፈጥሮ ምልክቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ አዳይ አበባ ያብባል የመጀመሪያ ጤፍ የተዘራው ያብባል ሎያ ባይ ሎያ ባይ፣ሎያ ማስቃላባይ፣ማስቃላይ ኡፋይሳ ባይ፣ሙሳኔ ኡሻ ባይ ፣ጋሼይካ ፊልጽምስ አድልኤይካ ጪይስ እያሉ በዜማ እያቀናቀኑ በተሠማሩበት የሥራ መስክ ላይ ባሉ ጊዜ ይመጣሉ፡፡ ታዲያ በዚህ መልኩ የተጀመረው መስቀልን ተቀብለው እስከ ሽኝት ሲጫወቱ ይቆያሉ፡፡ 13ኛ. ሄሎ ላሎ ሀሳ/ Heello laale Hasa/፡- የመስቀል በዓል ዓመቱን ጠብቆ በሚመጣበት ጊዜ በጎፋ ብሔረሰብ በማህበራዊ ግንኙነት ውስጥ ባህላዊ ክንዋኔዎች ሲፈፅሙ ከጥንት ጀምሮ ይስተዋላል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንደኛውን በሄሎ ላሎ ሀሳ ጨዋታ የሚንመለከተው ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ዓመት ጠብቆ መስቀል ስመጥ ከቤትሰቡ ውስጥ በሞት የተለየ ሰው ካለ የመስቀል ደመራ ችቦ በሚመጣበት ጊዜ በየቤቱ የሚለቀስበት ሥራዓት አለው፡፡ ታዲያ ሀዘንተኛ ቤተሰብ እቤቱ ስያለቅስ ሌላው ደግሞ በየቤቱ የመስቃላ ደመራ ከወጣ በኃላ በጋራ ሆነው በአደባባይ የዳመራ እሳት ለማውጣት ባዘጋጀበት ስፍራ በአንድነት የመስቀል ደመራ ካወጡ በኃላ ወደ የቤታቸው አይመለሱም ሄ-ሎ-ላሎ ሀሳ እያሉ እየጨፈሩ ወደ ሀዘንተኛ ቤተሰብ በመሄድ በጋር ለአንድና ለመጨረሻ ጊዜ አልቅሰው ሄሎ ሀሳ ጨፈረው ሀዘናቸውን እንድረሱ ለቅሶየወጣበትን ቤት ሁሉ በመዞር የሀዘን ማስረሻ ሥራ ይሠራሉ፡፡ ይህ ከሆነ በኃላ ሀዘንተኛው ሀዘኑን ይረሳና ወደ መስቀል ደስታው የሚቀላቀል ይሆናል ማለት ነው፡፡ 14ኛ. ባዳላይ ሻምባራ ደምባን ባራቶ፡- ይህ ጭፈራ በቡድን ሆነው ተቃቅፈው በሕብረት የሚጫወቱት ጨዋታ ሲሆን በአከባቢው በስፋት የሚታወቀውን የቦቆሎ ምርትን አጉልቶ የሚያሳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ መስቀልን በጎፋ በሔረሰብ ስንመለከተው እጅግ ብዙ መልዕክቶችን በውስጡ የያዘና ለብሔረሰቡ ተወላጂ ልዩ ክብርና አድናቆት በውስጡ አዝሎ የያዘ ታርካዊ በዓል ነው፡፡ ለምሳሌ የመስቀል ደመራ የሚወጣበት ቀን/tami ke7iya qamma/ በመባል በመጀመሪያ ዕለት ይጠራል፣ቀጥሎ ሁለተኛው ቀን /bido qamma/ተብሎ ይጠራል፣ የተባሉበት ምንያት 1ኛ የደመራን እሳት ዝናብ የሚያጠፋቤት ቀን 2ኛ እስከ 6 ሰዓት ቆይታ ለቅሶ ያለቤት በራፍን እየዞሩ አልቅሰው ሀዘን እንዲደርሱ የሚያረጉበት ከ6 ሰዓት በኃላ ለምግብ ዝግጅት የሚገቡበት ሲሆን ወንዶች የእርድ ሥነ -ሥራዓት የሚፈጽሙበት ጊዜ በመሆኑ ነው፡፡ 3ኛ. ማለትም ሦስተኛው ቀን በመስቀል ሣምንት ጶቴ/dhote qamma/ተብሎ ይጠራል፡፡ ምክንያቱም በዕለቱም አላፊው አግዳሚው ሁሉ ለመጣ እንግዳ በሙሉ ገንፎ ተገንፍቶ ይሰጣል፡፡ በልቶ ከቤት ስለሚወጣ /dhote qamma/ተብሎ ተሰይሟል፡፡ የመስቀል በዓል ሽኝት ጊዜ፡- መስቀል በጎፋ በሔረሰብ በሚሸኝቤት ጊዜ ለሽኝቱ ተብለው የሚደረግ የምግብ ዝግጅት ሥራዓት መኖሩ እና የመስቀሉ ሽኝት ጊዜ ዘፈኖች ተለይተው የሚታወቁ እና ከጨዋታ መነሻ ማንኛውም የብሔረሰቡ ተወላጅ የሆነ የሽኝት ጊዜ ጨዋታ መሆኑን መናገር መቻሉ ዓይነተኛና ልዩ ያደርገዋል፡፡ የመስቀል ዳመራ ከወጣበት ቀን አንስቶ ለሰባት ተከታታይ ቀናት ተቆጥረዉ የመስቀል ሣምንት ተብሎ የሚታወቁ በመሆናቸው የመጨረሻው ወይም ሰባተኛው ቀን መስቀል የሚሸኝበት ይሆናል፡፡በብሔረሰቡ አንደ ሁኔታው ለመስቀል በዓል ሽኝት ጊዜ የሚዘጋጁ የመብልና የመጠጥ ዓይነቶች አሉ፡፡ ከምግብ ዓይነት፡- ገንፎ፣ሥጋ፣ቡላ እና ሌሎች ከመጠጥ ዓይነቶች፡- ቦርዴ፣የጌሾ ጠላ፣ሙዴ፣ማር እና ሌሎች መስቀል በዓል በሚሸኝበት ቀን ከትንሽ እሰከ ትልቅ ቀኑን ጠብቀው /ቤላ ጪሻ/የአዳይ አበባ በእጃቸው ይዘው ወደ የሚጫወቱበት አደባባይ /ቃኤ/የሚወጡ ሲሆን ይህም ያለ ቅስቀሳ የሚፈጽሙትና ምናልባት ቀኑን ያላወቀ እንኳን ቢኖር የመስቀል በዓል ጨዋታውን ሰምቶ የሽኝት ጊዜ ጨዋታ መሆኑን ያውቃል፡፡ ሆሴ /Hosse /እና ጋዜ /Gaze/ በተደጋጋሚ በዕለቱ የሚጫወቱት ሲሆን ከሌሎች ቀናት በተለየ መልኩ በከፍተኛ ስሜትና ደስታ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በተለይ ሆሴ ጨዋታ ተቃቅፈው እየጨፈሩ ፊታቸውን ወደ ምስራቅ በማዞር 10 ሜትር ያህል ወደ ፊትና ኃላ እየሄዱ ጨዋታውን በድምቀት የሚጫወቱት ሲሆን ወደ ምሰራቅ የዞሩበት ምክንያት የሠላም፣የፍቅር እና የጥጋብ ዘመን ይሆናል ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሽኝት ጊዜ በአከባቢው ታዋቂ የተባሉ ሽማግለዎች ይገኛሉ፡፡ ቢታንቴዎች የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት በተገኙበት ፊታቸውን ወደ ምስራቅ የደርጉ ተጫዋቶች ወደ ፊት 10 ሜትር እየጨፈሩ ከተጓዙ በኃላ በአንድነት እጃቸውን ከፍ በማድረግ ማስቃላ ዮ! ዮ! ሳሮ ባዳ ሳሮ ያ! መስቀል በደህና ሄደ በደህና ተመለስ እያሉ በመካከላቸው የሚገኘውን ቢታንቴን ተከትለው በእጃቸው የያዙትን የአዳይ አበባ ወደ ምስራቅ ይወረውራሉ፡፡ በብሔረሰቡ አባባል ሆሴ ማስቃላ ላይታን ሳሮ ያ! መስቀል ደህና ሁን በዓመቱ በደህና ተመለስ እያሉ በድምቀት እየጨፈሩ ማስቃላ ዮ! ዮ! ሳሮ ባዳ ሳሮ ያ! መስቀል በደህና ሄደ በደህና ተመለስ ብለው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚሸኙበት ሥርዓት አላቸው፡፡ በእንዲህ ዓይነት መስቀል ሽኝት ከተደረገበት ዕለት ገምሮ እስከ መጪው ድረስ በብሔረሰቡ የመስቀል ነገር አይነሣም፡፡
የግጭት አፈታት ስርዓት በጎፋ
ቀን 2021-09-03
ግጭት በብያነዉ አሉታዊ ብቻ ሳይሆን ጠቃሚ ጎኖች ያሉት አንድ የሕይወት ክፍል ስሆን ከግብ፡ከዕሴት፡ከፍላጎቶች ና ጥቅሞች አለመጣጣም ጋር ተያይዞ የምፈጠር ሆኖ መንስኤዎችም መዋቅራዊ፤ፖለቲካዊ፤ኢኮኖሚያዊ እናማህበራዊ እንድሁም ባህላዊ እና ዕይታዊ በማለት ይከፈላል፡፡የሰው ልጅ በሚፈጥሯቸዉማናቸዉም መስተጋብሮች ትስስርናግንኙነቶች መልካም ና ጠንካራ ጎኖች እንዳሉሁሉ መልከ ብዙ የሆኑ ተከሳች ግጭቶችም ይኖራሉ፡፡ እነዚህን ግጭቶች የሚፈቱበት እንደየአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች አሉ፡፡ ከነዚህ የግጭት አፈታት ስርዓቶች የጎፋ ህዝብ ግጭት አፈታት ዘዴን እንመለከታለን፡፡ የጐፋ ህዝብ በመካከላቸው ግጭት እንዳይከሰት አኩሪ የሆነ ባህላዊ የመከላከያ ዘዴ ያላቸው ከመሆናቸው ባሻገር ሰው ናቸውና ግጭት ከተፈጠረም የራሱ የሆነ ልዩና ዓይነተኛ የግጭት አፈታት ሥርዓት አላቸዉ፡፡ በህዝቡ የግጭት አፈታት ሥርዓት የት በማንና እንዴት ይከናወናል? የጎፋ ህዝብ ሰፍሮ በሚገኝባቸው የአስተዳደር እርከኖች ሥር በሚገኙ ቀበሌያት የሚኖሩ ህዝቦች የራሳቸው የሆነ የግጭት አፈታት ሥርዓት የሚያከናውኑ (የሚፈፅሙ) ቁጥራቸው 7 እስከ 9 የሚደርሱ ሽማግሌዎች አሉት፡፡ የግጭት አፈታት ወይም የዳኝንነት ሥራውን የሚመራ ሰው “ቢታንቴ” ተብሎ ይጠራል ፡፡ “ ቢታንቴ” ማለት በእያንዳንዱ ቀበሌ ውስጥ የሚገኝ የመሬት ሥሪት /አስተዳደር / የሚመራ ሰው ነው ፡፡ የቢታንተ ማዕረግ /ሹመት/በዘር ሐረግ የሚመጣ ሣይሆን በንጉሥ /Kawo/ የሚሰጥ ሹመት ነው ፡፡ ከቦታ ቢታንቴ ወይም ከመሬት አስተዳደርጋር ዳኝነቱን የሚመሩ የሌሎች አባላት ምርጫ ሁኔታን በተመለከተ በድምፅ የሚመረጡ ሣይሆን የዚያ ቀበሌ የጎሣ ውይም የባህል መሪ መሆን ሲሆን ተጨማሪ መስፈርቱ በመሪነታቸው በህዝብ ተደማጭ መሆኑና ተናግሮ ሰውን የማሰመን ችሎታና ብቃት ያላቸው መሆን ይጠበቃል ፡፡ የጎሣ ወይም የባህል መሪ በእያንዳንዱ ቀበሌ ሊኖር ስለማይችል ሌላ አመራጭ መንገድ እነዚህ መሪዎች በቀበሌው ካሌሉ በታማኝነቱ በነገር አዋቅነቱና በማስታረቅ በህዝቡ ዘንድ የታወቀ ሽማግሌ ሊመረጥ ይችላል፡፡ ሽማግሌ ከአባልነት ስመረጥ መስፈርቶቹ እነዚህ ሲሆኑ ሽማግሌ ሲባል የግድ በዕድሜ የገፋ መሆን አይጠበቅም ፡፡ በዋናነት የጐሣ ወይም የባህል መሪ መሆን የተመረጡበት ዓቢይ ምክንያት የጎሣው አባል ወይም የባህሉ ተከታይ የሆነ ሰው በመሪያቸው ፊት ቀርቦ አይዋሽም ወይም ሀሰት አይናገርም ተብሎ ስለሚታመን ነው ፡፡ በብሔረሰባችን አውራ የሆነው የግጭት አፈታት ሥርዓትይኑር እንጂ ሁሉም ዓይነት ግጭቶች በእነዚህሽማግሌዎች አይፈታም፡፡ በግጭት አፈታት ሽማግሌዎች የማይታዩና ሥልጣናቸው ያልሆኑም ግጭቶች ወይም የማየት የመሽምገልና ዳኝነት ሥልጣን የሌሉአቸው የወንጀል ጉዳዮች አሉ ፡፡ የማየት ሥልጣን ያላቸው ከሰው መግደል በመለስ ያሉት ወንጀሎችና የፍ/ብሔር ጉዳዮች በአጠቃላይ ሲሆን የሰው መግደል ወንጀልን ጉዳይ የሚያየው ንጉሡ /ካዎ /ብቻ ነው ፡፡ ይህም ስባል በግጭት ፊቺ ሽማግሌዎች የሚታየው ዳኝነት የመጨረሻ ሣይሆን ያልተሰማማው ወገን በተለይ ወንጀል ጉዳዮች ይግባኝ በመጠየቅ እስከ ንጉሡ ወይም ካዎ ችሎት ድረስ መሄድ የሚፈቀድ ሲሆን የንጉሡ ውሣኔ የመጨረሻ ነው ፡፡ የግጭት አፈታት ሥርዓት የሚከናወንበት ቦታ/ሥፍራ/ የግጭቱ አፈታት ሥርዓት የሚከናወንበት ቦታ በዘፈቀደ እግር ባደረሰባቸው ቦታ የሚከናወንአይደለም እንደዘመናዊም የራሱ የሆነ ተቋም ያለው ባይሆንም የሚመረጠው ሥፍራ የጊዜውን መስፈርት የሚያሟላ መሆን አስገዳጅ ነው ፡፡ የጊዜውን መስፈርት ከሚያሟሉ መምረጫ መንገዶች ለመጥቀስ ያህል፡- ሀ/ ህብረተሰቡ በበዓላት ጊዜ ደስታቸውን ለመግለጽ ችግር ከተከሰተም ለመወያየትና ፀሎት ለማድረስ የሚሰበሰቡበት ቦታ መሆን ሲሆን ይህ ቦታ አደባባይ ወይም በአከባቢው አጠራር“ቡጫ” ይባላል፡፡ ለ/ በጐሣ ወይም በባህል መሪዎች ወይም በታዋቂ ሽማግሌዎች ደጅ ባለ አድባር ሥር ይሆናል ይህ አድባር በአከባቢው አጠራር (Dubusha) የሚባል ስሆን ቅጠሉ የማይራገፋ መሆን የግድ ይላል የአድባሩ ቅጠል በአየር ለውጥ ምክንያት የሚራገፍ መሆን ያልተመረጠበት ምክንያት የቅጠሉን መራገፍ ከቃለ አባይነት ጋር ስለሚያመሳስሉ ሲሆን ያለመራገፋን ደግሞ ቃላቸው ወይም ፍርዳቸው ፀንቶ የሚቆይና ዘላቂነት ያለው ይሆናል ፡፡ ተብሎ ስለሚታመን ነው ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አድባሩ የሚመረጥበት ምክንያት የብሔረሰቡ ተወላጆች ለጐሣ ባህል መሪያቸው ክብር ስለሚሰጡ ነው ፡፡ አጠቃላይ የግጭት አፈታት ሥርዓት አፈፃፀም /የዳኝነት ሥራ አካሄድ / አጠቃላይ የግጭቱ አፈታት ሥርዓት የሚፈፀመው በቃል ነው፡፡ በወንጀል ሆነ በፍ/ብሔር ተበደልኩ የሚል ወገን አቤቱታውን ለሽማግሌዎች መሪ ወይም“ቢታንቴ” በቃል ካቀረበ በዳይ ወይም ተከሣሽ ቀርቦ መልሱን እንድሰጥ ትዕዛዝ በመሪው ይተላለፋል፡፡በመሪው የሚተላለፈው ትዕዛዝ ወይም መልዕክት ለተከሣሽ የሚደርሰው “በጉራቻ” አማካኝነት ነው ፡፡“ ጉራቻ” ማለት በቀበሌው ህዝብ የሚመረጥ የበሰለ ጐረምሣ ወይም ጐልማሳ ሲሆን አገልግሎቱም የቀበሌውን ፀጥታ ማስከበር ሥራ የሚሠራና በንጉሡም ሆነ በግጭት አፈታት ሽማግሌዎች የምሰጡት ትዕዛዞች የሚፈፀም ሕግ አስከባሪ ወይም ታጣቂ ማለት ነው ፡፡ በዳይ ቀርቦ ክሱን ካመነ እንደ አቤቱታው ውሣኔ ይሰጣል፡፡በዳይካላመነየግራ ቀኝማስረጃእንድሰማ ተደርጎ ውሣኔ ይሰጣል፡የግጭት ፈቺ ሽማግሌዎች ብዛት ከፍተኛው ከዘጠኝ እስከ ሰባት ዝቅተኛው ደግሞ እስከ ሦስት አባላትያሉበትሊሆን ይችላል፡፡ ብዛታቸውም ጐዶሎ ቁጥር ላይ የተመሠረተበት የራሱ የሆነ ምክንያት አለው ይህ የሀሳብ ልዩነት በሽማግሌዎች መካከል ከተከሰተ ስብሰሳቢው ወደ ምስማማው ሀሳብ ላይ በመድረስ ውሣኔ ለማስተላለፍ እንዲያስችል ነው፡፡ከሣምንቱ ዕለት መካከል ሥራውን ለመሥራት በዋናነት የተመረጠው ዕለት ረቡዕ ነው፡፡ይህም ዕለት የተመረጠበት ምክንያት ከሣምንቱ ዕለታት አማካይ ዕለት አድርገው ስለሚወስዱ ሲሆን አስቸኳይ ሁኔታ ስያጋጥማቸው ዕለተ ዓርብንም በተጨማሪ እንደ ሥራ ዕለት ይጠቀማሉ፡፡ የውሣኔ አሰጣጥ ሥርዓትና ውሣኔው የሚያጠቃልላቸው የውሣኔ አሰጣጥን በተመለተ በዳይ ቀርቦ ካመነ ወድያውኑ ፍትህ የሚሰጥ ሲሆን ካላመነ የግራ ቀኝ ማስረጃ ተሰምቶ ከ15 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ውሣኔው ይሰጣል ፡፡ በበዳይ ላይ የሚተላለፈው ቅጣት እንደዘመናዊው የእሥራት ቅጣት ሣይሆን ለተበዳይ ካሣ በገንዘብም ሆነ በዓይነት እንዲከፍል ማድረግ የተወሰነውን እንድመልስ ማለት የይዞታ ክርክር ከሆነ ከካሣው በተጨማሪ ይዞታውን ማስመለስ ፣ ጉዳዩ ወንጀል ሆኖ የህዝብን ጥቅም የሚጐዳ ማለት ቃጠሎና ስርቆት ከሆነ ህዝቡን ይቅርታ እንድጠይቅ ማድረግ የመሳሰሉት ናቸው ፡፡ የግጭትን አፈታት ሽማግሌ ፣ አባላት ሥራቸው የሚሰሩት ያለ ክፍያ ሲሆን ምንም የሚሰጣቸው ነገር ባይኖርም በክርክር ጊዜ ስለምደክሙ በዳይ የሆነ ወገን “ የቦርዴ መጠጥ “ እንድቀጣ ስለምደረግ ይሄው መጠጥ ይቀርብላቸዋል፡፡ መጠጡን የሚጠጡት ብቻቸውን ሣይሆን በቦታው ካለው ሰው ሁሉ ጋር ሲሆን በዳይ አቅም ያለውና ከፍ ያለ በደል ያደረሰ ከሆነ የበርዴ መጠጥ ብዛት እስከ 7/ ሰባት እንሥራ ወይም በአከባቢው አጠራር (Xugga) ድረስ እንደ ሽማግለዉ ብዛት ሊቀጣ ይቻላል ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ አብሮ በማህበራዊ ሕይወት መኖር የግድ ሲሆን ሰው ናቸውና ግጭት አይፈጠርም ማለት የማይቻል ነባራዊ ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን የጐፋ ብሔረሰብ ግጭት መፈጠር አይቀረ መሆኑን የሚያምኑ ቢሆንም ከድርጊቶች መካከል አስቦ ሰው መግደል፣ስርቆት፣ቃጠሎየይዞታ ድንበርን መግፋት፣አስገድዶ መድፈርንና ሴሰኝነት በብሔረሰቡ ከዳር እስከ ዳር የተወገዙና የተኮነኑ ድርጊቶች ናቸው፡፡ የጐፋ ብሔረሰብ የግጭት አፈታት ሁኔታን ከዘመናዊው ዳኝነት ሥራ ጋር በንፅፅር ሲታይ ባህላዊ ዳኝነቱ የተሻለና ጠንካራ ጐን ያለው ነው ለማለት ያስችላል ፡፡ በዘመናዊው የዳኝነት ሥርዓት ውስጥ ቅጣት እሥራት ከመኖሩ በተጨማሪ ያጣውን እንድክስ ማድረጉ ያለ ሲሆን ካሣ ከማስከፈልና ከቅጣት ባለፈ በባህላዊ ዳኝነቱ ሁለቱም ወገኖች በውስጣቸው ቂም እንዳይያያዙ ዕርቅ ሁሉ እንዲያደርጉ ማድረግ ግዴታ ስለሆነ ነው ፡፡ በመዘናዊው ዳኝነት ባለቀ ጉዳይ እርቅ የሚባል ነገር ስለማይፈፀም ተከራካሪዎች ሥጋ ለባሽ ናቸውና ወደ ቀድሞው ማህበራዊ ሕይወት የመመለሱ ሁኔታ እንብዛም የለም ፡፡ስለዚህ ይህ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት በብሔረሰብም ሆነ በመንግሥት ሊበረታታ የሚገባና ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው ፡፡ ባህላዊ ዳኝነት ለጠንካራ ባህላዊ ዕሴቶቻችን ግንባታ መልዕክታችን ነዉ፡፡ (ምንጭ፤-የጋ/ጎ/ህ/5ቱ ብሔረሰቦች የግልናየጋራ ዕሴቶች መጽሐፍ፡2008 ዓ/ም የታተመ ገፅ 31-32፤tips of zeleqe dosa;written materials on gofa nationality about conflict resolution mechanisms;2007 e.c nonpublished) ከግጭት መንስኤዎችና ማስታረቅ ዘደዎች በጥቅቱ እነሆ…..// የግንጭት መንስኤዎች የተለያዩ ምክንያቶች ሆኔዉ ዉጤቱም “gomme”(የተሌያዩ መተላለፍ ዉጠቶች) እንደሆኔ ይነገራል፡፡በመሆኑም”gomme” የምባሉት በዋናኔት በሶስት ቦታ ይከፈላሉ፡፡ 1- ካዉሻ ጎሜ(Kawsha gomme) ስድብና የቃል መተላለፎች 2- ፓላ ጎሜ(Pala gomme) -ዘመድ ከዘመድ መጋባት/መዳራት፡ዝሙት፡ራስን ማጥፋት፡ግፍ መፈጸም -ሰዉ ከእንሰሳ ጋር ያለዉ አግባባዊ ያልሆኑ ግንኙነቶች 3- ግታ ጎሜ(Gita gomme) • ዉል ማፍረስ/ቃል መለወጥ • ማጭበርበር፡ክህዴት • የወሸት ክስ ና ምስክርነት---ወዘተ ተብለዉ ይታወቃሉ፡፡ የማስታረቅዘደዎች ደረ ዱላታ(Dere duulata)-በአከባብዉ ነዋሪ ወይም ህዝብ ዉስጥ ማጭበርበርና በዉል ያልታወቁ ጉዳዮችን ለመመርመር ና ለማዉጣት የምደረግ ነዉ፡፡ ጋደ ጭማ(Gade cima)-ትላልቅ የሆኑትን ማሌትም መሪን ከመሪ፡ መሪን ከህዝብ ጋር ለማስታረቅና ለማግባባት ላፑን ጭማ(Laapun cima)-በተሰባዊ ና ዘመድ ከዘመድ ጋር ያለን ችግር ለመፍታት ና ለማግባባት የምሰባሰቡበት ነዉ ፡፡ ዱቡሻ(Dubusha)-ተራናቀላል የሆኑ ግጭቶችን ለመፍታት የምደረግ ሰብሰባ ነዉ፡፡ ኩረሲ(Kuurethi)-ከተከራካርዎች መካከል ለባህላዊ ዳኝነቱ እምብተኝነቱን ለሚያሳዩ በማህበራዊ ተሳትፎ እና እንቅስቃሰዎች ላይ የምጣል የተለያዩ ዓይነት ማዕቀቦች ናቸዉ፡፡ጉፐሲ(Guupethi)-በግጭት አፈታት ግዜ የምደረግ ብይን ወይም ፍርድ ነዉ፡፡ ባራንቾ(Baarancho)-በማናቸዉም ግጭት ወቅት ይቅርታና ዕርቅ ማዉረድ ስርዓት ነዉ፡፡
በልዩ ልዩ ሥራዓት ወቅት የሚዘፈኑ በህላዊ ዘፈኖች፡-
ቀን 2021-09-03
በወሊድ ጊዜ የሚዘፈን ዘፈን ፡- ወላድ በምትወልድበት ጊዜ የሚዘፈነው ዘፈን ሲያሜው ሶሬ ይባላል፡፡ ሶሬ ሲዘፈን/ በሚዘፈንበት ጊዜ የተወለደው ልጅ ወንድ ከሆነ ህፃኑ በዘፈኑ በሚዘፈኑበት ጊዜ ጋሻ/ጎንዴሌ እና ጦር/ቶራ/ ምልክት በማዘጋጀት ከህፃኑ ፊት ለፊት በመስቀመጥ ሲሆን ህፃኑዋ ሴት ልጅ ከሆነች እንዝርት እየተፈለች ያለ የምመስል ከፊት ለፊቷ በማስቀመጥ ነው፡፡ ወንድ ህፃን ጋ ተወግቶ ይችላል ጀግና ይሆናል እንድ በማለት ሶሬ ሶሬ በማለት ይጫወታሉ፡፡ ለሴቷ ሲዘፈን መፍተል ትችላለች ቡሉኮ ጋቢ ማዘጋጀት ትችላለች እያሉ ሶሬ ሶሬ በማለት ይጫወታሉ፡፡ ለተለያዩ የዕምነት ሥራዓት እና የሚዘፈን ዘፈን ሄቦ ወዜ የተለያዩ ፌስት ባሎች የሚዘፈን ለመስቀል በዓል ጊዜ የሚዘፈን ላል ጋሼና ኦሴ ወዘተ… በለቅሶ ጊዜ የሚዘፈን ፡- ሻሬ ፈርጉልሳ፣ኦሊዛ፣ጎይሌ፣በዋናነት በለቅሶ ጊዜ ከሚዘፈኑ ዘፈኖች ሻሬ በመባል የሚታወቀው ትልቅ ቦታ የማሰጠው እና በተለያየ የሻሬ ዓይነቶች የሚታወቀው ለምሳሌ ጥርስ ላልበቀለ ልጅ ሻሬ የለም አይዘፈንም፡፡ ከዚህ ባለፈ የሻሬ ዓይነቶች ያልቄና የላ ዮሻ/ወጣቶች ሲሞት/ በትግልና በጀግንነት ሲሞቱ፡- ኤበሎ ኮያ ወሪያ ሀርጌ ምቃኘ አዛውንት ሲሞት ፡- ጋሞ አርሼ አፋ የሚባሉ የተለያዩ የሻሬ ዓይነቶች በፆታ በዕድሜ በመለየት የሚዘፈኑ ይሆናል፡፡ ለጦርነት ጊዜ፡- ሽለላ ፉከራ ጋይሮ ለጀግና ወይም ገዳይ ማወደሻ የሚዘፈን ሳባ በአደን ጊዜ የሚዘፈን ሴሎ በአደኑ አንበሳን፣ነብርን ስገድል የሚዘፈን ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ሜሶ በአደን ጊዜ ትናንሽ አውሬ የገደለ እንደሆነ በእርሻ ሥራ ወቅት በግልና በሕብረት የሚዘፈን እርሻው በዶማ የሚሠራ ሲሆን ሶዴ ኤኬ እርሻው በካሶ የሚከናወን ከሆነ ዛሮ በቆሎ ከማሣ የሚጋዝበት ጊዜ በሕብረት የሚያመጡበት ወቅት ባይዴ ምሶሶ ወደ ቤት የሚያመጡበት ጊዜ በሹመት ጊዜ የሚዘፈን ወዜ ፣በሶፌ ጊዜ የሚዘፈን ባራንቼ፣ኤራሳ ስርአቶ ፣አዳ ወዬ፣ላሎ ወላሌ፡፡ በጋብቻ ጊዜ የሚዘፈን፡- ወሎሎ ሜሌ ሾኦቢ ሾቤ፣ኤክድ ባና እምቴ/Ekidi Baana Immite Baanaw Dendda/ የተለያዩ መልዕክቶች / Dumma Dumma Kiitata/
ያግኙን
☏046-777-1536
ተዛማጅ ሊንኮች
Copyright © 2021-2025 Gofa Zone Adminstration.All Rights Reserved
Gofa,Ethiopia